GridArt_20250729_161726737

በኮሌጁ የግንባታ ዝርፊያ፣ ብልሹ አሰራሮች፣ ሀሰተኛ የትምህርት መረጃዎችና ሀሰተኛ ደረሰኞች ማጭበርበር መኖሩ ተገልጿል።

WT ሚዲያ ባደረገው ማጣራት እና የደረሱት ተጨባጭ የሰነድ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በዎላይታ ሶዶ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ውስጥ በርካታ እና አሳሳቢ የሙስና እንዲሁም የሀሰተኛ ሰነድና የትምህርት መረጃ አጠቃቀም ማጭበርበር ወንጀሎች መፈፀሙ ተነግሯል።

እነዚህ ወንጀሎች የኮሌጁን መልካም ስም ከማጉደላቸውም በላይ የህዝብ ገንዘብ በግል ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረጋቸው ተገልጿል።

የWT ሚዲያ ከደረሰው አስተማማኝ ምንጭ በተገኘው የሰነድ መረጃ መሠረት፣ በኮሌጁ ውስጥ የተፈጸሙት ዋና ዋና ጥፋቶች የሚከተሉትን ያካትታሉ፦

  • የሀሰተኛ የትምህርት እና የሥራ ልምድ መረጃዎች:
  • ሁለት የኮሌጁ ሰራተኞች የ8ኛ ክፍል የትምህርት መረጃ ካርድ የሀሰት መሆኑ ተረጋግጧል።
  • የሁለት የሰው ሀብት ባለሙያዎች እና የመረጃ ዴስክ ባለሙያዎች ዲግሪና የስራ ልምድ ሀሰተኛ መሆናቸው ተመላክቷል።
  • አንድ የግዥ ባለሙያ ዲፕሎማ እና ሌላ አንድ ሰራተኛ የሥራ ልምድ ሀሰተኛ ሰነድ እንደሆነ ታውቋል።
  • የሰነድ ያዥ ባለሙያ የሥራ ልምድም ሀሰተኛ መሆኑን መረጃው ያሳያል።
  • የኮሌጅ የገቢ ደረሰኝ ሀሰተኛ በሆነ መንገድ ሲሰራ ተገኝቶ ተይዟል።
  • የገቢ አሰባሰብ ባለሙያ የገቢ አሰባሰብ ደረሰኝ ሀሰተኛ መሆኑን የሚያሳይ መረጃ ደርሷል።
  • የተቋሙ ሞተር ተሽጦ በግል ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን፣ በጉዳዩ የተጠየቀ አካል የለም።
  • ለኮሌጁ ከአለም ባንክ አስር ሚሊዮን ብር ድጎማ የተሰጠው ምንም አገልግሎት ሳይሰጥ ለግል ጥቅም መዋሉ በሰነድ ተረጋግጧል።

ከዚህ በተጨማሪ በ2004 ዓ.ም ተጀምሮ የተቋረጠው የዚሁ ኮሌጅ ህንጻ ግንባታ ከቀድሞ ህንጻ ተቋራጭ ጋር ያለው ውል ተቋርጦ በአዲስ መልክ የቀድሞ ደቡብ ክልል ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ቢሮ ከኬላ ሀላላ ህንፃ ተቋራጭ ጋር የተቋረጠውን ሥራ ለማስቀጠል በ37 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር የውል ሥምምነት ተፈራርሞ ከእንደገና ተጀምሮ የነበረ ቢሆንም እስካሁን በብልሹ አሰራርና ትኩረት ባለመሰጠቱ ምክንያት ግንባታው መቆሙን ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

WT ሚዲያ ከዎላይታ ሶዶ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ የደረሱትን ከላይ የተገለፁ እንዲሁም ሌሎች ይፋ ያላደረግነው መረጃዎች በተመለከተ ማብራሪያና ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ሙከራ ለጊዜው አልተሳካም።

wolaitasodo #Ethiopia #southethiopia