GridArt_20250914_155608850

ኬኒያ ናይሮቢ ውስጥ የሚኖር አንድ ኢትዮጵያዊ ግለሰብ በርካታ ኢትዮጵያውያንን ወደ ካናዳ እልካለሁ በማለት በሀሰት በርካታ ገንዘብ እንዳጭበረበረ ተጎጂዎች ለሚዲያ ገልጿል።

ተጠርጣሪው ዳንኤል ሙሉነህ ለማ የሚባለው የ26 ዓመቱ ወጣት ሲሆን፣ ከተለያዩ ግለሰቦች ከ1.5 ሚሊዮን ብር እስከ 2.5 ሚሊዮን ብር የሚደርስ ገንዘብ እንደተቀበለ ተነግሯል።

ተጎጂዎቹ ለWT Media በሰጡት ቃል መሰረት፣ ዳንኤል ሙሉነህ የማጭበርበሪያ ዘዴውን ሲጠቀም ከስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽን (UNHCR) ሰራተኞች ጋር በቅርበት እንደሚሰራ እንዲሁም ሌሎች ተቋማት ውስጥ የሚያውቃቸው ሰዎች እንዳሉ በመግለጽ ሰዎችን እንደሚያሳምን ተገልጿል።

በተጨማሪም “ሰዎችን ለማጭበርበር የሚጠቀሚበት መንገድ በሌላ ስራ አጋጣሚ የሚቀርበውን ሰው ሁሉ፦ ከኢትዮጵያ ወደ ካናዳ ለመላክ ያመጣው ግለሰቦች ናቸው ለማለት አስቀድሞ ለማሳመን ያዘጋጀው ቤት ውስጥ የተቀመጡ ኢትዮጵያዊያን ግለሰቦችን እንዲጎበኙ ያስደርግና በርካታ ገንዘብን ይዘው ተሰውረዋል” ብሏል።

ተጎጂዎቹ ግን አሁን ላይ እነዚህ ሰዎች ሆን ተብሎ ያሳመናቸው የወንጀሉ ሰለባዎች ወይም ወንጀሉን ለማስፈጸም እንደመሳሪያ ያገለገሉ እንደሆኑ ይጠረጥራሉ።

አንድ ተጎጂ ለ WT Media እንደገለጹት፣ ተጠርጣሪው “የቆዩ ስደተኞች ወደ ሶስተኛ ሀገር የሚሄዱበትን ዕድልና ወረፋ ከUNHCR ሰራተኞች ጋር በገንዘብ ተደራድረን በመሸጥ ወደ ተለያዩ ሀገራት እንልካለን” በማለት ስምምነት ያደርጋል።

ከዚያም በፓስፖርት ኢትዮጵያውያንን ወደ ኬንያ በማስመጣት ጉዳዩን በአንድ ወር ውስጥ እንደሚያጠናቅቅ ቃል ይገባ ነበር።

በዚህ የማጭበርበር ወንጀል ከተሳካ በኋላ ዳንኤል ሙሉነህ መሰወሩን ተከትሎ፣ የኬንያ ፖሊስ በተጎጂዎች ጥቆማ መሰረት ክትትል እያደረገበት እንደሆነ ተነግሯል።

በተጨማሪም፣ ተጠርጣሪው ከዚህ ከአምስት ወራት በፊት በናይሮቢ ጎንግሮድ በተባለ ቦታ በሰው ማዘዋወር ወንጀል ተጠርጥሮ እንደታሰረና በዋስ እንደተለቀቀ WT Media ያገኘው መረጃው ያመለክታል።

ተጎጂዎቹ የግለሰቡ መታወቂያ ነው በሚል ለ WT Media ያሳዩት የመታወቂያ ኮፒ የኬኒያ መንግስት ለዜጎቹ የሚሰጠው መታውቂያ ነው፣ ሙሉ ስሙ ዳንኤል ሙሉነህ ለማ ይላል፣ በተጨማሪም የተወለደበት ስፍራ ሞያሌ ይላል፣ ነገር ግን ይሄው መታወቂያ እውነተኛ ይሁን ሀሰተኛ ስለመሆኑ አልተረጋገጠም።

የግለሰቡ መታወቂያ ነው በሚል ለ WT Media ያሳዩት የመታወቂያ ኮፒ

ሌላው ተጎጂዎቹ ለግለሰቡ በተለያዩ ጊዜያት ገንዘብ የከፈሉበት በእሱ ስም ቀጥታ ባለው ባንክ አካውንት ቁጥር ሳይሆን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተከፈተ በሌላ ሰው ስም እንደሆነ አስረድተዋል።

ይሄም ተጠርጣሪው ግለሰብ አስቀድሞ ለማጭበርበርና ማንነቱ እንዳይታወቅ ለመደበቅ የተጠቀመበት ዘዴ እንደሆነ ይገመታል።

ተጎጂዎቹ ለሚዲያ ባስተላለፉት መልእክት፣ “ለወዳጅ ዘመዶች ህይወት መለወጥ በማሰብ ለዘመናት በላባቸው ሰርተው ደክሞ ያፈሩትን ገንዘብ በርካቶች ተነጥቀዋል፣ ቢያንስ ገንዘቡ ባይገኝ ሌላ ሰው በዚህ ግለሰብ እንዳይጭበረበር እና ከመሰል መጭበርበር ጥንቃቄ እንዲያደርግ መልዕክት አድርሱልን” በማለት ገልጸዋል።