የኢትዮጵያ መንግስት በሀገሪቱ የታጠቀ ቡድን ባይኖር ከማን ጋር ጦርነት ይገጥማል ?

የትጥቅ ትግል ያስከተለው ሰቆቃ፣ የሰላማዊ ትግል አስፈላጊነት እና የፖለቲከኞች ኃላፊነት ላይ ያተኮረ ፅሁፍ በ WT ሚዲያ እንደሚከተለው ተዘጋጅቷል 👇
በታሪኳ ደም አፋሳሽ ግጭቶች ያልተለዩት ኢትዮጵያ ከዘመናት በፊት ጀምሮ የታጠቁ ቡድኖች በተለያዩ ምክንያቶች ጫካ በመግባት ከመንግስት ኃይሎች ጋር ሲዋጉ ኖረዋል። “የህዝብን ጥያቄ እናስመልሳለን” በሚል የሚደረገው ይህ ትግል በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ንፁሃን ዜጎችን ህይወት ቀጥፏል፣ የሀገር ሀብትም ወድሟል። እስካሁን ድረስ ከዚህ የኃይል ትግል ዘላቂ እና አበረታች ውጤት የታየ ነገር የለም።
በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን፣ አለም በሰላማዊ እና በሰለጠነ መንገድ ችግሮችን ለመፍታት በምትጥርበት ወቅት፣ በኢትዮጵያ የሰው ህይወት መስዋዕት የሚከፈልበት እና ሀገር የሚወድምበት የትጥቅ ትግል አሁንም በሰሜኑ እና በተወሰኑ ሌሎች አከባቢዎችም እንደ መፍትሔ አማራጭ መታየቱ በእጅጉ ያሳዝናል።
ለምን የሰላማዊ ትግል ስልቶችን በመጠቀም ዘላቂ ሰላምን እና ልማትን ማስፈን አንችልም?
የተለያዩ የዓለም ሀገራት ተሞክሮ እንደሚያሳየው ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት ስኬታማ የለውጥ እንቅስቃሴዎች የተገኙት በሰላማዊ የትግል ስልቶች ነው።
ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ በመደራጀት፣ በመወያየት፣ በመደራደር እና ህዝባዊ ንቅናቄዎችን በመፍጠር የሚመጣው ለውጥ ዘላቂነት ያለው ከመሆኑም በላይ አነስተኛ ዋጋ ያስከፍላል።
ኢትዮጵያ ከተመሰረተችበት ጊዜ አንስቶ የፖለቲካ ቁንጮዎቿ የትጥቅ ትግልን እንደ መፍትሄ ሲያዩ ኖረዋል። ይህ አካሄድ ሀገሪቱን ከአለም የኋላ ቀር ሀገራት ተርታ እንድትሰለፍ ከማድረጉም በላይ ለዘመናት የዘለቀ አለመረጋጋትን አስከትሏል።
የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ከዚህ ሁሉ የሰው ህይወት መጥፋት እና በቢሊዮኖች የሚቆጠር የሀገር ሀብት ውድመት መቼ ነው ትምህርት የሚወስዱት? ሰላማዊ ትግል ምንም ያህል ጊዜ ቢወስድም ማንኛውንም የህዝብ ጥያቄ ለማስመለስ ብቸኛው አስተማማኝ መንገድ መሆኑን መገንዘብ መቼ ይሆን?
ይህ ጉዳይ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የትኩረት ርዕስ ሊሆን ይገባል። ወጣቶች፣ ምሁራን፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና ሁሉም ዜጎች ስለ ሰላማዊ ትግል አማራጭነት በሰፊው ሊወያዩበት ይገባል።
የኃይል ትግል ያመጣውን ጥፋት በመገንዘብ፣ ለዘላቂ ሰላምና ልማት የሰላማዊ ትግልን መንገድ እንድንከተል ሁላችንም ድምፃችንን ከፍ ማድረግ አለብን።
መንግስት የታጠቀ ቡድን በሌለበት ሁኔታ ከማንም ጋር ጦርነት እንደማይገጥም ግልጽ ነው። የታጠቀ ቡድን ህግን ተላልፎ ህዝብን ሲያስቸግር ወይም ሀገርን ሲያተራምስ መንግስት ህግ የማስከበር ኃላፊነት አለበት። ይህንንም ሲያደርግ ጦረኛ ተብሎ ሊፈረጅ አይገባውም። ነገር ግን መንግስትም ህግን በማስከበር ሂደት ላይ ሚዛናዊ እና ጥንቃቄ የተሞላበት እርምጃዎችን መውሰድ ይኖርበታል።
ዋናው ቁም ነገር የታጠቀ ትግልን ከመጀመሪያውኑ የሚያስፈልግበትን ሁኔታ መፍጠር ማስቀረት ነው። ይህ ደግሞ ፍትሃዊ በሆነ የፖለቲካ ስርዓት ግንባታ፣ የህዝብን ጥያቄዎች በሰላማዊ መንገድ ለመመለስ ዝግጁ በመሆን እና ሁሉን አሳታፊ የሆነ የውይይት መድረክ በመፍጠር ይቻላል።
የኢትዮጵያ የወደፊት እጣ ፈንታ የሚወሰነው ፖለቲከኞቻችን እና መላው ህዝባችን ከታሪክ ስህተቶች በመማር ዘላቂ ሰላምን በሚያስገኝ የሰላማዊ ትግል ጎዳና ለመጓዝ ሲወስኑ ነው። ጊዜው አሁን ነው። By Journalist Natnael Gecho
👉🤝 እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ሰብዓዊነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚንፀባረቅበት መረጃዎች🙌
👉🤝 ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ነን🙏
👉🤝 ስለዘውትር አብሮነታችሁና ድጋፍ እናመሰግናለን🤲
🤜👁👀 #WT ሚዲያ👏