ይሄንን የመፍትሔ ሀሳብ ልማት ለተጠማ ህዝብ የሚያስፈፅም ማነው?
ዳልቦን በከተማነት የማልማት አስፈላጊነትና ምክንያቶቹ
የዳልቦ ታሪካዊ ጠቀሜታ እና ስትራቴጂካዊ አቀማመጥ ወደ በለፀገ የከተማ ማዕከልነት እንድታድግ የሚያስገድድ ጠንካራ መከራከሪያ ያቀርባል። ይህ ለውጥ የቀድሞ ታሪኳን ከማክበር ባለፈ ለሰፊው የዎላይታና አከባቢው ጭምር ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊና መሠረተ ልማታዊ ጥቅሞችን እንደሚያስገኝ የWT ሚዲያ ተጋባዥ ጸሓፊ የሆኑት ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና በጥልቀት ያብራራሉ።

1. ዳልቦ: የቀድሞዋ የዎላይታ ዋና ከተማ
ዳልቦ ለዘመናት የዎላይታ መንግሥት መቀመጫ በመሆን በዎላይታ ታሪክ ውስጥ ጥልቅ ስፍራ አላት። የታሪክ ድርሳናት እንደሚያሳዩት ከምኒልክ ወረራ በፊትም ዳልቦ ቤተመንግሥት ስልክ ጭምር የነበራት ሲሆን ይህም በአፍሪካ ደረጃ የሥልጣኔ ምልክት እንደነበረች ያሳያል።
በ1894 ዓ/ም ዳልቦ ቤተመንግሥት ስልክ ነበረ፤ ዳልቦ ገበያ የዎላይታ ህዝብ በራሱ የመገበያያ ገንዘብ በማርጯ ይገበያይ ነበር፡፡ ዳልቦን በከተማነት ማልማት የዎላይታን ጥንታዊ ሥልጣኔ የሚያሳይ ታሪካዊ ሙዚየም ለመገንባትና የተለያዩ የመታሰቢያ ቦታዎችን ለመመሥረት ልዩ ዕድል ይፈጥራል።
2. በዎላይታ ሶዶና በቦዲቲ ከተሞች መሃል መገኘቷ
ዳልቦ በአሁኑ ሰዓት የክልል መቀመጫ ከሆነችዉ ተስፋ ያላት የዎላይታ ሶዶ ከተማና በአዲስ አበባ መንገድ ላይ አስደናቂ እድገት እያስመዘገበች ካለቺዉ ቦዲቲ ከተማ መሃል ላይ መገኘቷ ትልቅ እምቅ አቅም አላት። ይህ አቀማመጥ በተለይ ሁለቱን ወሳኝ ከተሞች በተለያዩ ዘርፎች ለማገናኘትና ለማስተሳሰር ትልቅ ጥቅም ይሰጣል።
ዳልቦ የሁለቱንም ከተሞች የተቀናጀ ዕድገት ለማስፋፋት ቁልፍ ሚና መጫወት ትችላለች፤ ለምሳሌም ሁለቱን ከተሞች የሚያቋርጠዉን የፌዴራል መንገድ የከተሞቹን ደረጃ በሚመጥን መልኩ እንዲሰራ ለማስቻል ጠቃሚ ነች።
3. በአራት በኩል በአስፋልት የተሰራ መግቢያና መውጫ ያላት መሆኗ
ዳልቦ በአሁኑ ወቅት በአራት አቅጣጫዎች በአስፋልት የተሸፈኑ መግቢያና መውጫዎች አሏት። እነዚህም ከቦዲቲ በዳልቦ ገብርኤል አልፎ ወደ ዎላይታ ሶዶ በሌዊ ሪዞርት የሚያስገባዉ መንገድ፤ ከባዴሳ በኩል በማዮ ማዞሪያ የሚገባዉ መንገድ፤ እንዲሁም ከኦቶና በኩል ከዎላይታ ሶዶ ጋር የሚያገናኛት መንገድ ናቸው።
ከዚህም በተጨማሪ የዳልቦን ገበያ ፊት ለፊት የሚያልፍ ከማዮ ማዞርያ እስከ ቦዲቲንና ዎላይታ ሶዶን ከሚያገናኘዉ የአዲስ አበባ መንገድ ጋር የሚገናኝ በጥሩ ሁኔታ የተሠራ የተወሰኑ ኪሎ ሜትሮችን የሚረዝም አስፋልት አላት። ይህ ያለው ጠንካራ መሠረተ ልማት ለቀጣይ የልማት ተነሳሽነቶች ትልቅ መሠረትና ማነቃቂያ ነው።
4. የመሬት አቀማመጧ ሜዳማነት
በዳሞታ ግርጌ የምትገኘዉ ዳልቦ በአብዛኛው የመሬት አቀማመጧ ሜዳማ በመሆኑ ብዙ ትልልቅ ተቋማትን፣ ፋብሪካዎችንና የመኖሪያ መንደሮችን በቀላሉ ለመገንባት አመቺ ያደርጋታል። ይህንን ጥቅም ለመጠቀም ለዳልቦ ጥሩ የከተማ ፕላን ማዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑ አያጠያይቅም። በተለይ ሰፋፊ መሬት የሚያስፈልጋቸዉ ተቋማት በዳልቦ ቢቋቋሙ፣ ሪል እስቴትና የጋራ መኖሪያ ቤቶች ቢሰሩባት በጣም አመቺ ነች።
5. ከአረካና ከአየር ማረፊያው ጋር ዎላይታ ሶዶንና ቦዲቲን በአጭሩ ለማገናኘት አማካይ ቦታ የመሆን እድሏ
ቀጥተኛ መንገድ ባይኖርም ካርታ ላይ ስናየዉ ከዎላይታ ሶዶ ወደ አረካ ካለዉ ርቀት፣ ከአረካ ወደ ቦዲቲ ያለዉ ርቀት በእጅጉ ያንሳል። አረካና ቦዲቲን ቀጥተኛ መንገድ ሰርቶ ማገናኘት በጣም ወሳኝና ጠቃሚ መሆኑ መታወቅ አለበት።
መንገዱ ወጭዉ በዝቶም ቢሆን አፈርን በመቁረጥና ድልድዮችንም በመገንባት እዉን ቢደረግ ለዎላይታ ትልቅ ጥቅም ያመጣል። አሁን ከዎላይታ ሶዶ ወደ አረካ የሚወስደዉ መንገድ ወደፊት በዳልቦ በኩል በአቋራጭ ቢሰራ መንገዱን ያሳጥራል። ዎላይታ ሶዶ፣ አረካና ቦዲቲ ተያይዘውና ተሳስረው ማደጋቸዉ ለመላዉ የዎላይታ ሕዝብ ወሳኝና ቁልፍ ነው፤ ትልቅ የከተማ አማራጭም ናቸው።

አሁን በአንድ ጊዜ ይህን ሁሉ በአስፋልት ደረጃ ለመሥራት አቅም ሊያጥር እንደሚችል ይታወቃል። ነገር ግን ማቀድና ማጥናት፣ እንዲሁም መንገዶችን በደረጃ መገንባት አሁን ላይ ከዞኑ አቅም በላይ አይደለም።
በተለይ አሁን ላይ የክልል መቀመጫ የሆነችው ዎላይታ ሶዶ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ኩነቶችን የማስተናገድ እድሎች ወደፊት በስፋት ስለሚኖሯት የአረካና ቦዲቲ ከተሞች በብዙ መልኩ የዎላይታ ሶዶ ከተማን ሊደግፉ የሚችሉበት አግባብ መኖሩ መታወቅ አለበት።
የዎላይታ ሶዶ አቅምና ደረጃ ሲታሰብ በተለይ በጥሩ የእድገት ደረጃ ላይ የሚገኙትን አረካና ቦዲቲን አካቶ ማሰብ ይገባል። ከተወሰኑ እንግዶችን ከማስተናገድ ጀምሮ፣ በተለይ ልማትን ተቀናጅተዉ በጋራ ከሰሩ ትልቅ አቅም መፍጠር ይችላሉ።
ማሳሰቢያ: በልማት ስም የአርሶ አደሩን መሬት ወስደው በበቂ ሁኔታ መቋቋሚያ ሳያዘጋጁ ሜዳ ላይ መበተንና ባለይዞታዎች በድህነት እንዲታወቁ ማድረግ ተቀባይነት የለውም።
የWT ሚዲያ ሁልጊዜ በህብረተሰቡ ውስጥ ነው🙏