1756562913158

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የታሰረውን ባለሀብት እንዲያሰቃይ ርዕሰ መስተዳድሩ የሰጠውን ትዕዛዝ አልቀበልም ያለ የጎፋ ሳውላ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ከኃላፊነት ታግዶ እንዲታሰር መደረጉ ተገልጿል።

በሌላ በኩል የባለሀብቱ የፍርድ ቤት መያዣ ትዕዛዝ የሰጠው የጋሞ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቢሆንም የጎፋ ሳውላ ከተማ ፍርድ ቤት ጉዳዩን ያለስልጣን በፍርድቤት ማየቱ አነጋጋሪ ሆኗል።

አቶ ጥላሁን ከበደ በግፍ ያሳሰረውን የማራ ማይነርስ ባለቤት አቶ ብርሃነመስቀልን እንዲያሰቃይ የሰጠውን ትዕዛዝ አልቀበልም፥ እንደማንኛውም እስረኛ የሰብዓዊ መብት ክብሩን እጠብቃለሁ በማለቱ ጥላሁን ከበደ በቀን 22/12/2017 ዓ.ም በሳውላ ከተማ በመገኘት በሰጠው ቀጥታ ትዕዛዝ ተወዳጁ እና ታታሪው ወጣት የፖሊስ አዛዥ ደሳለኝ ጩቱሎ በግፍ ከስራ መታገዱን እና መታሰሩን በራሱ ይፋዊ የፈስቡክ ገፅ አረጋግጧል።

አቶ ጥላሁን ከበደ በቀን 22/12/2017 ዓ.ም ጎፋ ዞን ሳውላ ከተማ የነበረ ሲሆን፣ የተገኘው ግን እንደ ሌላው የክልል መስተዳደር የልማት፣ የጤና እና የመልካም አስተዳደር ችግር ለመከታተል እና የመፍትሔ አቅጣጫ ለመስጠት ሳይሆን፣ በግፍ ያሳሰረውን እንጂነር ብራሀነመስቀል ክንፈን ሰቆቃ ለመጨመር ነበር ሲሉ ሁኔታውን እየተከታተሉ የሚገኙ ግለሰቦች ለWT Media ገልጸዋል።

ታዲያ ርዕሰ መስተዳደሩ ሳውላ ምድር ተገኝቶ እንድ ዞኑ የፖሊስ አዛዥ የከተማ ፖሊስ አዛዥን ከስራው አግዶ ያሳሰረ ሲሆን የሳውላ ከተማ የመጀመሪያ ዳኛ የሆኑትን ሻ/ል ሀብታሙን ጥቁር ካባ አስለብሶ የሚፈልገውን ፍርድ አሰጥቷል በሚል አስረድተዋል።

ኢ/ር ብርሀነመስቀል ክንፈ ስም የወጣውን የፍርድ ቤት የመያዣ ትዕዛዝ የሰጠው የጋሞ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሲሆን፣ የጊዜ ቀጠሮ መዝገብ እየተከታተለ ያለው በሌለው ስልጣኑ የሳውላ ከተማ ፍርድ ቤት ነው፣ ይህ የሆነበት የሳውላ ከተማ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት እና ዳኛ የሆኑትን በዲስፕሊን ለዚህ ቀደም የተቀጣ ሰነምግባር የሌለውን አቶ ሀብታሙ በላይነህን እንዳሻው ለመጠቀም እንደሆነም አስረድተዋል።

ዳኛ በቀን በዋለው ችሎት ተጠርጣሪው ፖሊስ ጣቢያ ወይም ማረፊያ ቤት ሆኖ ጉዳዩን እንዲከታተል በቀን 19/12/2017ዓ.ም የሰጠውን ትዕዛዝ፣ ራሱ ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመሆን የሰጠውን ትዕዛዝ ራሱ ሽሮ በቀን 22/12/2017 ዓ.ም ጥላሁን ከበደ በሳውላ ተገኝቶ በሰጠው ቀጥተኛ ትዕዛዝ፣ በቀን 22/12/2017 ዓ.ም በመሻር ወደ ማረሚያ እንዲገባ ትዕዛዝ አሰጥቷል ብሏል።

ይህ ትዕዛዝ ፍፁም ህገ ወጥ እና ቀድሞኑም የሙስና ወንጀል የተባለውን ምንም እንኳን በውሸት የተመሰረተ ክስም ቢሆን የሳውላ ከተማ ጉዳዩን የማየት ስልጣን ሳይኖረው፣ ለሆዱ ያደረው ዳኛ ካባ ለብሶ የጥላሁን ከበደን ትዕዛዝ መፈፀሙን በመግለፅ ሁኔታው በክልሉ ህጋዊ አሰራር እየተጣሰ ስለመሆኑ ማሳያ ነው በሚል ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል የክልል ፍትህ ቢሮ የሙስና ወንጀል ዳይሬክቶረት ዳይሬክተር አቶ አዲቃ የተባለ ካድሬ ዐቃቤ ህግ ከጥላሁን ጋር እጅና ጓንት ሆኖ የሚሰራ ሲሆን የዚህ ጥፋት ዋና አስተባባሪ ስለመሆኑ ጠቅሷል።

ከ32 በላይ ብሄር ብሄረሰቦች ያቀፈዉን ክልል ይመሩ ዘንድ ቢሾሙም ሌላዉን አካባቢ ማየት ተስኗቸዋል ተብለዉ እና ስልጣናቸዉን ተገን በማድረግ ሌብነት ዉስጥ በመዘፈቃቸዉ በተጨባጭ የሚተቹት ርዕሰ መስተዳድሩ በተለይ ከከሰል ድንጋይ ማዕድን ጋር በተገናኘ የተፈፀመበትን በደል በፍርድ ቤት እየሞገተ የሚገኘዉን ወጣቱን የማራ ማይነርስ ባለቤትን አቶ ብርሃነ መስቀል እና ሌሎች ህገወጥ ድርጊት በሚቃወሙት ላይ ህገወጥ እርምጃ እየወሰዱ ይገኛሉደ

በተለይ የማራ ማይነርስ ባለቤት አቶ ብርሃነ መስቀል በደሉን ወደ ፍርድ ቤት ከመዉሰዱ ባሻገር የፓርቲ ሚዲያ የሆነዉ ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን መጥቶ በክልሉ ዉሃና ማዕድን ቢሮ ዉስጥ የሚፈፀመዉን ብልሽትና ሌብነት እንዲያጋልጥ አድርጓል በሚል ርዕሰ መስተዳድሩን ትልቅ ነጥብ ማስጣሉን ተከትሎ መፈላለግ እየሰፋ መምጣቱ ተነግሯል።

በዚህም አቶ ብርሃነመስቀልን በህገወጥ መንገድ ለማሳሰር በህግ አግባብ ለመሄድ ምንም ማስረጃ ማቅረብ ባለመቻላቸዉ በተደጋጋሚ ለካቢኔያቸዉ ቢያቀርቡም የካቢኔ አባላቱ በክልሉ የፍትህ ስርዓት ላይ ጣልቃ እንደማይገቡ፤ እንዲሁም የህግ ማስከበሩ ስራ ከፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ተጠብቆ በማስረጃ ላይ ተመስርቶ ብቻ እንዲሆን አቋም በመያዝ ሀሳባቸዉን ዉድቅ እንዳደረጉባቸዉ ነዉ ከዉስጥ ሾልከዉ የሚወጡ መረጃዎች የሚጠቁሙት፡፡

በካቢኔያቸዉ ተደጋጋሚ ዉሳኔ የተበሳጩት አቶ ጥላሁን ከበደ አሁን ላይ የክልሉ ካብኔ ሳያውቅ በጥቅምና በተለያዩ ትስስር የሚገኙ ሰዎችን በመጠቀም ከፍትህ ቢሮ ጋር በመተባበር መጥሪያ በማውጣት እንዲታሰር አድርገዋል።

ክልሉ በተለይ በከሰል ማዕድን ማዉጣት ላይ ከህግ አግባብ ዉጪ በአከባቢያዊነት እና በግል ጥቅም ትስስር የሚደረግን ዝርፊያ ዘጋቢ ፊልሙ ፍንትዉ አድርጎ ያሳየ ሲሆን በርካታ የርዕሰ መስተዳደር ስር ያሉ ባለስልጣናት የከሰል ማዕድን ቦታ በተለያዩ ማህበራት ስም መያዛቸዉን ነዉ መረጃዎች የሚጠቁሙት፡፡

በአከባቢው በበርካታ በጎ እና ልማት ስራዎች ተሳትፎ የሚታወቀው ወጣት ባለሀብት ብርሃነመስቀል ክንፈ በዎላይታ ዞን አበላ አባያ ወረዳ ላይ ግዙፍ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የስራ ዕድል ይፈጥራል የተባለ የድንጋይ ከሰል ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ለማስጀመር ህጋዊ መስፈርቶችን በሙሉ በማሟላት 40 ሄክታር መሬት የጠየቀው ከብዙ ውጣውረድ በኋላ በቀን 9/2/2017 ዓ.ም የክልሉ ካቢኔ ባደረገው 17ኛ መደበኛ ስብሰባ መወሰኑ ይታወሳል።

ይሁን እንጂ በግልጽና በተጨባጭ በዎላይታ ላይ ኢንቨስትመንት እንዳይስፋፋ ቀጥተኛ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ የሚገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ጥላሁን ከበደ በቀን 28/2/2017 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ የርዕሰ መስተዳድሩ ምክር ቤት የወሰነው የኢንቨስትመንት መሬት ውሳኔ እንዲሻር ማድረጉን ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ የደረሰው የሰነድ መረጃ ማጋራታችን ይታወሳል።

ከዎላይታ ዞን የሚቀርቡ የኢንቨስትመንት መሬት ውሳኔዎች ሆን ተብሎ ከ1 ዓመት በላይ ሳይወሰንና ሰይፀድቅ እንዲቆይ በማድረግ፣ ባለሀብቶች ተስፋ ቆርጠው ወደ ሌላ ዞን እንዲኮበለሉ እየተደረገ ሲሆን በተቃራኒው ከርዕሰ መስተዳደሩ ትዕዛዝ የመጣ የትኛውም ኢንቨስትመንት መሬት ጥያቄ ገና በካቢኔ ሳይወሰን በቀጥታ “የኢንቨስትመንት መሬቱ የተፈቀደ” የሚል ደብዳቤ እንዲጻፍ ይደረጋል። በተቃራኒው ለዎላይታ እና ለሌሎች አከባቢ ሲሆን በካብኔ የተወሰነውን ከእንደገና በመሻር ለመፃፍ ተደርሷል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለአከባቢው ሁለንተናዊ ዕድገት ወሳኝ ሚና ያላቸውን የንግዱ ማህበረሰበንና ባለሀብቶችን የማሳደድና ተረጋግተው እንዳይሰሩ እየተወሰደ የሚገኘው እርምጃ በግልጽ የከተማዋን ዕድገት ወደኋላ የመመለስ እቅድ የተሰራ እንዲሁም በህጋዊ መንገድ የተለያዩ ግዙፍ ፋብሪካ ጀምሮ እንቨስትመንት ለመስራት መሬት ተረክበው በአከባቢው ለበርካታ ወጣቶች የስራ ዕድል የሚፈጥሩ እንቅስቃሴ የጀመሩ ባለሀብቶች ስራ እንዲቆም መደረጉን ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ የሚደርሱ መረጃዎች ይጠቁማሉ።