GridArt_20250918_191310804

በጎፋ ዞን ሳውላ ማረሚያ ተቋም ላይ በእስር ላይ በሚገኝ ባለሀብት ላይ የረቀቀ የግድያ ሙከራ መፈፀሙ ተገለፀ።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ የክልሉን ብልሹ አሰራሮችና መብቱን በፍርድቤት ለማስከበር ባደረገው እንቅስቃሴ ምክንያት በግፍ ታስሮ በሚገኘው የማራ ማይነርስ ባለቤት፣ ወጣት ባለሀብት ኢንጂነር ብርሃነመስቀል ክንፈ በታሰረበት በሳውላ ማረሚያ ተቋም የተደረገው የተጠና የግድያ ሙከራ በተቋሙ ጠንካራ ስራና ክትትል ሊከሽፍ መቻሉን WT Media ያገኘው መረጃ ያረጋግጣል።

ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ እንደዘገብነው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ተልዕኮ ሰጭነት፣ የባለሀብቱ ከሳሽ የሆነው የክልሉ ውሃ ማዕድን እና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ አክሊሉ አዳኝ አማካይነት፣ ከህግ አግባብ ውጪ የዎላይታውን ወጣት ባለሀብት ኢንጂነር ብራሀነመስቀል ክንፈን፣ ከተቋም እውቅና ዉጪ ተላላኪ የክልሉ ምክትል ፖሊስ ኮሚሽነር ጉራማይሌ ጉርኣ (የጎፋ ተወላጅ) አዲስአበባ ድረስ በመላክ እና ህዝብና መንግስትን ለመጠበቅ የቆመን የፖሊስ ሰራዊትና ስልጣን ያለአግባብ በመጠቀም፣ ወጣቱን ያልተፈጸመ ወንጀል ፈጽሟል የሚል ሽፋን በመስጠት በጎፋ ማረሚያ ግዞት አስቀምጠውታል።

በ “ማዕድን ስር ቁማር” በተሰኘው የፋና ምርመራ ዘገባ ያጋለጠውን የሙስና ወንጀል እና በክልሉ ያለውን ብልሹ አሰራር አጋልጠሃል በሚል የቅም በቀል በመነሳት የከሳሽን ወንድም ዳኛ አብራሃም አዳኝ ጭምር ተጠቅሞ የሀሰት ክስ በመመስረት አቶ አክሊሉ አዳኝ በበላይነት በሚመራው ጎፋ ዞን ላይ ወጣቱን ባለሀብት በግፍ አስረውና ህገመንግስታዊ የዋስትና መብቱን ጭምር በመከልከል የወጣት ባለሀብቱ የሆነውና በፍርድቤት እግድ ላይ የሚገኘውን የቦሮዳ የድንጋይ ከሰል ማዕድን ቦታ በጥቅም ተጋሪዎቻቸው ኢያሱ ወሰን፣ ፍፁም ታዬ፣ አለማየሁ ጎንጮ፣ ያለነው (ለምለም ሆቴል) እና የመሳሰሉት ጋር በጥምረት ዝርፊያው እየፈጸሙ እንደሆነም በደረሰን መረጃ ላይ ተገልጿል።

ይህንን ለመቆም የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድቤት ትዕዛዝ በመቀበል ለማስፈጸም ወደ ክልሉ የመጣውን የፌዴራል ፖሊስ ወደ ክልሉ አይገባም ብለው በመከልከል የዝርፊያ ተግባሩን ሊያስቆሙ ሲገባ ተባባሪ በመሆን ወንጀል እየፈጸሙ እንደሆነ WT Media መዘገቡ ይታወሳል።

ይህንንም ተከትሎ የወጣት ባለሀብት ኢንጂነር ብራሀነመስቀል የህግ ቡድን በሰራው ጠንካራ ስራ በፌዴራል ፍርድቤት ውጤት እየተገኘ መሆኑን የተመለከተው እና የማታ ማታ ወንጀል የፈጸመ አካል ተጠያቂ መሆኑ እንደማይቀር የተረዳው በክልሉ የሚገኘው እኩይ ቡድን፣ “ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንገላገለው ይወገድ” በሚል ሀሳብ መስማማታቸውን  አንድ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተል የህግ ባለሙያ አብራርተዋል።

በዚህም ባለሀብቱ በሳውላ ማረሚያ ባለበት ለማስገደል ወይም ተጠያቂ የሚያደርገው ከባድ ወንጀል እንደፈጸመ ለማድረግ እንዲሁም በህዝብና በበላይ አካላት የሀሰት መሆኑን የተነቃባቸውን የአሁኑን ክስ በማቋረጥ በአዲስ ክስ ለመምጣት እየሰሩ እንደሆነም አስረድተዋል።

ይህንንም ለማሳካት የባለሀብቱ ከሳሽ የሆነው የክልሉ ውሃ ማዕድን እና ኤነርጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ አክሊሉ አዳኝ ይመራው ከነበረው የዲላ ክላስተር፣ ዲላ ማረሚያ ቤት፣ የጎፋ በተለይም የራሱ የአቶ አክሊሉ ቅርብ የአካባቢ ልጅ የሆነውን እና በቅጽል ስሙ “ሻፎ” በመባል የሚታወቀውን ግለሰብ የግድያ ሙከራ ወንጀል የፈጸመ እና በበርካታ ወንጀሎች ጥፋተኛ በመባል የገዛ አጎቱን ጭምር በችሎት ፊት በቢላዋ አንጀ’ቱን በመዘር’ገፍ በሰራው ወንጀሎች የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶበት በዲላ ማረሚያ ተቋም የሚገኘውን የህግ ታራሚ ግለሰብን በመጠቀም እንደሆነ ተነግሯል።

ታራሚው የዚህን የእኩይ ቡድኑ ተልእኮ ተሰጥቶት ወደ ሳውላ ማረሚያ እንዲዛወር በማድረግ በዚህ በሳውላ ማረሚያ የሚገኘውን ወጣቱን ባለሀብት ብራሀነመስቀል ላይ ግድያ እንዲፈጽም የተላከ ቢሆንም፣ የሳውላ ማረሚያ ተቋም ከተላከው የህግ ታራሚ ግለሰብ ስልክ፣ በርካታ ሲም ካርድ፣ የሞባይል ባትሪ፣ አደገኛ አደንዛዥ እጽ፣ ስለት (ጩቤ) በትራስ እና በፍራሽ ውስጥ በደበቀበት በፍተሻ በማግኘት፣ ከዚህ በፊትም የግለሰቡ አደጋኝነቱ የታወቀ ነው በሚል ወደ ዲላ ማረሚያ እንዲመለስ መደረጉን ከስፍራው ለ WT Media አፈትልኮ የደረሰው መረጃው ይጠቁማል።

ከዚህ በፊት ወጣት ባለሀብቱ ወደ ጎፋ በተወሰደበት ጊዜ ተመሳሳይ ድርጊት አቶ ጥላሁን ከበደ በግፍ ያሳሰረውን የማራ ማይነርስ ባለቤት አቶ ብርሃነመስቀልን እንዲያሰቃይ የሰጠውን ትዕዛዝ “አልቀበልም፣ እንደማንኛውም እስረኛ የሰብዓዊ መብት ክብሩን እጠብቃለሁ” በማለቱ ጥላሁን ከበደ በቀን 22/12/2017 ዓ.ም በሳውላ ከተማ በመገኘት በሰጠው ቀጥታ ትዕዛዝ ተወዳጁ እና ታታሪው ወጣት የፖሊስ አዛዥ ደሳለኝ ጩቱሎ በግፍ ከስራ መታገዱን እና መታሰሩን መዘገባችን ይታወሳል።

“በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በወጣት ባለሀብት ብራሀነመስቀል ላይ የተከፈተው የክስ ሂደት ህጋዊ ስልጣን በሌላቸው አካላት የተጀመረ ህገወጥ ክስ ነው” ሲሉ የህግ ባለሙያዎች መግለጻቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

በተጨማሪም “የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፍትህ ቢሮና የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በባለሃብቱ ኢንጂነር ብርሃነመስቀል ክንፈ ላይ የመሰረቱት ክስ ፍሬ ነገር ሲጨመቅ ባለሃብቱን ለማጉላላትና በማረሚያ አክርሞ ለመበቀል ካልሆነ በቀር ጭብጡ ውሃ የሚያነሳ አይደለም” ሲሉ የህግ ባለሙያዎች ተናግረዋል።

በቀዳሚነት የሙስና ወንጀል ዋና ፈጻሚ ሳይኖር ከዋና ፈጻሚዎች ጋር በድርጊት በመተባበር በሚል የቀረበው ክስ የት ከማን ጋር መቼ እና እንዴት የሚሉ መሰረታዊ የድርጊት ወይም ክዋኔ ዑደቶችንና ሂደቶችን የማያመላክት እጭቅ ፍረጃ እንጂ የሰውና የሰነድ ማስረጃ ቀርቦበት የተደራጀ ክስ አይደለም ብለዋል።

ሲቀጥል በፍትሐብሄር የወንጀል ዘውግ ላይ የሚወድቀው “ይህን ያህል ኪሳራ ደርሶብኛል” የሚለው ክስም ቢሆን ግለሰቡ ከክልሉ ጋር ያለውን አለመግባባት በውይይትም ሆነ በድርድር ለመፍታት የሚያስችል ቀናነት በማጣቱና በደም እና በአከባቢያዊነት ማሰብና መመዘን በመጀመሩ ጉዳዩን ወደ ፌዴራል ፍርድ ቤቶች ወስዷል ሲሉ ባለሙያዎቹ አስረድተዋል።

ጉዳዩ በፌዴራሉ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት እየታየ እያለ የፍርድ ቤት እግድ ጥሰው “የእኛ” ለሚሏቸውና በጥቅም ለተሳሰሯቸው ባለሃብት ግለሰቦች/ ጥላሁን ከበደ፤ አክሊሉ አዳኝ፤ ብርሃኑ ዘውዴ፤ አጸደ አይዛ፤ አለማየሁ ባውዲ፤ ተፈሪ አባቴና የመሳሰሉ የክልሉ ቱባ ሌቦች በስውር ባደራጇቸው ማህበራት ሊቀራመቱ የግለሰቡን ይዞታ መሸንሸን ተገቢነት የለለው ህገወጥ ተግባር ስለመሆኑ አብራርተዋል።

“ፋና ቲቪም ገመናቸውን አጋለጠ። ብርሃነመስቀልም ፋና ዶክመንተሪ ላይ በደሉን ዘረገፈ። ሀገር ጉድ አለ። ጥላሁን ጥርሱን ነከሰበት። ስልጣኑን ተገን በማድረግ ተስፈኛውን ወጣት ማረሚያ አስገብቶ መጫወት ጀመረ። ሲጀመር የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ላይ በክስ ሂደት ላይ ያለን ጉዳይ ወደ ግልግል ዳኝነት እንዲያመራ ዳኛ መርጠው ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ፣ በህገ ወጥ መንገድ የተሸነሸነውና እግድ የተላለፈበት ቦታ ይከበር በሚል እየጠየቀ ሳለ ባልተቋጨ ክርክር ረቺም ተረቺም ባልተለየበት ‘ጉዳት ደርሶብኛል’ ብሎ መክሰስ ክሽፈት ነው” ብለዋል።

በተጨማሪም “ክልሉ ላይ ፖሊስ የጥቂት ባለስልጣን ነን ባዮች መቀለጃ ወደመሆን እየተቃረበ መጥቷል። እከሌን እሰር ሲባል የሚያስር ፍታ ሲባል የሚፈታ ተላላኪ ሆኗል። ከሙያቸው ይልቅ ሆዳቸውን የሚያስቀድሙ አዛዥ ነን ባይ ደላሎች መዋቅሩን ሞልተውታል። እናዝናለን። ፍርድ ቤቶች በአንፃራዊነት ተቋማዊ ነጻነታቸውን ድንበር አያስደፍሩም። ጥቂቶች ቢያሸረግዱም አብዛኛዎቹ በህሊናቸው ይዳኛሉ። ህዝብም ይጠብቃችኋል። ፍትህ ሲሰፍን ሀገር ነውና የሚረካው” በሚል የህግ ባለሙያዎች ሀሳባቸውን አክለዋል።

ሌላኛው በዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የህግ ጠበቃ በጉዳዩ ዙሪያ ለ WT Media በሰጠው ሙያዊ ሀሳብ “በአዋጅ ቁጥር 1234/13 አንቀጽ 5 ላይ መደበኛ ነዋሪነታቸው በተለያዩ ክልሎች (አ.አ) ጨምሮ በሚኖሩ አካላት መካከል የሚከሰት ክስ የማየት ስልጣን የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ነው። የክልሉ ዐቃቤ ህግ አድራሻ ሳውላ ተከሳሽ አዲስ አበባ መሆኑ ብቻውን የክልል ፍርድ ቤትን ስልጣን ያሳጣል” ብለዋል።

አክለውም “ሌላው በህገመንግስቱ አንቀጽ 80 መሰረት የውክልና ስልጣን ለክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተሰጥቷል እንዳይባል ለክልል ከፍተኛ ፍ/ቤት የተሰጠው ውክልና የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት መሆኑን ከህገመንግስቱ ድንጋጌ መረዳት ይቻላል።

ይህን ይዘን የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ስልጣን ስንመለከት ከአስር ሚሊዮን በታች የገንዘብ ግምት ያላቸውን ጉዳዮችን ብቻ እንደሚመለከት ከአዋጁ 1234/13 አንቀጽ 11 መረዳት ይቻላል” በሚል አስረድተዋል።

ባለሙያው ሁኔታውን ሲያስረዳ “ይህ ማለት በሌላ አነጋገር ውክልና የተሰጠው የክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከአስር ሚሊዮን ገንዘብ መጠን የበለጠውን መዳኘት ስረ ነገር ስልጣን የለውም። የ1.3 ቢሊዮን ብር ግምት የፌዴራል ጉዳይ የማየት ብቸኛ ስረ ነገር ስልጣን የሚኖረው ተከሳሽ የሚገኝበት ፌደራል ከፍተኛ ማለትም ንፋስ ስልክ ላፍቶ ምድብ ችሎት ብቻ ነው” ብለዋል።

“ዐቃቤ ህግ ክስ የከፈተ አካል የሚያስጠይቅ ነው። ሌላው በዚህ ጉዳይ ይግበኛ ወደፊት ለማቅረብ የዳኝነት ከአምስት እስከ አስር ሚሊዮን ብር በአዲሱ ህግ ያስከፍላል።

በተቃራኒው መንግስት የዳኝነት ክፍያ ስለማይከፍል ተቃራኒ ወገን ለመጉዳት ግዙፍ ቁጥር ገምተው አቅርበዋል” በሚል የህግ ባለሙያው ሙያዊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኘው የማራ ማይነርስ ባለቤት የሆነው ወጣት ባለሀብት ኢንጂነር ብርሃነመስቀል ክንፈ፣ በክልሉ ባለስልጣናት ላይ ያጋለጠውን የሙስና ወንጀል ተከትሎ በግፍ ታስሮ በነበረበት በጎፋ ዞን ሳውላ ከተማ ማረሚያ ተቋም ውስጥ የግድያ ሙከራ ተፈጽሞበታል። ሴራውም በፖሊስ ክትትል ከሽፏል።

የግድያ ሙከራው፣ ከወንጀል ታሪክ ጋር በቅጽል ስሙ “ሻፎ” የተባለ የዕድሜ ልክ እስረኛን ከዲላ ማረሚያ ቤት በማምጣት የተፈጸመ ሲሆን፣ የህግ ባለሙያዎችም በባለሀብቱ ላይ የተመሰረተው ክስ ህገወጥ እና የፖለቲካ የበቀል እርምጃ መሆኑን ገልጸዋል። ይህ ክስተት በክልሉ የህግ እና የፍትህ ስርዓት ላይ የሚታዩ ብልሹ አሰራሮችን በግልፅ የሚያሳይ መሆኑን በርካቶች በመግለፅ ላይ ይገኛሉ።