GridArt_20250731_175952702

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ አማራ ክልል ጎጃም የሚኖሩ ሕዝቦች ከዎላይታ ተሰደው የመጡ እንደሆነ የታሪክ ምንጭ አረጋግጧል።

ባለፉት ዓመታት ከዎላይታ ሕዝብ አመጣጥና ታሪክ ጋር በተያያዘ ብዙ ጥናቶች ሲደረጉ ቆይተዋል። አሁን ደግሞ ከጎጃም ደጋ ዳሞት እስከ ሸዋ የተዘረጋውን ጥንታዊ የዎላይታ ታሪክ የሚገልጽ አዲስ መረጃ ብቅ ብሏል።

ከብሔራዊ ቤተ-መጻሕፍት በተገኘ ታሪካዊ መረጃ፣ ከእውቅ አለምአቀፍ ታሪክ ሰነዶች እንዲሁም በታዋቂው የታሪክ ምሁር ዶ/ር አበበ ሀረገወይን ጥናት መሰረት፣ በ12ኛው ክፍለ ዘመን የዎላይታ ታላቅ ንጉስ የነበረው ሞቶሎሚ ከጎጃም ደጋ ዳሞት እስከ ሸዋ ድረስ ግዛቱን አስፋፍቶ እንደነበረ ተመላክቷል።

በብሔራዊ ቤተ-መጻሕፍት ውስጥ የሚገኝ “የደጋ ዳሞት ትውልድ ከነታሪኩ” የተሰኘ ጽሑፍ፣ በደጋ ዳሞት የሚኖሩ አምስት መደብ ዳሞት የሚባሉ ሕዝቦች ከዎላይታ ተሰደው የመጡ እንደሆኑ ይገልጻል። ይህ ስደት የተከሰተው በ12ኛው ክፍለ ዘመን አካባቢ በአፄ ውድም አርዕድ ዘመን የእስላም ኃይሎች በበረቱ ጊዜ ነበር ይላል።

ከዎላይታ የተሰደዱት ሕዝቦች ወደ አራት አቅጣጫዎች የተበተኑ ሲሆን፣ አንደኛው ክፍል ጉራጌ አካባቢ፣ ሌላው ኩሎ (ኮንታና ዳውሮ አከባቢ)፣ ሦስተኛው ከፋ፣ አራተኛውና ትልቁ ክፍል ደግሞ በአማራ ክልል በጎጃም በርካታ ዎላይታዎች መስፈራቸውን የታሪክ ምንጭ ያረጋግጣል።

በአሁኑ አማራ ክልል ውስጥ በጎጃም የሰፈረው የዎላይታ ሕዝብ አምስት አለቆች እንደነበሩትና እነሱም አሞር፣ በርቀኝ፣ ጠሊም፣ ቋሬት እና የዛት ተብለው ይጠሩ እንደነበር ይኸው ታሪካዊ መረጃ ያስረዳል። እነዚህ አለቆች ሕዝባቸውን ይዘው በጎጃም ሰረቤ መሬት፣ ከጉድላ ወንዝ እስከ ብር ወንዝ እና ከየጨረቃን በላይ እስከ ጮቄ ተራራ ድረስ በመስፈር አገሩን “ደጋ ዳሞት” ብለው እንደሰየሙት ጽሑፉ ያትታል።

ዶ/ር አበበ ሀረገወይን የሞቶሎሚን ታሪክ ሲያብራሩ፣ በ12ኛው ክፍለ ዘመን ሞቶሎሚ የተባለ ኃያል የዳሞት ንጉስ ከወላይታ ተነስቶ ወደ ሸዋ በመዝመት ከፍተኛ ጦርነት እንዳደረገ ገልጸዋል። ንጉሱ ጦሩን እያበራከተ ቡልጋን፣ ሳልልሽን፣ ደዋሮን እና ደቡብ ሸዋን ድል አድርጎ ግዛቱን እስከ ጎጃም ደጋ ድረስ ማስፋፋቱ ተመዝግቧል።

የሞቶሎሚ ጦር በኃያልነቱ ይታወቃል፤ ወታደሮቹ በዳሞታ ተራራ ገደላገደሎች እና ዋሻዎች ውስጥ ገብተው የሚሰለጥኑ ከመሆናቸውም በተጨማሪ ልዩ ልዩ የጦርነት ስልቶችን በመጠቀም በዘመናቸው ታላቅ ኃይል መፍጠር ችለው ነበር። የእነዚህ ኃይለኛ የሰራዊት አባላት መካነ መቃብር በአሁኑ ጊዜ በአማራ ክልል ቡልጋ እንደሚገኝም ታሪክ ያመለክታል።

ሞቶሎሚ ከ1195 እስከ 1272 ድረስ ለ77 ዓመታት የዎላይታን ሕዝብ አስተዳድሯል ተብሎ ይታሰባል። በዚህ ረጅም ዘመኑም በዎላይታ ውስጥ ሶስት ታላላቅ የቤተ-መንግስት ማዕከላትን ገንብቷል።

እነዚህም:

  1. የኪንዶ ዜጌረ አካባቢ ቤተ-መንግስት
  2. በቦሎሶ ዛባ ተራራ ላይ የነበረው አፋማ ቤተ-መንግስት
  3. በዳሞታ ተራራ አናት ላይ የሚገኘው ጣዛ ቤተ-መንግስት (ጋሩዋ)

እነዚህ መረጃዎች የንጉስ ሞቶሎሚን እና የዎላይታን ሕዝብ ታሪካዊ ጥልቀት የሚያሳዩ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ስለነበራቸው ሚና አዲስ ብርሃን ፈንጥቀዋል። አንዳንድ የታሪክ መዛግብት እንደሚጠቁሙት የንጉስ ሞቶሎሚን ታሪክ የሕዝቦች መልካም ታሪክ እንዳይፃፍ እና በግልፅ እንዳይወጣ ታፍኖ ተይዟል የሚል እምነትም አለ።

#ንጉሥ #ሞቶሎሚ #Ethiopia #Wolaita