የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፕሬዝዳንት በአርባምንጭ ቤተመንግሥት ሊገነቡ እንደሆነ ተገልጿል።
በሌላ በኩል፣ በክልሉ እየተባባሰ የመጣውን ኢፍትሐዊነት እና አድሏዊ አሰራሮች ተቃውሞ ለማርገብ በሰኔ 23 እና 24 ክልል አቀፍ እርቅ መድረክ ለማካሄድ ኮሚቴ መዋቀሩንም የ WT ሚዲያ ምንጮች አረጋግጧል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ጥላሁን ከበደ በአርባምንጭ ከተማ ቤተመንግሥት ለመገንባት እንቅስቃሴ መጀመራቸው ተነግሯል፡፡
ይህ እርምጃ በክልሉ እየተባባሰ ከመጣው የፍትሕ መጓደልና አድሏዊ አሰራር ጋር በተያያዘ ከባድ ቅሬታዎችን እያነሳ ነው።
WT ሚዲያ የፕሬዝዳንቱን የቤተመንግሥት ግንባታን ጨምሮ በርካታ አሳሳቢ ጉዳዮችን መረጃዎች ደርሷል።
ሪፖርቱ እንደሚያመለክተው፣ አቶ ጥላሁን ከበደ በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ አከባቢ የፕሬዝዳንት ቤተመንግሥት ለመገንባት መሬት የተረከቡ ሲሆን፣ ግንባታ ለማስጀመር ከክልሉ በጀት የክልሉ አስተባባሪዎች ውሳኔ ሳይኖር 87 ሚሊዮን ብር ወጪ ማድረጋቸው ተሰምቷል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር መቀመጫ የዎላይታ ሶዶ ከተማ ብትሆንም፣ አቶ ጥላሁን ከበደ የቢሮ ግንባታ መጀመር ይቅርና የክልሉን ህገመንግስት ጭምር ከህዝብ ደብቀው ማስቀመጣቸው የበርካቶችን ጥያቄ አጭሯል።
ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ለአዲስ አበባ የሚሰጥ ቤት የታደሰና ለኑሮ ምቹ ቢሆንም፣ ርዕሰ መስተዳድሩ ከክልሉ በጀት 28 ሚሊዮን ብር ተጨማሪ ወጪ አድርገዋል፤ እንዲሁም 9 ሚሊዮን ብር የመሬት ግዢን ጨምሮ በአጠቃላይ 37 ሚሊዮን ብር ያለ ካቢኔ ውሳኔ በግለሰብ ትዕዛዝ ብቻ ወጪ ማድረጋቸው ተመላክቷል።
በተጨማሪም የአቶ ጥላሁን ከበደ አመራር በራሳቸው የትውልድ አካባቢ በሆነችው ጋሞ አርባምንጭ ከተማ ላይ ብቻ ለማተኮር መቁረጣቸው በክልሉ ውስጥ ተጨማሪ ውጥረቶችን እየፈጠረ ነው።
ምንም እንኳ ሶዶ ከተማ የክልሉ አስተዳደር መቀመጫ ብትሆንም፣ አቶ ጥላሁን ዋና ዋና የክልል ስብሰባዎችን እና ኢንቨስትመንት መሳብ የሚችሉ መድረኮችን ሙሉ በሙሉ ወደ ትውልድ አካባቢያቸው እያዘዋወሩ ይገኛሉ።
በተጨማሪም፣ በዎላይታ፣ በጌዲኦ፣ በጎፋ እና በሌሎች ብሔሮች ላይ ልማት እንዳይሰራ በማድረግ የራሳቸውን አንድ ብሔር ላይ ብቻ ልማት እየሰሩ ነው የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።
ከዚህ ቀደምም ርዕሰ መስተዳድሩ ያለ ካቢኔ ውሳኔ ለአርባምንጭ ስታዲየም ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲሁም ለብሔር ብሔረሰቦች ቀን ለማክበር ተብሎ ለአርባምንጭ አስፋልት ለመስራት ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ መሰጠቱ ተዘግቧል።
ለክልሉ የሚመጣ ኢንቨስትመንት በሙሉ ወደ አርባምንጭ ብቻ በግድ እንዲሄድ ሲደረግ፣ ባለሀብቶች ወደዚያ መሄድ ካልፈለጉ የኢንቨስትመንት ፈቃድ እንደማይሰጣቸው ታውቋል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፖለቲካ ውስጥ አነጋጋሪ ጉዳይ የሆነው የአመራሮች እርስበርስ የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ በርካታ ግምቶችንና ጥያቄዎችን እያጫረ ነው።
ይህ ዘመቻ ከጀርባው የሙስና፣ የኮንትሮባንድ ንግድ እና የፖለቲካ ፍላጎቶች እንዳሉ ይታመናል ሲል ከጥልቅ ማጣራት የተገኘ መረጃ ያመለክታል።
እነዚህ አካላት የሙስና ሰንሰለታቸውን ሊበጥስ ይችላል ብለው በሚሰጉት ላይ ዘመቻውን ጀምረዋል፤ እንዲሁም የኮንትሮባንድ ነጋዴዎች ጥብቅ ቁጥጥር በመፍራት ዘመቻው ውስጥ እጃቸው አለበት ተብሏል።
በደቡብ ኢትዮጵያ በከፍተኛ ሌብነት የተጠረጠሩት ላይ የሚወሰደው ፖለቲካዊ፣ አስተዳደራዊ እና ህጋዊ እርምጃ ዝግጅት ተጠናቆ በቀናት ጊዜ ወደ ተግባር የሚገባ በመሆኑ፣ ይህን ትኩረት ለማስቀየር ዘመቻው መጀመሩን ከፌዴራል ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በያለንበት ዘውትር ኢፍትሃዊነትን ታግለን ፍትሀዊ የሆነች ኢትዮጵያን ለመገንባት ሁላችንም እንታገል!!