የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ለፌደራል መንግስት እምቢተኝነት ማሳየትን ተከትሎ የፌዴራል ፖሊሶች ትዕዛዙን ሳያፈፅሙ ተመለሱ
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠውን የእግድ ትዕዛዝ ለመቀበልና ለማስፈጸም ፈቃደኛ ባለመሆኑ፣ ትዕዛዙን በኃይል ለማስፈጸም ወደ ክልሉ የተላኩት የፌዴራል ፖሊስ ኮማንዶ አባላት ሳያስፈጽሙ ወደ ኋላ መመለሳቸው የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
የፌዴራል ፖሊስ ወደኋላ የመመለስ ውሳኔ
WT Media አሁን ባገኘው መረጃ መሠረት፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት ለመተባበር ፈቃደኛ ባለመሆኑ ምክንያት፣ የፌዴራል ፖሊስ አባላቱ ወደ መጡበት እንዲመለሱ ተወስኗል።
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደመላሽ ገብረሚካኤል ጉዳዩን ከፌዴራል መንግሥት ጋር ለመነጋገር እና በቀጣይ የሕግ ተፈጻሚነት ላይ ለመወሰን ይህንን ውሳኔ ማሳለፋቸው ተገልጿል።
የፌዴራል ፖሊስ አባላቱ ወደተፈለገው የቦረዳ ወረዳ ሳይት እንዳይገቡ ተከልክለው ለሦስት ቀናት ያህል ዎላይታ ሶዶ ከተማ ላይ ተቀምጠው መንገላታት እንደገጠማቸው ይታወቃል።
የመረጃ ምንጮች ይህ የፌዴራል ፖሊስ መደናቀፍ አዲስ አለመሆኑንና ከዚህ ቀደምም በተመሳሳይ መልኩ ሶስት ጊዜ ተመላልሶ የክልሉ መንግሥት እምቢተኛ ሆኖ መመለሱን አስረድተዋል።
የክልሉ መንግሥት ይህንን ሕግ የማስፈጸም ፈቃደኛ አለመሆን ያሳየው፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ ልደታ ምድብ 6ኛ ንግድ ይግባኝ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 337812 የሰጠው ግልጽ የእግድ ትዕዛዝ እያለ ነው። ትዕዛዙ የተሰጠው ከማራ ማይነርስ ባለቤት አቶ ብርሃነመስቀል ክንፈ ጋር በተያያዘ ነው።
ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ባለሀብቱ በክልሉ ውኃና ማዕድን ቢሮ ውስጥ የሚፈጸመውን ብልሽት በማጋለጣቸው ቂም በመያዝ፣ የክልሉን የፍትህ ተቋማት (ም/ኮሚሽነር ጉራማይሌን ጨምሮ) በመጠቀም፣ ጉዳዩ በፍርድ ቤት ክርክር ላይ እያለ ባለሀብቱን በሐሰት ክስ አስረው እያሰቃዩ ይገኛሉ።
ባለሀብቱ ከታሰሩ በኋላ፣ በርዕሰ መስተዳድሩ ቀጥተኛ ትዕዛዝ በክስ ሂደት ላይ ባለው የማዕድን ቦታ ላይ ከአምስት በላይ ድርጅቶች ገብተው እየሰሩ እንደሚገኙ የፌዴራል ፖሊስ ከዚህ ቀደም አረጋግጦ ነበር።
ይህ የፌዴራል ፖሊሶች መንገላታት “በክልሉ የሕግ የበላይነት እንደሌለ ለማረጋገጥ አንዱ ማስረጃ ነው” ያሉት የመረጃ ምንጮች፣ በአንባገነን እና ሙሰኛ መሪ እየተሰቃየ ያለው ክልሉ የፌዴራል መንግሥትን ልዩ ትኩረት ሊያገኝ እንደሚገባ አሳስበዋል።
WT Media የፌዴራል መንግሥት በቀጣይ በሚወስነው ውሳኔ ዙሪያ ዝርዝር መረጃዎችን ማቅረቡን ይቀጥላል።