በጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ

የፌዴራል ምርመራው እንደቀጠለ፣ ከፍተኛ አመራር ከስልጣን ተነሱ፣ ከመቶ ሚሊዮን በላይ ተገኘ
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሲቪል ሰርቪስ ቢሮ ሀላፊ የነበሩት አቶ ዳዊት ገበየሁ በህገወጥ ማዕድን ንግድ ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ የፌዴራል ምርመራው እንደቀጠለ ነው።
ከዚህ ቀደም በዎላይታ ታይምስ ሚዲያ እንደዘገብነው፣ የቀድሞ የኮንሶ ዞን ዋና አስተዳዳሪና የክልሉ ረዳት መንግስት ተጠሪ የነበሩት አቶ ዳዊት ከአራት ተጠርጣሪዎች ጋር በአዲስ አበባ በቁጥጥር ስር ውለዋል።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት አቶ ዳዊት እና ሌሎች ተጠርጣሪዎች በቦሌ ክፍለ ከተማ አካባቢ በህገወጥ መንገድ የተገኘ መርኩሪ የተባለውን ማዕድን ለመሸጥ ሲደራደሩ እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል።
ባለፈው ማክሰኞ ዕለት ግለሰቦቹ በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ ፍርድ ቤት የቀረቡ ሲሆን፣ መርማሪ ፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ጠይቋል። ምንጮቻችን እንዳረጋገጡትም ተጠርጣሪዎቹ በፖሊስ ጣቢያ እንደሚገኙ ይታወቃል።
በተያያዘ ዜና ደግሞ ዛሬ ይፋ የሆነው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ምርመራው እየሰፋ ሲሄድ አዋሽ ባንክ 87 ሚሊዮን ብር እንዲሁም ዳሽን ባንክ 112 ሚሊዮን ብር ከተጠርጣሪው አካውንት ውስጥ ማግኘታቸውን ያሳያል።
በአጠቃላይ ስድስት ባንኮች ውስጥ የሚገኙ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ገንዘቦች የማጣራት ሂደት መቀጠሉን ምንጮች ገልጸዋል። ይህ ሁኔታ እጅግ የሚያሳዝን መሆኑንም ብዙዎች እየገለጹ ነው።
በተጨማሪም ዛሬ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፕሬዚዳንት በፅሁፍ ባስተላለፉት ደብዳቤ የክልሉ ሲቪል ሰርቪስ ቢሮ ሀላፊ የነበሩትን አቶ ዳዊት ገበየሁን ከስልጣን መነሳቱን አሳውቀዋል።
የክልሉ መንግስት ይህንን መረጃ መቀበሉንና ግለሰቡ “ከኃላፊነታቸው ተነስተው በህግ መጠየቅ አለባቸው” የሚል ፅኑ አቋም መያዙንም ለማረጋገጥ ሞክረናል።
የፌዴራል ፖሊስ ይህንን ከፍተኛ የክልል አመራር ያሳተፈ የህገወጥ የንግድ ወንጀል ምርመራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ይጠበቃል። በቀጣይ ስለጉዳዩ የሚወጡ አዳዲስ መረጃዎችንም እንደደረሱን የምናደርስ ይሆናል።
👉🤝 እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ሰብዓዊነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚንፀባረቅበት መረጃዎች🙌
👉🤝 ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ነን🙏
👉🤝 ስለዘውትር አብሮነታችሁና ድጋፍ እናመሰግናለን🤲
🤜👁👀 #WT ሚዲያ👏