በዎላይታ በበርካታ በጎ ተግባራት እና በልማት ስራዎች ተሳትፎ የሚታወቀውን ወጣት ባለሀብትን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አስሮ ወደ አርባምንጭ እያመጣ እንደሆነ ተገልጿል።
የማራ ማይነርስ ባለቤት የሆኑትን አቶ ብርሃነመስቀል ክንፈን (ቤቢ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በተለያዩ ወንጀሎች እንፈልጋለን የሚል የፍርድቤት መጥሪያ ይዘው እንደመጡና ጉዳዩን በአርባምንጭ ለማየት ይዘን እንሄዳለን” በሚል ከአዲስአበባ በአሁኑ ሰዓት እያመጡ እንደሆነ ለWT ሚዲያ የአይን እማኝ አስረድተዋል።
የአይን እማኝ እንደገለፀው የማራ ማይነርስ ባለቤት የሆኑትን አቶ ብርሃነመስቀልን ከ20 በላይ የሚሆኑ የታጠቁና ያልታጠቁ ኃይሎች በፖሊስ መኪና ጭኖ በዛሬው ዕለት ከቀኑ 6:00 አከባቢ መውሰዳቸውን አስረድተዋል።

ከ32 በላይ ብሄር ብሄረሰቦች ያቀፈዉን ክልል ይመሩ ዘንድ ቢሾሙም ከትዉልድ አከባቢያቸዉ ዉጪ ሌላዉን አካባቢ ማየት ተስኗቸዋል ተብለዉ እና ስልጣናቸዉን ተገን በማድረግ ሌብነት ዉስጥ በመዘፈቃቸዉ የሚተቹት ርዕሰ መስተዳድሩ በተለይ ከከሰል ድንጋይ ማዕድን ጋር በተገናኘ የተፈፀመበትን በደል በፍርድ ቤት እየሞገተ የሚገኘዉን ወጣቱን የማራ ማይነርስ ባለቤትን አቶ ብርሃነ መስቀል እና ሌሎች የዎላይታ ባለሃብቶችን በተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች ስማቸዉን በማጠልሸት ሊከሷቸዉ ማቀዳቸውን ከዉስጥ ምጮች ያገኘነዉ መረጃ ጠቅሰን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
በተለይ የማራ ማይነርስ ባለቤት አቶ ብርሃነ መስቀል በደሉን ወደ ፍርድ ቤት ከመዉሰዱ ባሻገር የፓርቲ ሚዲያ የሆነዉ ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን መጥቶ በክልሉ ዉሃና ማዕድን ቢሮ ዉስጥ የሚፈፀመዉን ብልሽትና ሌብነት እንዲያጋልጥ አድርጓል በሚል ርዕሰ መስተዳድሩን ትልቅ ነጥብ ማስጣሉን ተከትሎ መፈላለግ እየሰፋ መምጣቱ ተነግሯል።
በዚህም አቶ ብርሃነመስቀልን በህገወጥ መንገድ ለማሳሰር በህግ አግባብ ለመሄድ ምንም ማስረጃ ማቅረብ ባለመቻላቸዉ በተደጋጋሚ ለካቢኔያቸዉ ቢያቀርቡም የካቢኔ አባላቱ በክልሉ የፍትህ ስርዓት ላይ ጣልቃ እንደማይገቡ፤ እንዲሁም የህግ ማስከበሩ ስራ ከፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ተጠብቆ በማስረጃ ላይ ተመስርቶ ብቻ እንዲሆን አቋም በመያዝ ሀሳባቸዉን ዉድቅ እንዳደረጉባቸዉ ነዉ ከዉስጥ ሾልከዉ የሚወጡ መረጃዎች የሚጠቁሙት፡፡

በካቢኔያቸዉ ተደጋጋሚ ዉሳኔ የተበሳጩት አቶ ጥላሁን ከበደ አሁን ላይ የክልሉ ካብኔ ሳያውቅ በጥቅምና በተለያዩ ትስስር የሚገኙ ሰዎችን በመጠቀም ከፍትህ ቢሮ ጋር በመተባበር መጥሪያ በማውጣት እንዲታሰር አድርገዋል።
ክልሉ በተለይ በከሰል ማዕድን ማዉጣት ላይ ከህግ አግባብ ዉጪ በአከባቢያዊነት እና በግል ጥቅም ትስስር የሚደረግን ዝርፊያ ዘጋቢ ፊልሙ ፍንትዉ አድርጎ ያሳየ ሲሆን በርካታ የርዕሰ መስተዳደር ስር ያሉ ባለስልጣናት የከሰል ማዕድን ቦታ በተለያዩ ማህበራት ስም መያዛቸዉን ነዉ መረጃዎች የሚጠቁሙት፡፡
በአከባቢው በበርካታ በጎ እና ልማት ስራዎች ተሳትፎ የሚታወቀው ወጣት ባለሀብት ብርሃነመስቀል ክንፈ በዎላይታ ዞን አበላ አባያ ወረዳ ላይ ግዙፍ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የስራ ዕድል ይፈጥራል የተባለ የድንጋይ ከሰል ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ለማስጀመር ህጋዊ መስፈርቶችን በሙሉ በማሟላት 40 ሄክታር መሬት የጠየቀው ከብዙ ውጣውረድ በኋላ በቀን 9/2/2017 ዓ.ም የክልሉ ካቢኔ ባደረገው 17ኛ መደበኛ ስብሰባ መወሰኑ ይታወሳል።
ይሁን እንጂ በግልጽና በተጨባጭ በዎላይታ ላይ ኢንቨስትመንት እንዳይስፋፋ ቀጥተኛ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ የሚገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ጥላሁን ከበደ በቀን 28/2/2017 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ የርዕሰ መስተዳድሩ ምክር ቤት የወሰነው የኢንቨስትመንት መሬት ውሳኔ እንዲሻር ማድረጉን ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ የደረሰው የሰነድ መረጃ ማጋራታችን ይታወሳል።
ከዎላይታ ዞን የሚቀርቡ የኢንቨስትመንት መሬት ውሳኔዎች ሆን ተብሎ ከ1 ዓመት በላይ ሳይወሰንና ሰይፀድቅ እንዲቆይ በማድረግ፣ ባለሀብቶች ተስፋ ቆርጠው ወደ ሌላ ዞን እንዲኮበለሉ እየተደረገ ሲሆን በተቃራኒው ከርዕሰ መስተዳደሩ ትዕዛዝ የመጣ የትኛውም ኢንቨስትመንት መሬት ጥያቄ ገና በካቢኔ ሳይወሰን በቀጥታ “የኢንቨስትመንት መሬቱ የተፈቀደ” የሚል ደብዳቤ እንዲጻፍ ይደረጋል። በተቃራኒው ለዎላይታ እና ለሌሎች አከባቢ ሲሆን በካብኔ የተወሰነውን ከእንደገና በመሻር ለመፃፍ ተደርሷል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለአከባቢው ሁለንተናዊ ዕድገት ወሳኝ ሚና ያላቸውን የንግዱ ማህበረሰበንና ባለሀብቶችን የማሳደድና ተረጋግተው እንዳይሰሩ እየተወሰደ የሚገኘው እርምጃ በግልጽ የከተማዋን ዕድገት ወደኋላ የመመለስ እቅድ የተሰራ እንዲሁም በህጋዊ መንገድ የተለያዩ ግዙፍ ፋብሪካ ጀምሮ እንቨስትመንት ለመስራት መሬት ተረክበው በአከባቢው ለበርካታ ወጣቶች የስራ ዕድል የሚፈጥሩ እንቅስቃሴ የጀመሩ ባለሀብቶች ስራ እንዲቆም መደረጉን ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ የሚደርሱ መረጃዎች ይጠቁማሉ።