በሲዳማ ክልል የሀዋሳ ዙሪያ ወረዳ ነዋሪዎች ለተቃውሞ አደባባይ ወጡ።
ነዋሪዎቹ አደባባይ የወጡት በወረዳው አስተዳደር ሥር የሚገኙ አምስት ቀበሌያት ወደ ሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ሊካለሉ ነው መባሉን በመቃወም ነው።
ነዋሪዎቹ በወረዳው የአስተዳደር መቀመጫ ዶሬ ባፈኖ ከተማ ባካሄዱት ትዕይንተ ህዝብ፤ የክልሉ መንግሥት የወሰደው እርምጃ ከአራት ዓመታት በፊት ለነዋሪው የተገባውን ቃል የሚጻረር ነው በማለት ድምጻቸውን አሰምተዋል።
ቀደምሲል በወረዳው የሚገኙ ሃያ ሦስት ቀበሌያት እና ሁለት ከተሞች በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ሥር ገብተው በአንድ ክፍለ ከተማ እንደሚደራጁ ቃል ተገብቶላቸው እንደነበር ሠልፈኞቹ ጠቅሰዋል።
ይሁን እንጂ አሁን ላይ አምስት ቀበሌያትን ብቻ በመነጠል ወደ ከተማው መዋቅር ለማስገባት የተጀመረውን ሂደት ለመቃውም አደባባይ መውጣታቸውን ከሠልፉ አስተባባሪዎች አንዱ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት ሃምሳ አባላት ያሉት የወረዳው ማህበረሰብ ተወካዮች ተመልምለው ከክልሉ የሥራ ሃላፊዎች ጋር ለመጋገር ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙ አስተባባሪው ተናግረዋል።
በሲዳማ ክልል ሰሜን ሲዳማ ዞን የሚገኘው የሀዋሳ ዙሪያ ወረዳ ከርዕሰ ከተማ ሀዋሳ በ17 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል።
ወረዳው ሰሜናዊ የሀዋሳ ሐይቅን ተጎራብቶ የተመሠረተ ወረዳ እንደሆነም ይታወቃል።
ዶቼቬሌ ሠልፉን አስመልክቶ የሀዋሳ ዙሪያ ወረዳውንም ሆነ የሰሜን ሲዳማ ዞን አስተዳደር የሥራ ሃላፊዎችን ለማነጋገር ጥረት ቢያደርግም ምላሽ የሚሰጠጥ አልተገኘም ብሏል።