1000069823

የዎላይታ ቴሌቪዥን እና ዎገታ ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች በአከባቢው ወረዳዎች እና ከተሞች ዕዳ ባለመክፈላቸው፣ ከአየር ላይ የመውረድ አደጋ እንደተጋረጠባቸው ለWT ሚዲያ አፈትልኮ የደረሰው ሰነድ ያመለክታል።

እንደ መረጃችን ከሆነ ጣቢያዎቹ ለሠራተኞች ደመወዝ መክፈልም እንዳቃታቸው ይጠቁማል።

የዎላይታ ቴሌቪዥን ማስታወቂያ ያሰሩ ወረዳዎች፣ ከተማ አስተዳደሮችና ሌሎች አካላት ከ13 ሚሊዮን ብር በላይ ዕዳቸውን ባለመክፈላቸው ማስጠንቀቂያ የተጻፈላቸው ሲሆን፣ የዎገታ ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያም ከ6.1 ሚሊዮን ብር በላይ የውዝፍ ገንዘብ ከወረዳዎች፣ ከከተሞች እና ከዞን መምሪያዎች እንደሚፈለግ WT ሚዲያ አፈትልከው ከወጣው ሰነድ ተመልክቷል።

የተቋማቱ የፋይናንስ ችግር የአድማስ ሽፋናቸውን እንዳያሳድጉ እና የቀጥታ ስርጭት አገልግሎት እንዳይጀምሩ እንቅፋት እንደሆነባቸው ተነግሯል።

ከዚህ ቀደም በተደረገ የአደረጃጀት ለውጥ ሁለቱ ተቋማት በአንድ መዋቅር ስር እንዲተዳደሩ መወሰኑ የሚታወስ ሲሆን አሁን ላይ በገጠመው የፋይናንስ ቀውስ ምክንያት የሰራተኞች ደመወዝ ለመክፈል ከመቸገር ባሻገር ጣቢያው የሳታላይት ክፍያ በጊዜ ባለመክፈሉ ከአየር ሊወርድ ይችላል የሚል ስጋት ተጋርጦባቸዋል።

ሁለቱም የብዙሀን መገናኛ ተቋማት ከመንግሥት ልሳን ባሻገር የህዝብን ድምጽ በማሰማት እና የአከባቢውን ማህበራዊና ባህላዊ እሴቶች በማስተዋወቅ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደነበራቸው ይታወቃል።

ethiopia #Wolaita