በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ጋሞ ዞን፣ ዛይሴ አካባቢ ከዞኑ 20 መዋቅር መደበኛ ፖሊስ፣ የክልሉ አድማ ብተና ከተወጣጡና አርሶ አደሮች መካከል በተፈጠረ ግጭት የሰው ሕይወት ጠፋ።
ከዚሁ ግጭት ጋር በተያያዘ በዘይሴ ወዘቃ ቀበሌ የሚገኘው የዘንሳ የሐውሻ ትምህርት ቤት በእሳት መውደሙም ተነግሯል።


ግጭቱ የተቀሰቀሰው በቀን 23/11/2017 ዓ.ም በዘይሴ ኤልጎ ቀበሌ፣ ሻንካ አካባቢ ሰራዊቱ የአርሶ አደሮችን የእርሻ ምርት በእሳት ካቃጠለ በኋላ እንደሆነ ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
ለWT ሚዲያ የደረሰው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ግጭቱ የተቀሰቀሰው የፖሊስ አባላት 120 ኩንታል ገደማ የሚሆን በቆሎ እና ማሽላ በእሳት ካወደመ በኋላ እንደሆነ ተገልጿል።
በግጭቱ ምክንያት አንድ የዘይሴ ኤልጎ ቀበሌ ወጣት ሕይወቱ ያለፈ ሲሆን፣ ሁለት የሰራዊቱ አባላት በቦታው ተገድለዋል።
ሌሎች ሁለት የሰራዊት አባላት ከባድ ጉዳት ደርሶባቸው ወደ አርባምንጭ ሆስፒታል ተወስደው የነበረ ሲሆን፣ አንደኛው በማግስቱ ሕይወቱ አልፏል።
በሆስፒታሉ የጽኑ ሕሙማን ክፍል ውስጥ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት የሚገኘው ሌላኛው የሰራዊት አባል ደግሞ የዘሮ ሦስት ቀበሌ ተወላጅ ነው ተብሏል።
ከዚሁ ግጭት ጋር በተያያዘ፣ በዚያው ቀን ከሰዓት በኋላ በዘይሴ ወዘቃ ቀበሌ የሚገኘው የዘንሳ የሐውሻ ትምህርት ቤት በእሳት ተቃጥሏል።
ትምህርት ቤቱ ቀደም ሲል ለሦስት ወራት ያህል በወታደራዊ ካምፕነት ሲያገለግል መቆየቱ ተገልጿል።
ትምህርት ቤቱን በእሳት ያቃጠሉት ወታደራዊ አባላት ወደ ዘይሴ ደንብሌ ቀበሌ ጤና ጣቢያ በማምራት የጤና ባለሙያዎችን በማስፈራራት የጤና ጣቢያውን ወደ ወታደራዊ ካምፕነት እንደቀየሩት መረጃው ያመለክታል።
በዚህ ድርጊት ምክንያት የአካባቢው ሕፃናት እና ነፍሰ ጡር ሴቶች ከፍተኛ ሥጋት ውስጥ ወድቀዋል።
በአርባምንጭ ከተማ በጋሞ ዞን አመራሮች የሚመራ ስብሰባ ተካሂዶ እንደነበር የተገለጸ ሲሆን፣ በዚህ ስብሰባ ላይ የቀድሞ ወታደራዊ አባላት ወይም ከጦር ኃይል የሸሹ የጋሞ ተወላጆች በገንዘብ ተመርምለው ለወታደራዊ ተግባር እየተመለመሉ እንደሆነ መረጃዎች ደርሰዋል።
በተጨማሪም፣ በከተማው የሚኖሩ የፌዴራል ፖሊስ አባላት በገንዘብ በመታለል ወደ ዛይሴ አካባቢ ሕዝቡን ለመግደል እየተንቀሳቀሱ መሆኑ ታውቋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዛይሴ ሕዝብ ተወካይ አቶ አብርሃም አሞሼ፣ በተደጋጋሚ የሚፈጸመው ጥቃትና የሰብዓዊ መብት ጥሰት እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ለWT ሚዲያ ገልጸዋል።

በአከባቢው በተፈጸሙት ጥቃቶች 113 ቤቶች ሙሉ በሙሉ እንደወደሙ፣ ከ21 በላይ ሰዎች እንደተገደሉ እና በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች እንደተፈናቀሉ ተናግረዋል።
አቶ አብርሃም ጥቃቱን የሚያስተባብሩት የጋሞ ዞን መዋቅር አመራሮች ናቸው ሲሉ፣ በተጨማሪም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ እና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ለዚህ ድርጊት ሽፋን እየሰጡ እንደሆነም ከሰዋል።
ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የአካባቢው ነዋሪዎች በሰጡት መግለጫ፣ ሕዝቡ በአስከፊ ረሃብና ፍርሃት ውስጥ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የጸጥታ ኃይሎች በሚወስዱት የኃይል እርምጃ ምክንያት ነዋሪዎች ወደ እርሻ ቦታቸው እንዳይሄዱ በመከልከላቸው ለከፋ ረሃብ እየተዳረጉ ነው።
የዛይሴ ብሔረሰብ ጥቃት የሚፈጸምበት ዋና ምክንያት የራሱን የአስተዳደር መዋቅር ለማግኘት ያቀረበው ሕጋዊ ጥያቄ እንደሆነም መረጃው ያመለክታል። የአካባቢው ነዋሪዎች እና ተወካዮች የፌዴራል መንግስት በአስቸኳይ ጣልቃ እንዲገባ እና የሰብዓዊ መብት ጥሰትን እንዲያስቆም ጥሪ አቅርበዋል።