የዎላይታ ቡና ከአለም አቀፍ ገበያ ስያሜውን በማጣት ቀድሞ ወደነበረበት በሲዳማ ሲ ቡና ስር እንዲሆን መደረጉ ተገልጿል።
የዎላይታ ቡና በጣዕሙ እና በጥራቱ በአውሮፓ ገበያ እየተሸጠ በራሱ ብራንድ ስያሜ አግኝቶ የነበረ ቢሆንም በአሁን ሰዓት ስያሜው ከገበያ እንዲወርድ መደረጉን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የዎላይታ ኦርጋኒክ ቡና ከዚህ በፊት የራሱን ስያሜ አግኝቶ በአለም አቀፍ ገበያ ሲሸጥ የነበረ ቢሆንም ይህንን ይልክ ከነበረው የዳሞታ ዩኒዬን እጅ እንዲወጣ የተደረገ በመሆኑ አዲስ የተደራጀው የቡና ማህበር ቡናን መላክ ባለመቻሉ ለሁለት ተከታታይ አመት ያልተላከ ስለሆነ ከአለም ገበያ ስያሜው ይነሳ እና ቀድሞ ወደ ነበረበት ወደ ሲዳማ ሲ ቡና ይመለስ መባሉን ተከትሎ መመለሱን WT ሚዲያ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
እንደ መረጃው፣ የዎላይታ ቡና ከዚህ በፊት በሲዳማ ሲ ስያሜ በአለም አቀፍ ገበያ እየተሸጠ ቆይቶ የራሱን ስያሜ አግኝቶ በዎላይታ ስም በአለም ገበያ እየተሸጠ የአከባቢው ቡና አምራች አርሶ አደር በከፍተኛ ሁኔታ ተጠቃሚ እየሆነ መምጣቱን ይገለፃል።

ይሁንና ከዚህ በፊት ይሄ ቡና በዎላይታ ስም እየሸጠ የነበረው የዎላይታ ዳሞታ ሁለገብ ገበሬዎች ዪኒየን በኩል የነበረ ቢሆንም በዞን መንግስት በኩል በህብረት ስራ ቢሮ አማካኝነት ዩኒየኑ እንዳይሸጥ በመደረጉ ለተከታታይ ሶስት አመት ቡና ማቅረብ ባለመቻሉ የብራንድ ስያሜው ተቀምቶ ቀድሞ ወደ ነበረበት ሲዳማ ሲ ብራንድ እንዲመለስ ተደርጓል።
አንድ ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ በዘርፉ የተሰማራ ምንጭ ለWT ሚዲያ ሲያስረዳ “የዎላይታ ቡና በጣዕሙ እና በጥራቱ ታዋቂ እየሆነ የመጣ በመሆኑ በአውሮፓ ገበያ እና በአሜሪካ በተለያዩ የገበያ አማሮጮች እየቀረበ በመምጣቱ በጣዕሙ ተመራጭ እየሆነ የነበረ ቢሆንም አሁን በዚህ ጊዜ ለቡናችን ትኩረት በመነፈጉነና ባለቤት በማጣቱ ምክንያት ከገበያው ስያሜው ወርዷል” ብሏል።
በጉዳዩ ዙሪያ ተጨማሪ ምላሽና ማብራሪያ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው ያልተሳካ ቢሆንም የህብረት ስራ ጽ/ቤት የዞን ግብርና እና ዋና አስተዳደሪ በአለም ደረጃ የምንጠራበት ስያሜ ሲወሰድ ምላሻቸው ከወዴት አለ በሚለው ዙሪያ በሰፊው እንመለሳለን።