1759065591813

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከሚገኙ ብሔረሰቦች አንዱ የሆነው የቁጫ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ የሆነው “ዎዳላ ጋዜ” በዓል በተለያዩ መርሃግብሮች በድምቀት እየተከበረ መሆኑ ተገልጿል።

በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የቁጫ ተወላጆች በሀገር ፍቅር ቴአትር ባዘጋጁት መርሃ ግብር፣ በዓሉን በከፍተኛ ድምቀት አክብረዋል።

የቁጫን የምርጫ ክልል ወክለው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት ረ/ፕሮፌሰር ገነነ ገደቦ፣ “ዎዳላ ጋዜ” የቁጫ ሕዝብ ካሉት ታላላቅ ሃብቶች መካከል አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።

በዓሉን አስመልክቶ ጥናቶች ሊከናወኑ እንደሚገባና ባህላዊ ይዘቱ ተጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፍ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የቁጫ ብሔረሰብ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኝ ሲሆን፣ ከኦሞዓዊ ቋንቋ ቤተሰብ የሚመደብ ነው። የታሪክ አዋቂዎችና ሰነዶች እንደሚያረጋግጡት፣ ብሔረሰቡ የራሱ የሆነ የዘመን አቆጣጠር ያለው ከመሆኑም ባሻገር የተለያዩ ባህሎችና ሥርዓቶች ከጥንት ጀምሮ አሉት።

“ዎዳላ ጋዜ” ከቅድመ ዝግጅት ጀምሮ እስከ ፍጻሜው ድረስ በርካታ ተግባራት የሚከናወኑበት በዓል ሲሆን ከእነዚህም መካከል የባህላዊ ምግብና መጠጥ ዝግጅት፣ የሀብት አሰባሰብ፣ የእርቅና የይቅር መባባል፣ እንዲሁም ለሌለው ማካፈል ይገኙበታል።

ሆኖም ከሁሉም የሚለየውና የበዓሉ ዋና ተግባር ተደርጎ የሚወሰደው፣ አዲሱ ዓመት ከመግባቱ በፊት ያዘነን ቤተሰብ የማፅናናት ልዩ ሥርዓት ነው።

በዚህ ሥርዓት መሰረት፣ በአሮጌው ዓመት መጀመሪያ፣ መሃል ወይም መጨረሻ ሰው የሞተበት ቤተሰብ በሰፈሩ ካለ፣ በአዲስ መልክ ለቅሶው ይደረስና ቤተሰቡ ዳግም ሀዘን ውስጥ እንዳይገባ ወይም የነበረበትን የሐዘን ድባብ ሙሉ ለሙሉ እንዲረሳ ይደረጋል።

የቁጫ ሕዝብ ይህን በዓል እንደ ሕዝብ መኖር ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ሲያከብረው የቆየ ቢሆንም፣ በተለያዩ ምክንያቶች በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደብዘዝ የማለት ሁኔታ ላይ እንደነበር ተገልጿል። ይሁን እንጂ፣ ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ በዓሉ በድምቀትና በደመቀ ሁኔታ እየተከበረ መሆኑ ተጠቁሟል።

የዘንድሮው “ዎዳላ ጋዜ” በዓልም፣ በተለያዩ እንግዶች፣ የኃይማኖት መሪዎች፣ የተለያዩ ብሔርና ብሔረሰቦች ተወካዮችና የቁጫ ብሔረሰብ ተወላጆች በተገኙበት በአዲስ አበባ በሀገር ፍቅር ትያትር ቤት በልዩ ሁኔታ በድምቀት እየተከበረ መሆኑን ምንጮች አመላክተዋል።