የጋሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር መታሰር: የፕሬዝዳንቱ ኢ-ፍትሐዊ አሰራር እና የሙስና ቅሌት
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ በዘፈቀደ የዜጎች እስርና በሙስና የተጨማለቀ ልማት ሲያካሂዱ በሌሎች ላይ ኢፍትሐዊ አሰራር እየፈጸሙ ነው የሚለውን አቋም በግልጽ በመቃወም የነበሩት የጋሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ቡንካሼ ሀንጌ በትናንትናው ዕለት በአርባ ምንጭ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ መታሰራቸውን ለ WT Media የደረሰው መረጃ ያመለክታል።
ይህ የእስር እርምጃ የመጣው በክልሉ ውስጥ “በርካቶች ያለ ሕጋዊ አሠራር ሰብዓዊ መብት ተጥሶ በጋሞ ዞን ታስረው የሚገኙ” ሲሆን፣ “ለፍትሕ የሚጮኹም እየታሰሩ ነው” የሚል ስጋት በሰፋት በተነሳበት ወቅት ነው።
ከክልሉ የተውጣጡ ምሁራን ለWT ሚዲያ በሰጡት አስተያየት፣ አቶ ጥላሁን ከበደ የራሳቸውን ማንነት በመደበቅ እና ከሥልጣን የመውረድ ስጋትን ለመቀነስ ሲሉ፣ የራሱ ቡድንና ጥቅም ባለበት አርባ ምንጭ ከተማ ልማት ላይ ብቻ ትኩረት በማድረግ ሌሎች መዋቅሮችን መርሳት ትልቅ ኃላፊነትን መዘንጋት ነው ሲሉ ይከሳሉ።
ባለፉት ሁለት ዓመታት የክልሉ ሀብት በአብዛኛው ወደ አርባ ምንጭ ከተማ ልማት እንደተዘዋወረና በልማት ስም ከፍተኛ ገንዘብ በጥቂት አመራሮችና ግለሰቦች እጅ መግባቱ ተገልጿል።
ሌላው ቀርቶ የክልሉ መዋቅሮች ለመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ ለመክፈል በሚቸገሩበት ጊዜ በአርባ ምንጭ ከተማ ላይ ከፍተኛ የመዋለ ንዋይ ፍሰት ታይቷል።
ምሁራኑ እንዳስረዱት፣ አቶ ጥላሁን ከበደ አርባ ምንጭን ብቻ ትኩረት ያደረጉበት ምክንያት “በያንዳንዱ ፕሮጀክት ላይ ከፍተኛ ጥቅም ትስስር በመፍጠር በግንባታ ሰበብ ለግሉ ገንዘብ ለመመዝበር እንዲመቸው እና አርባ ምንጭ ከተማ ውስጥ የረጅም ጊዜ የጥቅም ወዳጅ የሆኑ ግለሰቦችን ፍላጎት ለማሳካት” ነው።
ርዕሰ መስተዳድሩ ለዚህ የምዝበራ ዓላማ የሚጠቀሙት ታማኝ ተላላኪ አመራሮችን በመሾም፣ ያለ ጨረታ ለምስጢር ላደራጀው ኮንትራክተሮች ፕሮጀክቶችን በመስጠት እና የሕዝብ ተቋም የሆነውን ጋሞ ልማት ማህበርን እንደ ጭምብል በመጠቀም እንደሆነ ተብራርቷል።
በአቶ ጥላሁን ከበደ ኢ-ፍትሐዊ አሠራር ምክንያት፣ ሌሎች የክልሉ ዞኖች ከልማት እንዲገለሉ ተደርገዋል።
በጌዴኦ፣ በጎፋ፣ በዎላይታ እና በኮንሶ ዞኖች የልማት ፕሮጀክቶች ተከልክለዋል፣ የጨረታ ሂደቶች ተስተጓጉለዋል፣ እንዲሁም ከሌሎች ብሔረሰቦች የተወጣጡ ኮንትራክተሮች ከሥራ ታግደዋል ወይም ታስረዋል።
በጋሞ ዞን ውስጥ በሚገኙ እንደ ዛይሴ፣ ቁጫ፣ ካምባ፣ ጨንቻ እና ሌሎች ቦታዎች የሕዝብ መሠረታዊ ልማት ጥያቄዎች ተነፍገው፣ ዜጎች በመንገድ፣ በንፁህ መጠጥ ውሃ እንዲሁም የጤና ተቋማት እጦት እየተሰቃዩ ሲሆን፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ጭምር እየደረሰባቸው ነው።
አቶ ጥላሁን ከበደ ይህንን የሙስና ዓላማ ለማሳካት በአካባቢው የሚገኙ ሕዝቦችን የሚያባላ አጀንዳ መፍጠርን ሥራዬ ብለው እንደያዙት ምሁራኑ አስታውሰዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ነዋሪዎችና ወጣቶች ለፍትሕ እና እኩል ልማት መብታቸው እንዲታገሉ ጥሪ የቀረበ ሲሆን፣ የሚመለከታቸው አካላት በተለይም የፌዴራል መንግሥት በክልሉ እየተስተዋለ ያለውን ኢፍትሐዊነት፣ ብልሹ አሠራሮችና ሌብነት ሕዝብን ከመንግሥት ወደ መነጠል ደረጃ እየሸጋገረ በመሆኑ አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጥበት ተጠይቋል።
ማሳሰቢያ፦ WT MEDIA በሀገሪቱ በተለይም ደቡብ ኢትዮጵያ አከባቢ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት በማያገኙ ለተጮቆኑ ህብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥተው እውነትንና ሀቅን መሠረት አድርገው የሚሰራ ስለሆነ የመረጃ ሰጪ ግለሰቦች ምስጥርና ደህንነት በተጠበቀ ሁኔታ የደረሱን መረጃዎችን መልሰን አጣርተን ለህዝብና የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዲሰጡበት በታማኝነት ይፋ እናደርጋለን።
ለማህበረሰቡ ከፍተኛ ፋይዳ ባላቸው ህዝብ ጉዳዮች ላይ ሀሳባችሁን ለማካፈል ለሚፈልጉ ሁሉ ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ሆነን እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ሰብዓዊነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚፀባረቅበት በሌሎች ትላልቅ ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለ ዘውትር አብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው!! እኛ ዘውትር የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን !!
Voice of Marginalized Community – WT Media