የጋሞ ልማት ማህበር ቦርድ በትናንትናው ዕለት ባካሄደው ስብሰባ፣ የቦርድ አባሉን አቶ ደሳለኝ ከበደ ካዛ እና እጩ ዶ/ር ወንድማገኝ ታዬ ከማህበሩ አባልነት እንዲታገዱ ወስኗል ተብሏል።
ውሳኔው የወጣው ግለሰቦቹ በማህበራዊ ሚዲያ የማህበሩን ስም አጥፍተዋል በሚል ምክንያት እንደሆነ ማህበሩ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ውዝግቡ እንዴት ተጀመረ?
ውሳኔው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተከላካይ ጠበቆች ጽህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ደሳለኝ ከበደ፣ ከጋሞ ልማት ማህበር ቦርድ አባልነታቸው በገዛ ፍቃዳቸው መልቀቃቸውን ተከትሎ ነው።
አቶ ደሳለኝ የለቀቁበትን ምክንያት ሲያስረዱ፣ በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፕሬዝዳንት በሆኑት በአቶ ጥላሁን ከበደ ላይ አስር ከባድ ክሶችን በማህበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ አቅርበው ነበር።
ከክሶቹ መካከል ዋና ዋናዎቹ፡-
👉 የአርባምንጭ እርሻ መሬት ቅርምት: ከ200 ሄክታር በላይ መሬት በአቶ ጥላሁን ከበደ ቀጥተኛ ትእዛዝ ለተለያዩ ግለሰቦች እና ትምህርት ቤቶች በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ብሮች ተላልፏል።
👉 የሙስና እና ብልሹ አሰራር: የልማት ማህበሩ የሰው ሀብት አስተዳደር መመሪያ ተጥሶ፣ የወንጀል ሪከርድ ያለባቸውና ጡረታ የወጡ ግለሰቦች በአቶ ጥላሁን ትእዛዝ ተቀጥረው ሙስና እየፈጸሙ ነው የሚል ክስ ቀርቦ ነበር።
👉 ከህግ በላይ መቆየት: አቶ ጥላሁን እና ሌሎች ግለሰቦች ከ15 ዓመት በላይ በቦርድ አባልነት መቆየታቸው ህገ-ወጥ እንደሆነና ለጥቅም ግጭት መፈጠሩን አቶ ደሳለኝ ገልጸው ነበር።
👉 በሻራ እና ዘይሴ የሰው ህይወት ማለፍ: በአቶ ደሳለኝ መግለጫ፣ አቶ ጥላሁን ከበደ “ካልደፈረሰ አይጠራም” በሚል በንጹሃን ዜጎች ላይ ግድያ እንዲፈጸም ምክንያት ሆነዋል።
የእነዚህ ክሶች መውጣት በጋሞ ልማት ማህበር ውስጥ ከፍተኛ ውዝግብ የፈጠረ ሲሆን፣ WT ሚዲያ ይህን ጉዳይ በቅርበት ሲዘግብ ቆይቷል።
የቦርዱ ውሳኔ ምን ይላል?
ትናንት በተካሄደው የጋሞ ልማት ማህበር ቦርድ ስብሰባ ላይ፣ “ግለሰቦቹ በማህበራዊ ሚዲያ የማህበሩን ስም ማጥፋት ዘመቻ አድርገዋል” የሚል ክስ ቀርቦ ነበር።
በመግለጫው መሰረት፣ አቶ ደሳለኝ ከበደ ከቦርድ እና ከልማት ማህበር አባልነትም ጭምር እንዲወገዱ ሀሳብ ቀርቦ በቦርዱ ተቀባይነት አግኝቷል።
በተመሳሳይ፣ አባላትን ጥርጣሬ ውስጥ የሚያስገቡ ጽሁፎችን በማሰራጨት ክስ የቀረበባቸው እጩ ዶ/ር ወንድማገኝ ታዬም ከልማት ማህበር አባልነት እንዲታገዱ ተወስኗል።
WT ሚዲያ በዚህ ጉዳይ ላይ የቀረበው መረጃ ትክክለኛነትና ለተበደለው ማህበረሰብ የምናደርገው የመረጃ አብዮት ሀቅ ያስመሰከረ ነው ብሏል።
ሚዲያው፣ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት በጉዳዩ ላይ አፋጣኝና ተገቢ እርምጃ እንዲወስዱ ጥሪውን አቅርቧል።