በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል 2 ቢሊዮን ብሩ የት ገባ ? ቀጣይ እሁድ ርዕሰ መስተዳድሩ ያዘጋጁት የ2 ሚሊዮን እራት ድግስ ጥሪ ካርድ ደረሰ ወይ ?
ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ የተሰበሰበ ገንዘብ ያለአግባብ መውጣቱ እና የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ስልጣናቸውን አላግባብ እየተጠቀሙ ነው በሚል ከባድ የገንዘብ ምዝበራ እና የስልጣን አላግባብ አጠቃቀም ውንጀላዎች ተሰምተዋል።
WT ሚዲያ የደረሰው ሰነዶች መሠረት፣ ይህ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ከተለያዩ የመንግሥት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት እና ታዋቂ ግለሰቦች የተሰበሰበ ሲሆን፣ የካቢኔ ወይም የማስተባበሪያ አካላት ውሳኔ ሳይኖር በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ትዕዛዝ ብቻ ወጪ ተደርጓል።
ሪፖርቶቹ እንደሚያሳዩት፣ የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ እነዚህን ወጪዎች እንዲፈጸሙ አድርገዋል ተብሏል፤ ሆኖም ገንዘቡ የት እንደዋለ እና ምን ያህሉ ጥቅም ላይ እንደዋለ ወይም እንደቀረ እስካሁን አይታወቅም።
የክልሉ የካፒታል በጀት እና የፕሮጀክት ምደባ በከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሚገኙ ተገልጿል፤ ምንጮች እንደሚሉት የአጠቃቀም ሂደቱ ሙሉ በሙሉ ግልጽነት የጎደለው እና በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር በጎ ፈቃድ ላይ ብቻ የተመሠረተ ነው።
ይህ የተባለው የተሳሳተ አስተዳደር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በገንዘብ ፍሰት ላይም ተንጸባርቋል፤ 450 ሚሊዮን ብር ለአርባ ምንጭ አንድ ተቋም ቤት እየገነባ ነው በሚል እንደተላከ ተዘግቧል።
በተጨማሪም፣ የክልሉ ዘላቂ ልማት በጀት አጠቃቀም የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ሕግ ያላከበረ እና የተቀመጠውን የበጀት ማከፋፈያ ቀመር ያልተከተለ ነው ተብሏል።
ምንጮች እንደገለጹት፣ ዋናው ነጥብ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ዎላይታ ሶዶን እንደ አስተዳደራዊ እና የፖለቲካ ዋና ከተማ አድርገው አያምኑም፣ በክልሉ ፍትሀዊ የልማት ተደራሽነት እንዳይኖር በማድረግ በክልሉ ከፍተኛ ቅሬታ እየፈጠሩ ስለመሆኑ አስረድተዋል።
በተጨማሪም ህዝቦች አንድ ሆነው እንዳይኖሩ በንቃት እየሠሩ ሲሆን፣ ተቋማትን ወደ አርባ ምንጭ (የትውልድ ቦታቸው) እያዛወሩ ነው ተብሏል።
ሌላኛው የመረጃ ምንጭ ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “አቶ ጥላሁን ከበደ የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ እንጂ በምንም መመዘኛ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፕሬዝዳንት ሊሆኑ አይችሉም። ከፍተኛ የቅንነት ችግር ያለበት፣ እንደ ሰው ያለው እውቀት ለበቀል የሚጠቀም፣ ሌቦችን ለራስ ጥቅም ቁጭ አድርጎ የሚጠቀም፣ ‘የአሁኑን እንጂ የነገን ጉዳይ የማያየው በመሆኑ በክልሉ ኢፍትሃዊነት እንዲነግስ አድርገዋል’ ብሏል።”

ለአብነት ያህል፣ ምንጩ በሕዝቦች መካከል ሰላማዊ ግንኙነቶችን ከመፍጠር ይልቅ ሁሉንም ነገር ወደ አርባ ምንጭ የሚያመራ “ጠባብ እይታ” እንዳላቸው አውግዟል።
ምንጩ በተጨማሪም በዎላይታ እና በብልጽግና ፓርቲ መካከል ጥርጣሬ ፈጥረዋል እንዲሁም ከክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ተቃራኒ ሆነው እንደቆሙ እያስመሰሉ ነው ሲል ከሷል።
ሌላው ትናንት WT ሚዲያ እንደዘገበው፦ ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ጥላሁን ከበደ የክልሉን ቢሮዎች፣ ኤጀንሲዎች፣ ኮሚሽኖች እና የመንግስት ሰራተኞች ጭምር ወርሃዊ ደመወዛቸውን በመቀነስ ለአርባ ምንጭ ስታዲየም ግንባታ ገቢ እንዲያደርጉ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።
ይህ ውሳኔ ፍትሃዊነት የጎደለው እና የስልጣን አላግባብ አጠቃቀም ነው ሲሉ በርካታ አካላት ቅሬታቸውን እያሰሙ ነው።
አቶ ጥላሁን ስታዲየሙን ያለምንም ጨረታ በአርባ ምንጭ ማስጀመራቸው ሲታወስ፣ ከተቋማት በተጨማሪ እያንዳንዱ የክልሉ ሲቪል ሰርቫንትም የወር ደመወዙን በግዴታ እንዲያዋጣ ማስፈራሪያ እንደደረሰባቸው መረጃዎች ያመለክታሉ።
የአቶ ጥላሁን ከበደ አመራር በትውልድ አካባቢያቸው በሆነችው ጋሞ አርባ ምንጭ ከተማ ላይ ብቻ ለማተኮር መቁረጣቸው በክልሉ ውስጥ ውጥረቶችን እየፈጠረ ይገኛል።
ምንም እንኳ ሶዶ ከተማ የክልሉ አስተዳደር መቀመጫ ብትሆንም፣ አቶ ጥላሁን ዋና ዋና የክልል ስብሰባዎችን እና ኢንቨስትመንት መሳብ የሚችሉ መድረኮችን ሙሉ በሙሉ ወደ ትውልድ አካባቢያቸው እያዘዋወሩ ይገኛሉ።
በተጨማሪም፣ በዎላይታ፣ በጌዲኦ፣ በጎፋ እና በሌሎች ብሔሮች ላይ ልማት እንዳይሰራ በማድረግ የራሳቸውን አንድ ብሔር ላይ ብቻ ልማት እየሠሩ ነው የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።
ከዚህ ቀደምም ርዕሰ መስተዳድሩ ያለ ካቢኔ ውሳኔ ለአርባ ምንጭ ስታዲየም ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲሁም ለብሔር ብሔረሰቦች ቀን ለማክበር ተብሎ ለአርባ ምንጭ አስፋልት ለመሥራት ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ መሰጠቱ ተዘግቧል።
ለክልሉ የሚመጣ ኢንቨስትመንት በሙሉ ወደ አርባ ምንጭ ብቻ በግድ እንዲሄድ ሲደረግ፣ ባለሀብቶች ወደዚያ መሄድ ካልፈለጉ የኢንቨስትመንት ፈቃድ እንደማይሰጣቸው ታውቋል።
ይህ ሁሉ ግፍ በክልሉ እየተፈጸመ እያለ ከርዕሰ መስተዳድሩ ውጪ ሁሉም አስተባባሪዎችና የካቢኔ አባላት በጉዳዩ ዙሪያ ዝምታ መምረጣቸው አሳሳቢ ሆኗል።
የውስጥ አዋቂዎች ከስፍራው ያደረሱት መረጃ ደግሞ እስካሁን በስታዲየም ግንባታ ስም ከአሰራር ውጪ የወጣው በቢሊዮን የሚቆጠር ከፍተኛ ገንዘብ በጥቅም ለተሳሰሩ ግለሰቦች እጅ እየገባ ነው፣ ከፍተኛ ማጭበርበር አየተከናወነ ነው” ሲል አስረድተዋል።
አሁን በደረሰን መረጃ ደግሞ ለስታዲየሙ ግንባታ በክልሉ የሚገኙ ከሁሉም የመንግስት ሰራተኞች፣ ባለሀብቶች በግዴታ መዋጮ እንዲያደርጉ ከማስገደድ ባለፈ በመጪው ዕሁድ በአርባ ምንጭ ከተማ ሁሉም የክልሉ የየዞን አመራሮችና ባለሀብቶች ጨምረው በግዴታ መዋጮ እንዲያደርጉ ርዕሰ መስተዳድሩ የእራት ግብዣ አለ በሚል በደብዳቤ ቀጭን ትዕዛዝ አሰራጭተዋል።
የመረጃ ምንጮቹ እንደገለፁት፣ “እኛ ልማት እዛ ለምን ይሰራል ሳይሆን ከ32 በላይ ብሔር ብሔረሰቦች ያሉበት ክልል ላይ ርዕሰ መስተዳድሩ ኃላፊነትን በመተው ለትውልድ አከባቢው ብቻ በማድላት ተጨባጭ ኢፍትሃዊ ተግባር ላይ መሰማራታቸውን ሁሉም እንዲያውቁ ስለተፈለገ ነው” ብለዋል።