በኬንያዉያን ፖለቲከኞች የሚከበረዉ ሞተር ሳይክል በኢትዮጵያ በተለይም በአዲስአበባ ለምን ትኩረት ተነፈገው ? …(የ WT Media ልዩ ጥንቅር)
በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የሞተር ሳይክል ቁጥር እያደገ ቢሆንም፣ በተለይም በኬንያ የፖለቲካ ድጋፍ እያገኘ ባለበት በዚህ ወቅት፣ በአዲስ አበባ ከተማ ያለው አመለካከትና የሞተር ሳይክል አጠቃቀም ላይ የወጣው መመሪያ ግን እያወዛገበ ነው። ይህ የ WT Media ልዩ ዝግጅት በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን የሞተር ሳይክልን ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ሚና ያለውን ልዩነት ይቃኛል።
በተለይም በምስራቅ አፍሪካ ሐገራት በሕንድና ቻይና የሚመረቱ ሞተር ሳይክሎች ቁጥር በፍጥነት እያደገ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ። ይህ ማንም በቀጠናው የተንቀሳቀሰ ሰው የሚታዘበዉም ሐቅ ነው። በተለይ በደቡባዊው የኢትዮጵያ ክፍል ከተቀረዉ ኢትዮጵያ እጅግ በቁጥር በርካታ የሆኑ ሞተር ሳይክሎችን ማየት የተለመደ ነው። በዚህም ብዙዎች ለግል መጓጓዣነት፣ እንዲሁም እንደ ታክሲ ብሎም ለ delivery service ይገለገሉበታል።
ሊጠቀስ የሚችል ጥናት ለማግኘት ባንችልም፣ urban mobility በመጨመር፣ አጎራባች ገጠራማ መንደሮችን ከከተሞች ጋር በማገናኘት፣ ለመንግስትና ለግል ሠራተኞችም አገልግሎት በመስጠት ሞተር ሳይክሎች ተጨባጭ ድርሻ በኢኮኖሚ ዉስጥ እየተጫወቱ ይገኛሉ። ከአስመጪና አካፋፋይነት እስከ ነጋዴነት፣ እስከ ጋራጅ ባለዉ ሰንሰለት እንኳን የሚንቀሳቀሰዉ ገንዘብና የሚፈጠረዉም የሥራ እድል ቀላል የሚባል አይደለም። ብዙዎች በሞተር ሳይክል የታክሲና የመሳሰሉ አገልግሎቶችን በመስጠት የራሳቸዉን ብሎም የቤተሰባቸውን ኑሮ እየደጎሙ ነው።

ለዘመናት ሞተር ሳይክል ለ field ሥራ በተለያዩ ተቋማት ተመራጭ ሆኖ መዝለቁም ይታወቃል፣ መኪና ወደማይደርስባቸዉ ቦታዎችም ስለሚገባ።
በኬንያ የሞተር ሳይክሎች ኢኮኖሚያዊ ሚና
በቅርቡ በጎሮቤት ሐገር ኬንያ ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ በኢኮኖሚው ዉስጥ ሞተር ሳይክል ያለዉን ሚና በመገንዘብ ትልቅ የተባለ እርምጃ ወስዷል። በዚህም ዋጋዉን ከ 190,000 የኬንያ ሽሊንግ ወደ 95,000 እንዲወርድ አድርገዋል። ቅድመ ክፍያዉንም ከ70,000 ወደ 9,500 አዉርደዉታል። በተጨማሪም በቀን ብድሩን ለመመለስ ይከፈል የነበረዉን 500 ሽሊንግ ወደ 180 ማዉረዳቸዉ ሳያንስ ፣ፓርላማዉ ታክስ እንዲያነሳና ተጨማሪ ከዋጋዉ 10,000 ብር እንዲቀንስ ለማስደረግ ቃል ገብተዋል። በእዉነቱ ይህ የፕሬዝዳንቱ እርምጃ በጣም የሚደነቅ ነው።
በነገራችን ላይ በኢትዮጵያ የሞተር ሳይክል ዋጋ ባለበት ከቀጠለና የኬንያዉ ዉሳኔ በሐገራቱ መሐል ኮንትሮባዉንድ ሊያስፋፋ እንደሚችል ይጠረጠራል፣ ወደ ሌሎች የኬንያ አጎራባች ሐገራትም እንዲሁ።
በአዲስ አበባ ያለው አመለካከትና መመሪያ
ወደ ኢትዮጵያ ስንመለስ በተለይ በአዲስ አበባ ስለሞተር ሳይክል በአስተዳደር አካላት ዘንድ ያለዉ አመለካከት ጤናማ አይመስልም።
ሞተር ሳይክል በአዲስ አበባ በጥብቅ የሚከለከለዉ በሞተር ሳይክል የታገዘ የነጠቃ ሌብነትን የመከላከል ጤናማ አላማ ብቻ በመያዝ ነው ለማለት ይቸግራል፣ በተለይ መመሪያ ቁጥር 155/2016ን ያነበበ ይሄንን ይረዳል። አሁንስ በጥብቅ መመሪያ ሥር የ delivery ሥራ የሚሰሩትንስ ማዋከብ እዉን ሕገወጥነትን ለመታገል ነው የሚሉ ጥያቄዎች መልስ ያሻሉ። በተለይ የራይድ አይነት ድርጅት ቢቋቋም፣ ሰዉን የማጓጓዙን ሥራ የበለጠ አመቺና ከወንጀል የጸዳ ሊያደርገዉ ይችላል።
መኪና በማይገባባቸዉ መንገዶች፣ ከአስፋልት በተለይም ከታክሲ መጫኛ በሚርቁ ሰፈሮች፣ ሰፊ ጊቢ ባላቸዉ የመንግስትና የግል ተቋማት፣ ከአንዱ የከተማዉ ጫፍ ወደሌላዉ አቆራርጦ፣ ከትራፊክ መጨናነቅ ነጻ ሆኖ ለመጓዝ መሰል ድርጅት ቢኖሮ ተመራጭ እንደሚሆን ግልጽ ነው። ለብዙ ወጣቶችም የሥራ እድል ይፈጥራል፣ ሌሎች የትራንስፖርት ዘርፎችም ዉድድሩን ለማሸነፍ የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ ያግዛል።
በግልም ብዙ ሰዉ ሊጠቀም ይችል፣ ድርጅቶችም እንደዛዉ፣ ለአካል ጉዳተኞችም ምቹ የሆኑ ሞተር ሳይክሎች ለ economic inclusion አስተዋጽኦአቸዉ የጎላ ስለሆነ በልዬ ሁኔታ መታዬት አለባቸዉ።
በአዲስ አበባ ከተማ የወጣዉ መመሪያ በሁለት አመት ዉስጥ ሁሉም ሞተር ሳይክሎች የኤሌክትሪክ ብቻ ይሁኑ ማለቱ ቢደነቅም፤ ከመነሻዉ የትራንስፖርት አይነት ሲል ገድቦ ይጀምራል ይሄም፣ በተገጠመ ሳጥን እቃ ማጓጓዝ፣ ሌላዉ ለግል መጠቀም።
እዚህ ጋር ከአሽከርካሪዉ ተጨማሪ ሰው መጫን እንዳልተካተተ ማለትም እንደማይቻል ልብ ይሏል። የመመሪያዉ ጠንካራ ጎን የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል ፣ከእንግዲህ የኤሌክትሪክ ሞተር ሳይክሎችን ብቻ እንደአዲስ መቀበሉ፣ በተጨማሪም ከሁለት አመት በሁዋላ የኤሌክትሪክ ያልሆነ በሙሉ ከአገልግሎት ዉጪ እንደሚሆኑ መጠቆሙ ነው።
ከዛ ባለፈ ግን መመሪያዉ ጤናማ አመለካከት ባላቸዉ ሰዎች ተጽፏል ለማለት ይቸግራል፣ የደቡብ ሰዉ በኢኮኖሚው ዉስጥ በብዛት ይገባል ተብሎ የተሰራ ተንኮልም ሊሆን ይችላል። መመሪያዉ ሰዎች ሞተር ሳይክልን እንዳይጠቀሙ እንዴት እንገድብ በሚል እሳቤ የወጣም ይመስላል፣ ሰዉ ሞተር ሳይክልን ለሌብነት ብቻ የሚገዛዉ የሚመስላቸዉ ሰዎች አርቅቀዉታል። በመሰረቱ አዲስ አበባ ከሌሎች የኢትዮጲያ ከተሞች በዚህ ደረጃ የተለዬች አድርጎ ማሰብ ጤነኝነት አይደለም።
ሌብነትንም የመከላከል ኃላፊነት ያለበት አካል CCTV cameras ገጥሞም ጭምር ሥራዉን መሥራት ይጠበቅበታል። መመሪያዉ ሞተር ሳይክል በከተማዋ ከአለባበስ ጀምሮ፣ ከፈቃድ አሰጣጥ ጀምሮ በጣም አሰልቺና ተመራጭ እንዳይሆን ታስቦ የተሰራ ይመስላል። ከአሳሪ መመሪያዎች በተላቀቀ መልኩ ቢፈቀድ ብዙ ጥቅም መስጠቱ የሚጠበቅ ነገር ነው እንደሌሎቹ ከተሞች።
መኪና afford ለማያደርጉ ነገር ግን ሥራቸዉ እንቅስቃሴን ለሚፈልግባቸዉ፣ ከዳር ሰፈሮችና አጎራባች ከተሞች እየተነሱ በመሐል ከተማ ለሚሰሩ፣ ከታክሲ መያዣ ቤታቸዉ ለሚርቅባቸዉ፣ ለመኪና ሞቹ መንገድ በሌለባቸዉ ቦታዎች ከፍተኛ ግልጋሎት ሊሰጡ እንደሚችሉ ግልጽ ነው።
የአካባቢ ብክለትና የወደፊት አቅጣጫ
በቅርቡ በተሰራዉ የኮሪደር ልማት ላይ የሳይክል መንገድ መሠራቱ ይታወቃል፣ በዚህም የሳይክል ቁጥር እየጨመረ ነው፣ ከዛም በተጨማሪ E bikes እየታዩ ነው፣ እነሱን ፈቅዶ የኤሌክትሪክ ሞተር ሳይክሎችን በአሳሪዉ መመሪያ ጠርንፎ መቀጠሉ ዉሃ አያነሳም። ስለዚህ አጠቃላይ የተሻሻለ መመሪያ ከተማዋ እንደሚያስፈልጋት ግልጽ ነው።
በተለይ የኤሌክትሪክ ሞተር ሳይክሎች በጣም መበረታታት አለባቸዉ። በእንግሊዝ የቀድሞ ለንደን ከንቲባ ቦሪስ ጆንሰን (ሁዋላ ላይ ሐገሪቷን መርቷል) እና ከ2016 የአዉሮፓዉያን ዘመን እስካሁን ያለዉ ከንቲባ ሳዲቅ ካህን ብዙ ሥራ ሰርተዋል። ሆላንድ ከተሞቿን ለሳይክል ምቹ ከማድረግ በዘለለ ጥሩ ፖሊሲዎችን እንዳረቀቀች ይነገራል፣ ዴንማርክም በተከታይነት ትጠቀሳለች፣ እንደዉም ፖለቲከኞቿ ሁላ ወደ ሥራ በሳይክል ይሄዱባታል፣ ከዛ ትምርህት መዉሰድ ይገባል።
በዎላይታ ሶዶ በቅርቡ በብዙ ሚሊየን ብሮች የከተማ አስተዳደሩ ሞተር ሳይክሎችን ለሠራተኞቹ እንደገዛ ይታወቃል፤ ያ ግን የኤሌክትሪክ ቢሆን ለከተማዋ አንድ ድምቀትና ስልጡን አካሄድ ይሆን ነበር፣ ከእንግዲህ ሊታሰብበት ይገባል። በግለሰቦች ግን በከተማዋ ብዙ የኤሌክትሪክ ሞተር ሳይክሎች እየተስፋፉ መሆናቸዉ አስደሳች ነው።
ምናልባት ከሞተር ሳይክል ጋር ተያይዞ የሚነሱ ሁለት አሳማኝ ቅሬታዎች አሉ አንደኛዉ የድምጽና አየር ብክለት ሲሆን ሁለተኛዉ የአደጋ ተጋላጭነት ነው። የመጀመሪያዎቹ በኤሌክትሪክ ሞተሮች የሚፈቱ ሲሆን ሁለተኛዉ ጥብቅ የትራፊክ ሕግ ማስከበር ከተካሄደ በተለይ በቴክኖሎጂ የታገዘ ችግሩ ትርጉም ባለዉ ደረጃ ይቀረፋል።
ስለዚህ አዲስ አበባ ከተማ የመመሪያ ማሻሻያ ሞተር ሳይክልና ሳይክሎችንም አካትቶ እንደገና በሰፊዉ ተጠንቶ ተሻሽሎ መዉጣት አለበት፣ የሚጠቀሙት መንገድ የሚለያይበት ሁኔታ በተለይ በዋና መንገዶች መለያዬቱ እንደተጠበቀ ሆኖ። ኬንያ እንደ ሥራ እድል መፍጠርያና የኢኮኖሚ አካታችነት መሳሪያ የምታዬዉን፤ በአዲስ አበባ የሌብነት መሳሪያ አድርጎ ብቻ መዉሰድ ጤናማ አይደለም።
ስለዚህ ከተማዋ የሞተር ሳይክልን እና የሳይክልን የኢኮኖሚ ሚና ያካተተ የተሻሻለና ፍትሃዊ መመሪያ እንደምትፈልግ ግልጽ ነው።
ይህ የ WT Media ልዩ ዝግጅት ሌሎች ሚዲያዎች ትኩረት ያልሰጡት የሞተር ሳይክልን ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ሚና ያለውን ልዩነት ለማስቃኘትና መፍትሔ ለመጠቆም ያለመ ዝግጅት ነው።
ማሳሰቢያ፦ WT Media በሀገሪቱ በተለይም ደቡብ ኢትዮጵያ አከባቢ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት በማያገኙ ለተጮቆኑ ህብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥተው እውነትንና ሀቅን መሠረት አድርገው የሚሰራ ስለሆነ የመረጃ ሰጪ ግለሰቦች ምስጥርና ደህንነት በተጠበቀ ሁኔታ የደረሱን መረጃዎችን መልሰን አጣርተን ለህዝብና የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዲሰጡበት በታማኝነት ይፋ እናደርጋለን። ለማህበረሰቡ ከፍተኛ ፋይዳ ባላቸው ህዝብ ጉዳዮች ላይ ሀሳባችሁን ለማካፈል ለሚፈልጉ ሁሉ WT ሚዲያ በደስታ ተቀብሎ ያስተናግዳል። በሌሎች ትላልቅ ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለ ዘውትር አብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው!! እኛ ዘውትር የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን !!
Voice of Marginalized Community – WT Media