በጋሞ ዞን በዛይሴ ብሔረሰብ ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና ጥቃቶች ተባብሰዋል
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጋሞ ዞን በሚኖረው የዛይሴ ብሔረሰብ ላይ ከግንቦት 3 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ እየተፈጸመ ያለው ተደጋጋሚ ጥቃትና የሰብዓዊ መብት ጥሰት እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የብሔረሰቡ ተወላጆችና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዛይሴ ሕዝብ ተወካይ አቶ አብርሃም አሞሼ ገልጸዋል።

ባለፉት ጥቂት ቀናት ብቻ 12 ሰዎች ሲገደሉ፣ በርካታ አብያተ ክርስቲያናትና የመኖሪያ ቤቶች በእሳት መጋየታቸው ታውቋል።
በተለይም ከግንቦት 3 ቀን 2017 ዓ/ም ጀምሮ የጋሞ ዞን መዋቅር አመራሮች አስተባብረውታል በተባለው በዚህ ጥቃት 98 ቤቶች ሙሉ በሙሉ ወድመዋል።
ከሳምንት በፊት የወጡ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት፣ በቅርቡ በተፈጸመው የበቀል እርምጃ ከ15 በላይ ሰዎች ሲገደሉ፣ ከ18 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ከባድና ቀላል ጉዳት ደርሶባቸዋል።
በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከአካባቢያቸው ተሰደዋል፤ የግለሰቦች ቤት መቃጠሉ፣ ንብረት መዘረፉ እንዲሁም በርካታ ሰዎች በአርባምንጭ ዙሪያ ፖሊስ ጣቢያና ወደ ሌሎች ያልታወቁ ቦታዎች ተወስደው መታሰራቸው ተነግሯል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ አብርሃም አሞሼ ለWT ሚዲያ እንደገለጹት፣ “ሕገወጥ ታጣቂዎች (ልዩ ኃይል/አድማ በታኝ) እና የጋሞ ዞን መደበኛ ፖሊሶች በዛይሴ ነዋሪዎች ላይ ግድያ እየፈጸሙ፣ ንብረቶቻቸውን እየዘረፉ፣ በቤተክርስቲያን ውስጥ በመግባት ጭምር ሰብዓዊ መብት እየጣሱ፣ በሙሉ በእሳት እያወደሙ ነው” ብለዋል።
አቶ አብርሃም አሞሼ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ የሆኑት አቶ ታገሰ ጫፎ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ እና የጋሞ ዞን አመራሮች በዛይሴ ብሔረሰብ ላይ እየደረሰ ያለውን የኃይል እርምጃ ሽፋን እየሰጡ እንደሆነም አስረድተዋል።
የሕዝብ ተወካዩ አቶ አብርሃም ባቀረቡት መረጃ፣ በዛይሴ ሕዝብ ላይ ያልተቋረጠ ዘግናኝ የዘር ማጥፋት ዘመቻ እየተካሄደ ነው ብለዋል።
አዲሱ ክልል ከተመሰረተ ጀምሮ ከ25 በላይ ንጹሃን ዜጎች በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ትዕዛዝ ሕይወታቸውን እንዳጡ፣ በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው፣ ሰብዓዊ መብታቸው ተጥሶ እንደታሰሩ እንዲሁም ከአካባቢያቸው እንደተሰደዱ ጠቁመዋል።
አንድ ስሙን መግለጽ ያልፈለገ የአካባቢው ነዋሪ ለWT ሚዲያ በሰጠው መግለጫ፣ አቶ ታገሰ ጫፎ ከዚህ ቀደምም በ2017 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ የዛይሴ ሕዝብ ተወካይ የነበሩት አቶ አብርሃም አሞሼ የሕዝቡን ጭቆና ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ሲያቀርቡ፣ ድምጹን ለማፈን ሞክረዋል በሚል ወንጅለዋል።
አክለውም፣ “የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ብልሹ አሠራሮችን ሲፈጽሙ እና ሲያስፈጽሙ በቸልተኝነት በመመልከት፣ ይህ ድብቅ ሥራ እንዳይጋለጥ እና ፌዴራል መንግሥት በሕግ እንዳይጠይቃቸው አቶ ታገሰ ጫፎ ከላይ ሆነው እየሰሩበት ያለው ሥራ አሁን ላይ ይፋ መውጣት ጀምሯል” ብለዋል።
ከጥቂት ወራት በፊት የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ በተገኙበት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ብልሹ አሠራሮች ዙሪያ ለሦስት ቀናት በዎላይታ ሶዶ ውይይት ተካሂዶ እንደነበር በማስታወስ፣ በወቅቱ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር በበርካታ የብልሹ አሠራር ነጥቦች ተይዘው እንደነበርና ከሥራቸው ይታገዳሉ ተብሎ ሲጠበቅ፣ አቶ ታገሰ ጫፎ ሽፋን በመስጠት ዳግም ዕድል እንዲያገኙ ማድረጋቸው በአካባቢው እስካሁን ድረስ ችግሩ እንዲቀጥል ማድረጉን አስተያየት ሰጪው ጠቁመዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎች የሚመለከታቸው አካላት በእነዚህ ክስተቶች ላይ በአስቸኳይ ምርመራ እንዲያደርጉና እየደረሰ ያለውን ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲያስቆም ጥሪ እያቀረቡ ነው።
በተጨማሪም፣ የዛይሴ ብሔረሰብ የራሱን የአስተዳደር መዋቅር ለማግኘት ባቀረበው ሕጋዊ ጥያቄ ሽፋን የጋሞ አመራሮች እየፈጸሙት ነው ያሉትን በደል እንዲቆም ተማጽነዋል።
ሌላኛው ስሙን እንዳይጠቀስ የፈለገ የአካባቢው ነዋሪ ለWT ሚዲያ እንደገለጸው፣ የችግሩ መነሻ በአካባቢው የቆየው የዛይሴ ብሔረሰብ የመዋቅር ጥያቄ ጋር የተያያዘ ነው።
መንግሥት በተደጋጋሚ የሚከሰቱ ግጭቶችን በዘላቂነት እንዲያስቆምና ተጠያቂነትን እንዲያሰፋ በመግለጽ፣ ሰላማዊ ዜጎች ጉዳት እንዳይደርስባቸው ጥሪ አቅርቧል።
አንድ የአካባቢው ነዋሪ ለWT ሚዲያ በሰጡት ቃል፣ “ሕዝቡ በአሁኑ ወቅት እጅግ አስከፊ በሆነ የረሃብና ፍርሃት ውስጥ እንደሚገኝ ገልፀው ይህ ሁኔታ የተፈጠረው በጸጥታ ኃይሎች እየተወሰደ ባለው የኃይል እርምጃ ምክንያት ነው።
አሁንም ሰው ማሳ ውስጥ እንዳይገባ ተከልክሎ የገቡትም እየተገደሉ ናቸው፣ ብዙዎቹ የተገደሉትን ቤተሰብ ለማንሳትና ገብቶ ለመፈለግም ተከልክሎ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው” ብለዋል።
በተለይም አሁን የጤፍ መሰብሰቢያ ጊዜ በመሆኑ፣ ማሳ መግባት መከልከሉ ባለቤቶቹ ንብረታቸውን ሙሉ በሙሉ እንዲያጡ እያደረጋቸው ነው። ከዚህ የከፋው ደግሞ ማሽላ የሚጠብቁትንም ሰዎች ከማማ ላይ እየገደሉ በመሆኑ፣ ማሽላውም በወፍ እየተበላ እንደሆነ ገልጸዋል።
ይህ ሁኔታ ሕዝቡ የዕለት ጉርስ ምንጩን እንዳያገኝ በማድረግ ለከፋ ረሃብ እየዳረገው ነው። ነዋሪው አክለውም፣ “ሰው አሁን ግማሹ ተሰደው ወደ አጎራባች ቀበሌዎች የቀሩት ማንም ወደ ማሳ እንዳይገባ ተብለው እንደ አርሶአደር አኗኗር ሰው የየዕለቱን አስቤዛ ከማሳ ነበር የሚያመጣው አሁን ግን ቁጭ ብሎ በረሃብ እየተሰቃዩ ነው ያሉት” ብለዋል።
አስተያየት ሰጪዎቹ በመጨረሻም፣ “እየተወሰደ ያለው የበቀል እርምጃ በግልጽ የዘር ማጥፋት ወንጀል ድርጊት ስለሆነ የኢትዮጵያ ሚዲያዎች፣ የሰብዓዊ መብት ተቋማት እንዲሁም የሚመለከታቸው የፌዴራል መንግስት በ21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ በማንነታቸው ምክንያት እየደረሰ ያለውን የንጹሃን ዜጎች ግድያ፣ እስር፣ ስደትና ቤትና ንብረት በእሳት ማውደም አሳዛኝ ድርጊት እንዲያስቆምል በፈጣሪ ስም እንማፀናለን” ብለዋል።
ፌዴራል መንግሥት በአስቸኳይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጣልቃ በመግባት ለብሔረሰቦቹ መብት ማስከበር እንዳለበት እና በግለሰቦቹ ላይ ፖለቲካዊ እርምጃ መውሰድ እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል።