GridArt_20251006_183233683

ተጨማሪ #ሰበርዜና

የጎፋ ተጎጂዎች እርዳታ ገንዘብ የዘረፉ ሦስት አመራር ተጠርጣሪዎችን የፌዴራል ደህንነቶች በቁጥጥር ሥር አዋሉ

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በጎፋ ዞን የመሬት ናዳ አደጋ ለተፈናቀሉ ወገኖች የተሰበሰበውን የእርዳታ ገንዘብ ለማሸሽ የተደረገው ከፍተኛ የሙስና ሙከራ መጋለጡን ተከትሎ፣ የፌዴራል ደህንነት አካላት ሦስት ቁልፍ ተጠርጣሪዎችን ማምሻውን በቁጥጥር ሥር ማዋላቸውን ለ WT Media ከስፍራው የደረሰው መረጃ ያረጋግጣል።

ከአንድ ሰዓት በፊት የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ (WT Media) እንደዘገበው፣ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ እና የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዳግማዊ አየለ የተባሉ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ከጎፋ ዞን ፋይናንስ መምሪያ ኃላፊ አቶ ተክለማርያም በቀሌ ጋር በመሆን ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ ለማሸሽ ከደላላ ጋር ተመሳጥረው ነበር።

በዚህም የፌዴራል ደህንነቶች እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በጋራ በመተባበር ደላላውን በአዲስአበባ ከተማ ከባንክ ገንዘቡን ለማውጣት በሚሞክርበት ወቅት በቁጥጥር ስር በማዋል ከአራት ቀን በላይ በሕግ ጥላ ስር አቆይተዋል።

የጎፋ ዞን ፋይናንስ መምሪያ ኃላፊ አቶ ተክለማርያም በቀሌ የባንክ ቼክ ማሻርያ ደብዳቤ በማዘጋጀት ወደ ሳውላ ንግድ ባንክ የማጭበርበር ሥራ ሲሰሩ በፌዴራል ደህንነቶች እጅ ላይ ደርሶባቸዋል።

ጉዳዩ ለሕዝብ እንዳይደርስና ቁጣ እንዳይቀሰቀስ ተፈርቶ ታፍኖ መቆየቱ ተገልጿል፤ ሆኖም WT Media በተጨባጭ የሰነድ ማስረጃዎችን ባደረገው ብርቱ ጥረት ያገኘውን ከሰዓት በፊት መዘገቡ ይታወሳል።

ከዚህ ዘገባ በኃላ አሁን በደረሰን መረጃ መሠረት ተጨማሪ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር የማዋል ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን አሁን አመሻሽ በሳውላ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ በሕግ ቁጥጥር ሥር የዋሉት ግለሰቦች፡-

 አቶ ተክለማርያም በቀሌ (የጎፋ ዞን ፋይናንስ መምሪያ ኃላፊ)
 አቶ ማርቆስ መለሰ (የጎፋ ዞን አደጋ ሥጋት መምሪያ ም/ኃላፊ)
 ወ/ሮ አበበች ታዬ (የባንክ ቼክ አዘጋጅ)

በተጨማሪም፣ ገንዘብ የማዛወር ሥራውን በቀጥታ ሲያመቻቹ የነበሩ ሁለት ቁልፍ ግለሰቦች ላይ የፌዴራል ደህንነት ጥልቅ ምርመራ ጀምሯል። እነርሱም፦

 አቶ ነፃነት ገመዳ (የወንዶ ኩባንያ ሠራተኛ እና ደላላ)
 አቶ ጋንታ ጋምኣ (የክልሉ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን እና የአቶ ጥላሁን ከበደ የቅርብ ሰው)

አቶ ጋንታ ጋምኣ በክልል ማዕከል የተሰበሰበ 48 ሚሊዮን ብር በአቶ ነፃነት ገመዳ ደላላነት በተለያዩ ሲስተሞች ወደ ነጋዴዎች አካውንት እንዲዛወር የማድረግ ሥራ መሥራታቸው የሚያረጋግጥ መረጃ በመገኘቱ ክትትል እየተደረገባቸው ነው።

የሕዝብ ጥያቄ፡ ዋናዎቹ ተጠያቂዎችስ?
ይህ የማጭበርበር ሙከራ፣ የክልሉ አመራሮች ቀደም ሲል ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆን የእርዳታ ሀብት ለተጎጂዎች ሳይደርስ መመዝበሩን በተመለከተ WT Media ከወራት በፊት የዘገበውን ስጋት የሚያጠናክር ነው።

በአሁኑ ሰዓት አቶ ተክለማርያም በቀሌን ከሕግ ለማሸሽና ለመሰወር በጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ እና በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር በኩል ከፍተኛ እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል።

ይህንን ሁኔታ የተመለከቱ የክልሉን ፖለቲካ ተንታኞች፣ ሙከራው በፌዴራል መጋለጡን ሲያደንቁ፣ ዋናዎቹ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድርና ከፍተኛ አመራሮች ተጠያቂነት ሊሰፍን ይገባል የሚል ጥያቄ አቅርበዋል።

ለዚህም የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ በመግባት በወንጀል አድራጊዎች ላይ እርምጃ መውሰድ አለበት የሚል ጥሪ ቀርቧል።

የሕዝብ ሀብት በግልጽ እየተዘረፈ ባለበትና በአደጋው የተጎዱ ወገኖች አሁንም በረሀብና በችግር እየተሰቃዩ ባሉበት ሁኔታ፣ አመራሩ በሕዝብ ለቅሶና በሰው ደም የመነገድ ተግባር ውስጥ መግባቱ “የዘመናችን ነውረኛ ተግባር” መሆኑ ተገልጿል።

ማሳሰቢያ፦ WT MEDIA በሀገሪቱ በተለይም ደቡብ ኢትዮጵያ አከባቢ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት በማያገኙ ለተጮቆኑ ህብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥተው እውነትንና ሀቅን መሠረት አድርገው የሚሰራ ስለሆነ የመረጃ ሰጪ ግለሰቦች ምስጥርና ደህንነት በተጠበቀ ሁኔታ የደረሱን መረጃዎችን መልሰን አጣርተን ለህዝብና የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዲሰጡበት በታማኝነት ይፋ እናደርጋለን።

ለማህበረሰቡ ከፍተኛ ፋይዳ ባላቸው ህዝብ ጉዳዮች ላይ ሀሳባችሁን ለማካፈል ለሚፈልጉ ሁሉ ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ሆነን እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ሰብዓዊነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚፀባረቅበት በሌሎች ትላልቅ ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለ ዘውትር አብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው!! እኛ ዘውትር የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን !!
Voice of Marginalized Community – WT Media