GridArt_20250713_181510129

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፕሬዘዳንት የመጨረሻውን ተልዕኮ ተግባራዊ ለማድረግ ምቹ ሁኔታ ያጡት የእንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ ጉዳይ የበርካቶችን ትኩረት መሳቡ ተገለፀ።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፕረዚዳንት አቶ ጥላሁን ከበደ በስልጣን ዘመናቸው የመጨረሻው ተልዕኮ የሆነውን የእንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ በትውልድ አካባቢያቸው እንዲሆን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ሁለት ቢሮዎች ተቀንሰው በአንድ እንዲደራጅ ለማድረግ ቅድመ ሁኔታውን መጨረሳቸውን ለWT ሚዲያ የደረሰው መረጃ ያመለክታል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ለዚሁ አላማቸው ምቹ ሁኔታ ለመፈጠር ያለመ ነው የተባለለት አሁን ላይ በቢሮ ደረጃ የሚገኙትን፦ ንግድ ቢሮ እና እንዱስትሪ ቢሮ ወደ ንግድና እንዱስትሪ ቢሮ በሚል በማዋቀር የአመራር ለውጥ ለማድረግ የሚያስችላቸውን ከሁለት ቀናት በፊት በተካሄደው የክልሉ ካቢኔ ስብሰባ ላይ ይፋ ማድረጋቸው ታውቋል።

በዚሁ አዲስ አወቃቀር ላይ በርካታ ከዚህ በፊት የነበሩ የክልሉ መስሪያ ቤቶች ከሌሎች ጋር የሚዋሃዱበት እንዲሁም አዲስ መዋቅር የተጨመረበት እንደሆነ WT ሚዲያ ከደረሰው ዝርዝር ሰነድ ተመልክቷል።

WT ሚዲያ በዚሁ ከዚህ በፊት የነበሩ የክልሉ መስሪያ ቤቶች ከሌሎች ጋር የሚዋሃዱበት እንዲሁም አዲስ መዋቅር የተጨመረበት ስነድ በተመለከተ በቀጣይ ዘገባ በጥልቀት የሚዳስስ ሲሆን በዛሬው ዕለት የፕሬዘዳንቱ የመጨረሻው ተልዕኮ እና ተግባራዊ ለማድረግ ምቹ ሁኔታ ያጡት የእንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ ጉዳይ በተመለከተ ከተለያዩ ምንጮች ያገኘውን መረጃ መሠረት በማድረግ እናቀርባለን።

እንደ ታማኝ መረጃ ምንጭ ከሆነ በፌደራል መንግስት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እንዲገነባ የቦታ መረጣ ተጠይቆ የነበረው የእንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ ጉዳይ የት ደረሰ የሚያውቅ የሌለ ሲሆን ሰሞኑን በተካሄደው በክልሉ ካቢኔ ስብሰባ ላይም ጉዳዩ አለመነሳቱ ተገልጿል።

እኚሁ የመረጃ ምንጫችን እንዳስረዱት “በፌደራል መንግስት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እንዲገነባ የቦታ መረጣ ተጠይቆ የነበረው የእንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ ጉዳይ በፕሬዚዳንቱ ምስጥር እንዲሆን የተፈለገበት ከዚህ በፊት እያደረጉት ያሉት አይነት ለእኔ ብቻ አይነት አስተሳሰብ ተግባራዊ ለማድረግ ያለመ ነው” ብለዋል።

ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ይሄንን ተግባራዊ ለማድረግ ምቹ ሁኔታ በማጣት እንደቆዩ በማስረዳት አሁን ላይ የመጨረሻ ሙከራ ያላቸውን ሁለት ተቋማትን በማዋሃድ ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለ የሚገኘውን የእንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ የሆኑትን ዶክተር ቦጋለ ቦሼን ወደ ሌላ ቢሮ በመውሰድ እንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ በትውልድ አካባቢያቸው ለማድረግ ያለሙትን ለማሳካት እንቅስቃሴ ጀምሯል” በማለት አስረድተዋል።

በተጨማሪም “በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በተለይም የዎላይታ ህዝብ ማህበራዊ፣ ፓለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ከየትኛውም ሀገራቱ ክፍል የተለየ መልክ ያለው ነው። በዎላይታ ሌሎች ስራአጥ ወጣቶችን ሳንቆጥር ከመንግሥት ዩንቨርስቲ ከዲግሪ የተመረቁ ከ200 ሺህ በላይ የተማሩ ስራአጥ ወጣቶች ስለመኖራቸው በቅርቡ በተደረገው ዳሰሳ ጥናት መረጋገጡን በማስረዳት ይሄም ርዕሰ መስተዳድር ለእኔ ብቻ እንጂ ለሌሎች ደንታ እንደሌላቸው ያሳያል” ብለዋል።

አስተያየት ሰጪው አክለውም “በሀገሪቱ ከተሞች በየጎዳናው በአባታቸው በእናታቸው አቅፍ ሆነው ማደግና መማር የሚገባቸው ህፃናት፣ ወጣቶችና ሴቶች በአከባቢው ምንም የስራ ዕድል ባለመፈጠሩ በስደት እንዲሁም በተስፋ መቁረጥ ላይ ናቸው። ይሄ ሁሉ የህዝብ ችግር በአደባባይ እየታወቀ በአቶ ጥላሁን ከበደ ኢፍትሐዊ አሰራር በአከባቢው ግፍ እየተሰራ ነው” ብለዋል።

ለመሆኑ ከአመት በፊት በፌደራል መንግስት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እንዲገነባ የቦታ መረጣ ተጠይቆ የነበረው የእንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ ጉዳይ የት ደረሰ? የሚለው አነጋጋሪነቱ ቀጥሏል።

እስካሁን ባለን መረጃ የፌደራል መንግስት በክልሉ እንዱስትሪ ፓርክ ለመገንባት ክልሉን የጠየቀው በክልሉ ካብኔ አለመቅረቡን አረጋግጠናል።

ከዚህ በፊት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከ3 ወራት በላይ ተሰርቆ ተደብቀው የነበረው የኢምግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ቅርንጫፍ ደብዳቤ ደብዳቤ ከተደበቀበት መውጣቱ ይታወሳል።

በመንግሥት አመራሮች ግልፀኝነት በጎደለው አኳኋን መረጃ ለወራት በመደበቅ ይፋ አለማድረግ ለሚመሩት ህዝብ ካለመታመን ባሻገር መሠል በርካታ ጉዳዮች በድብቅ እየተሰራ እንደሆነ ግልጽ ማሳያ እንደሆነ ያረጋግጣል በሚል በርካቶች ይገልፃሉ።

ክልሉ 32 ብሄረሰቦችን ያቀፈ ቢሆንም፣ የልማት ትኩረቱ በአንድ አካባቢ ላይ ማተኮሩ በሌሎች የክልሉ ከተሞች እና ብሄረሰቦች ዘንድ የመገለል ስሜት እንደፈጠረ እየተነገረ ነው።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ በፌዴራል መንግስት በጀት አማካኝነት በራሳቸው የትውልድ አካባቢያቸው ብቻ በርካታ ትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶችን በማስገንባት ላይ መሆናቸው በክልሉ ውስጥ ቅሬታዎችን ማስነሳቱ ይታወቃል።