የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አወዛጋቢው የካቢኔ ውሳኔዎች፣ የመዋቅር ብተና፣ የሥልጣን ሽኩቻ እና የግልፀኝነት ማጣት መቀጠሉ ተገለፀ።
WT ሚዲያ፦ በቅርቡ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በተካሄደው መደበኛ የካቢኔዎች ስብሰባ ላይ በርካታ አወዛጋቢ ውሳኔዎች መተላለፋቸውን WT ሚዲያ ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች አረጋግጧል።
እነዚህ ውሳኔዎች የአንዳንድ ቢሮዎችን መበተን፣ መደባለቅና ከደረጃ ዝቅ ማድረግን የሚያካትቱ ሲሆን፣ ከክልሉ ሙሁራን ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታ እያስነሱ ነው።
ከሁለት ቀናት በፊት በWT ሚዲያ የወጣ ዘገባ ደግሞ እነዚህ ውሳኔዎች ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ የኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታን በትውልድ አካባቢያቸው ለማስገንባት ካላቸው ፍላጎት ጋር የተያያዘ እንደሆነ ያመላክታል።
የካቢኔው ውሳኔ መሰረት የሚከተሉት ቢሮዎች እንዲታጠፉ ተወስኗል፦ ኢንዱስትሪ ቢሮ፣ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ፣ ሰራተኛና ማህበራዊ ቢሮ፣ ደንና አካባቢ ጥበቃ ቢሮ፣ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ እና ቴክኒክና ሙያ ቢሮ ይገኝበታል።
በተጨማሪም የፐብሊክና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ከደረጃ ዝቅ እንዲሉ ተደርጓል።
ለርዕሰ መስተዳድሩ ተጠሪ የሆኑ ተቋማትም ተፈጥረዋል፦ ከውሃና ማዕድን ቢሮ ወጥቶ ማዕድን ዘርፍ ብቻውን ኤጀንሲ እንዲሆን፣ የወጣቶች ዘርፍ ከስፖርት ቢሮ ወጥቶ ኮሚሽን ሆኖ ለፕሬዝዳንቱ ተጠሪ እንዲሆን እንዲሁም የአካባቢ ጥበቃ ቢሮም ለፕሬዝዳንቱ ተጠሪ እንዲሆን ተወስኗል።
እነዚህ ቢሮዎች መታጠፍ ወጪን ከመቆጠብና አላስፈላጊ ብክነትን ለመቀነስ ክልሉ የወሰደው እርምጃ ተገቢ ቢሆንም፣ ከወዲሁ ከፍተኛ ቅሬታ እና ስጋት ከሙሁራን ዘንድ እየተሰማ መሆኑን WT ሚዲያ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
በተለይም የክልሉ የቢሮ ክፍፍል እና የሹመት አመዳደብ ከፍተኛ የፍትሃዊነት ችግር እንዳለ እየታወቀ፣ አብዛኛውን ቢሮ በአርባምንጭ ክላስተር ማድረጉ ከፍተኛ የፍትሃዊነት ጥያቄዎችን እያስነሳ ይገኛል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል 32 ብሔረሰቦችን ያቀፈ ቢሆንም፣ በአርባምንጭ ክላስተር የብሔር ስብጥሩን በሚገፋ መልኩ ሰራተኛውን በአንድ ብሔር ማደራጀቱ ክልሉ የአለመረጋጋትና የፖለቲካ ትኩሳት መነሻ ሆኖ ዘልቋል።
አሁንም ቢሆን ወደ አርባምንጭ ክላስተር ቢሮዎችን እጅግ በረቀቀ መንገድ “ሜርጅ ተደርጓል” “ተቀንሷል” በሚል ለማጠቃለል ከፍተኛ ሽኩቻ በጋሞ ተወላጆች ዘንድ እየታየ ይገኛል።
ከህዝብ ቁጥርና ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ቀመር ውጪ እየተደለደለ ያለው የክልሉ የአመራር ምደባም እጅግ አነጋጋሪ ሲሆን፣ አዲስ በተፈጠረ ቢሮ ላይም የጋሞ ተወላጆችን ለመሰግሰግ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ከሁለት ቀናት በፊት በWT ሚዲያ የወጣው ዘገባ እንዳመለከተው፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ጥላሁን ከበደ በስልጣን ዘመናቸው የመጨረሻው ተልዕኮ የሆነውን የኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ በትውልድ አካባቢያቸው እንዲሆን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ሁለት ቢሮዎች ተቀንሰው በአንድ እንዲደራጁ ቅድመ ሁኔታውን ማጠናቀቃቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ፕሬዝዳንቱ ለዚህ አላማቸው ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ሲባል አሁን ላይ በቢሮ ደረጃ የሚገኙትን የንግድ ቢሮ እና የኢንዱስትሪ ቢሮ ወደ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ በሚል በማዋቀር የአመራር ለውጥ ለማድረግ የሚያስችላቸውን ከሁለት ቀናት በፊት በተካሄደው የክልሉ ካቢኔ ስብሰባ ላይ ይፋ ማድረጋቸው ታውቋል።
ይህ አደረጃጀት በዋናነት የዎላይታን ሙሁራንና የህዝቡን ስነልቦና ለማዳከም ያለመ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።
ዶ/ር ቦጋለ ቦሼን ጨምሮ ሌሎች ወደ ከፍተኛ ስልጣን እርከን ሊመጡ ይችላሉ ተብሎ የታሰቡ የዎላይታ ተወላጆችን ለማጥቃት ከአመት በፊት ፕሮጀክት ጽ/ቤት ተቋቁሞ ወደ ስራ እንደተገባ በቂ መረጃ ማግኘቱን WT ሚዲያ ይገልፃል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በተለይም በዎላይታ ህዝብ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ከየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል የተለየ መልክ ያለው መሆኑን የአስተያየት ሰጪዎች ይገልጻሉ።
በመንግስት ዩኒቨርሲቲ ከዲግሪ የተመረቁ ከ200 ሺህ በላይ የተማሩ ስራ አጥ ወጣቶች መኖራቸው በቅርቡ በተደረገው ዳሰሳ ጥናት መረጋገጡ፣ ርዕሰ መስተዳድሩ “ለእኔ ብቻ” የሚል አስተሳሰብ እንዳላቸው ያሳያል ተብሏል።
በሀገሪቱ ከተሞች በየጎዳናው በአባታቸው በእናታቸው አቅፍ ሆነው ማደግና መማር የሚገባቸው ህፃናት፣ ወጣቶችና ሴቶች በአካባቢው ምንም የስራ እድል ባለመፈጠሩ በስደት እንዲሁም በተስፋ መቁረጥ ላይ እንደሆኑ አስተያየት ሰጪዎች አክለዋል።
ይህ ሁሉ የህዝብ ችግር በአደባባይ እየታወቀ በአቶ ጥላሁን ከበደ ኢፍትሃዊ አሰራር በአካባቢው ግፍ እየተሰራ ነው ሲሉም ይገልጻሉ።
ከአመት በፊት በፌዴራል መንግስት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እንዲገነባ የቦታ መረጣ ተጠይቆ የነበረው የኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ ጉዳይ የት እንደደረሰ አነጋጋሪነቱ ቀጥሏል።
እስከአሁን ባለው መረጃ የፌዴራል መንግስት በክልሉ የኢንዱስትሪ ፓርክ ለመገንባት ክልሉን የጠየቀው በክልሉ ካቢኔ አለመቅረቡን WT ሚዲያ አረጋግጧል።
የመረጃ ምንጮች እንደሚያስረዱት “በፌዴራል መንግስት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እንዲገነባ የቦታ መረጣ ተጠይቆ የነበረው የኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ ጉዳይ በፕሬዝዳንቱ ምስጢር እንዲሆን የተፈለገበት ከዚህ በፊት እያደረጉት ያሉት አይነት ለእኔ ብቻ አይነት አስተሳሰብ ተግባራዊ ለማድረግ ያለመ ነው” ብለዋል።
ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ይሄንን ተግባራዊ ለማድረግ ምቹ ሁኔታ በማጣት እንደቆዩ በመግለፅ፣ አሁን ላይ የመጨረሻ ሙከራቸው የሆኑትን ሁለት ተቋማትን በማዋሃድ ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለ የሚገኘውን የኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ የሆኑትን ዶክተር ቦጋለ ቦሼን ወደ ሌላ ቢሮ በመውሰድ የኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ በትውልድ አካባቢያቸው ለማድረግ ያለሙትን ለማሳካት እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ምንጮቹ አብራርተዋል።
ከዚህ በፊት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከ3 ወራት በላይ ተሰርቆ ተደብቆ የነበረው የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ቅርንጫፍ ደብዳቤ ከድብቅበት መውጣቱ ይታወሳል።
በመንግስት አመራሮች ግልፀኝነት በጎደለው አኳኋን መረጃ ለወራት በመደበቅ ይፋ አለማድረግ ለሚመሩት ህዝብ ካለመታመን ባሻገር መሠል በርካታ ጉዳዮች በድብቅ እየተሰራ እንደሆነ ግልጽ ማሳያ እንደሆነ በርካቶች ይገልፃሉ።
ክልሉ 32 ብሄረሰቦችን ያቀፈ ቢሆንም፣ የልማት ትኩረቱ በአንድ አካባቢ ላይ ማተኮሩ በሌሎች የክልሉ ከተሞች እና ብሄረሰቦች ዘንድ የመገለል ስሜት እንደፈጠረ እየተነገረ ነው።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ በፌዴራል መንግስት በጀት አማካኝነት በራሳቸው የትውልድ አካባቢያቸው ብቻ በርካታ ትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶችን በማስገንባት ላይ መሆናቸው በክልሉ ውስጥ ቅሬታዎችን ማስነሳቱ ይታወቃል።
ይህ አዲሱ የቢሮ አደረጃጀት እና አመዳደብ የክልሉን ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍልና የአመራር ምደባ ጉዳይ ይበልጥ የሚያወሳስበው መሆኑን ብዙዎች ይስማማሉ።
#Ethiopia #southethiopia