GridArt_20250930_150249208

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በመልካም አስተዳደር ጉድለት፣ በሙስናና በሰብዓዊ መብት ጥሰት ምክንያት ህዝቡ ወደ ከፋ “ኩስምና” ውስጥ መግባቱን የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገልጿል።

በጉዳዩ ዙሪያ የጂንካና የዎላይታ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን፥ ክልሉ ከህጋዊ አሰራር ባፈነገጠ ሁኔታ በቁዘማ እና በባይተዋርነት እየተገዛ በመሆኑ ልዕልና የማጣትና በማሽቆልቆል (ኩስምና) ውስጥ” ይገኛል ሲሉ አስተያየታቸውን ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ( WT Media ) ሰጥተዋል።

በቅርቡ በተካሄደው የፓርቲ አመራር ሂስ-ግለ ሂስ መድረክ በተሰጡ ጥቆማዎች መሠረት በተዋቀረው የኢንስፔክሽን ቡድን ሪፖርት፣ በክልሉ መዋቅሮች ውስጥ በርካታ ዘርፈ ብዙ ብልሽቶችና የጥቅም ትስስሮች (ኔትወርክ) መገኘታቸው ተረጋግጧል።

በዋናነት አመራሩ የጥቅም ትስስሩን በመጠቀም፣ ከመመሪያ ውጪ የመንግሥትን በጀት አስተዳደር ሳይከተል፣ የሚሰበሰበው ገቢ ወደ መንግሥት ቋት እንዳይገባ በማድረግ ለግል ጥቅማቸው ያዋሉ አመራሮች መኖራቸው ታውቋል።

በተጨማሪም በአመራሩ ሥርዓት ጉድለት ምክንያት፣ የተለያዩ የጥቅም ትስስሮች በገጠርና በከተማ መሬት እንዲሁም በኢንቨስትመንት ሽፋን የራሳቸውን የጥቅም መረብ የዘረጉ ብልሹ አመራሮች መኖራቸው በሪፖርቱ ተመላክቷል።

ዘገባው እንደሚያመለክተው፣ የክልሉን ኢኮኖሚ የበላይነት የሚመራው በጥቅም ትስስር የተደራጀ ቡድን ጠቅልሎ ቁጥጥር ሥር ያደረገ ሲሆን፣ ጠንካራ ተወዳዳሪ የሆኑ ባለሀብቶችን፣ በተለይም የዎላይታ ባለሀብቶችን፣ በውሸት ክስ በመመስረት ሀብታቸውን ይዘርፋል።

ለዚህም ዋቢ ተደርጎ የቀረበው በጎፋ ሳውላ ማረሚያ ተቋም ያለ ፍርድ በእስር ላይ የሚገኘው ወጣቱ የዎላይታ ባለሀብት ኢንጂነር ብርሃነመስቀል ክንፈ ሲሆን የክልሉ ዜጎች እስከ ከፍተኛ ባለሀብቶች ድረስ በደረሰው በደል ሳቢያ ከፍተኛ ቅሬታ እያሰሙ ይገኛሉ።

በሌላ በኩል በትምህርት ዝግጅት የላቁና የሕዝቡን ተስፋ የጣለባቸውን የፊት አመራሮች ጭምር ያለ በቂ ግምገማ ከሥልጣን በማዞር የጥቅም ቡድኑን መቆጣጠር ማመቻቸቱ ተጠቁሟል።

የሰብዓዊ ቀውስ እና የሕዝብ እንቢተኝነት ስጋት
በክልሉ ያለው የኢኮኖሚ ውድቀት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ተከትሎ፣ የከተሞች ዜጎች ለከፍተኛ ችግር ተዳርገዋል።

የመንግሥት ሠራተኞች የደመወዝ ክፍያ መዘግየትን ተከትሎ የክልሉን መንግሥት በፍርድ ቤት እየከሰሱ ቢሆንም፣ የክልሉ ፍርድ ቤቶች ለርዕሰ መስተዳድሩ “ታዛዥ” በመሆናቸው ሠራተኞቹ በፍትህ እጦት እየተሰቃዩ ይገኛሉ።

ህዝቡ “ከክልሉ ዙሪያ ገቢው ጨለማ የሆነ እና ከለውጡ መንግሥት የብልጽግና ቱርፋት ጭላንጭል እንኳን ተነፍጎ” የሚገኝ በመሆኑ፣ በክልሉ የሕዝብ እንቢተኝነት በየትኛውም ሰዓት ሊፈነዳ እንደሚችል ስጋት ተጥሏል።

የፐብሊክ ሰርቪስ ሠራተኞች እና ምሁራን፣ ክልሉ አደገኛ ሁኔታ ላይ በመሆኑ የፌዴራል መንግሥት ብልጽግና ፓርቲ በክልሉ ጣልቃ ገብቶ አሰራሩን ጠብቆ የፖለቲካ እርምጃ አመራሩ ላይ እንዲወሰድ ጥያቄ አቅርበዋል።

ዘገባው እንዳመለከተው፣ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ክልሉን ወዳልተፈለገ ሁኔታ እየወሰዱት በመሆኑ፣ በቀጣይ የፌዴራሉ ጣልቃ ገብነትና እርምጃ ወሳኝ መሆኑን ያመለክታል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ቀደም ሲል በዘይሴና ቁጫ ሕዝብ ላይ ባደረሱት ከፍተኛ ሰብዓዊ መብት ጥሰትና አስተዳደራዊ በደል ምክንያት ብልፅግና ፓርቲ እንዲሸነፍ ያደረጉትን ተመሳሳይ ሽንፈት በክልል ደረጃ ለመድገም መቃረባቸውም ተጠቁሟል።

በዚህ ሁኔታ ህዝቡ የብልፅግና መንግሥት በ2018 ሀገር አቀፍ ምርጫ ከክልሉ ሕዝብ ምን ውጤት ይጠብቃል የሚለውን ጥያቄ ከወዲሁ በተለያዩ ሁኔታዎች በመግለፅ ላይ ይገኛል።

ማሳሰቢያ፦ WT MEDIA በሀገሪቱ በተለይም ደቡብ ኢትዮጵያ አከባቢ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት በማያገኙ ለተጮቆኑ ህብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥተው እውነትንና ሀቅን መሠረት አድርገው የሚሰራ ስለሆነ የመረጃ ሰጪ ግለሰቦች ምስጥርና ደህንነት በተጠበቀ ሁኔታ የደረሱን መረጃዎችን መልሰን አጣርተን ለህዝብና የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዲሰጡበት በታማኝነት ይፋ እናደርጋለን።

ለማህበረሰቡ ከፍተኛ ፋይዳ ባላቸው ህዝብ ጉዳዮች ላይ ሀሳባችሁን ለማካፈል ለሚፈልጉ ሁሉ ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ሆነን እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ሰብዓዊነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚፀባረቅበት በሌሎች ትላልቅ ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለ ዘውትር አብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው!! እኛ ዘውትር የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን !!
Voice of Marginalized Community – WT Media