GridArt_20251015_162340082

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን በአርባ ምንጭ ከተማ የፓርቲ አመራሮችና አባላት በፀጥታ አካላት እየታሰሩና ሰብዓዊ መብታቸው ተጥሰው እየተደበደቡ ነው ሲል 11 ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ያሰባሰበው ‘የሰላም ጥምረት’ አስታውቋል።

የጥምረቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዳሮት ጉምአ ለዶቼ ቬለ (DW) እንደተናገሩት፣ የጋሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ጋዴፓ) ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ቡንካሾ ሀንጌን ጨምሮ አንድ አመራርና ሁለት አባላት ከመስከረም አጋማሽ ጀምሮ በተለያዩ ቀናት በዘፈቀደ ተይዘው በእሥር ላይ ይገኛሉ።

አባላቱ የታሰሩት ‘የፍርድ ቤት መጥሪያ ባልተያዘበትና በሌሊት ጭምር በመኖሪያ ቤታቸው በመግባት’ መሆኑን አቶ ዳሮት ገልጸዋል።

በተለይ አቶ ቡንካሾ ሀንጌ ላይ የፀጥታ አባላት ድብደባ በመፈጸማቸው ለአካል ጉዳት እንደተዳረጉ ሰብሳቢው ጠቁመዋል።

‘በፓርቲ አባልነት ሳይሆን በወንጀል ተጠርጥረው ነው’ በተቃራኒው፣ የአርባ ምንጭ ከተማ ፖሊስ አባላቱ የተያዙት በፖለቲካዊ ምክንያት ሳይሆን በወንጀል በመጠረጠራቸው መሆኑን አስታውቋል።

የከተማው ፖሊስ ዋና አዛዥ ኮማንደር ክበበው አዳል ለዶቼ ቬለ እንደተናገሩት፣ ተጠርጣሪዎቹ “በከተማው ነዋሪዎች መካከል ግጭት ለመቀስቀስ እንቅስቃሴ በማድረጋቸው” ሕግን በተከተለ መንገድ ተይዘው ምርመራ እየተጣራባቸው ነው።

በፓርቲ አባላቱ ላይ አካላዊ ድብደባ ተፈጽሟል የሚለውን አቤቱታ ኮማንደር ክበበው “ፈጽሞ ሐሰት ነው” ሲሉ አጣጥለውታል። ማንኛውም ሰው መጥቶ ተጠርጣሪዎቹን ማየት እንደሚችልም አስረድተዋል።

“አርባ ምንጭ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ሐሳባቸውን በነጻነት የሚገልጹበት እንጂ ሰላማዊ ፖለቲካ ውስጥ በመሳተፋቸው የሚታሰሩበት ሁኔታ የለም” ሲሉም አክለዋል፤ የእሥሩ ምክንያትም ለፀጥታ መደፍረስና ለግጭት ምክንያት ሊሆኑ በሚችሉ ድርጊቶች ላይ ተሳትፈው በመገኘታቸው ነው” ብለዋል።

ይህ በፓርቲ አመራሮች ላይ እየተፈጸመ ነው የተባለው ድርጊት፣ WT Media (ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ) በተደጋጋሚ የዘገበውን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አመራር በሴራ የተደራጀ መዋቅርን በመጠቀም የፖለቲካ ምህዳሩን የማጥበብና የሕግ የበላይነትን የመናድ አካሄድ የሚያጠናክር ነው።

ክልሉን የሚመሩት አቶ ጥላሁን ከበደ መዋቅሩን በሴራ በማደራጀት፣ ጠንካራ የአካባቢ ልጆችን በማስጠቃትና ክልሉን እንደ ግል ንብረት በመጠቀም ፍትሕ የሚጓደልበት ክልል መሆኑን WT Media ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ መዘገቡ ይታወቃል።

በክልሉ በቅርቡ በሕገወጥ ድርጊት የተጠረጠሩ የመንግሥት ባለሥልጣናት ላይ ሳይሆን በልማታዊ ባለሀብት (ኢንጂነር ብርሃነመስቀል ክንፈ) ላይ 12 ቢሊዮን ብር የሙስና ክስ መመስረቱ፣ የእርዳታ ገንዘብ ዘረፋ ሙከራ መደረጉ እና የመንግሥት ሥራ እንቅስቃሴ መቆሙ፣ ክልሉ የሕግ የበላይነት ተናግሮ ወደ ውጥንቅጥ መውረዱን ያሳያል ተብሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮች ላይ የፖለቲካ እስርና ድብደባ መፈጸሙ መገለጹ፣ የክልሉ አመራር ሕገወጥነትንና ፖለቲካዊ ትርምስን ማስፈን መፈለጉን የሚያመላክት ነው ሲል የአከባቢውን ፖለቲካ እንቅስቃሴ በቅርበት የሚከታተሉ መግለፃቸውን መወገባችን ይታወሳል።

ማሳሰቢያ፦ WT MEDIA በሀገሪቱ በተለይም ደቡብ ኢትዮጵያ አከባቢ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት በማያገኙ ለተጮቆኑ ህብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥተው እውነትንና ሀቅን መሠረት አድርገው የሚሰራ ስለሆነ የመረጃ ሰጪ ግለሰቦች ምስጥርና ደህንነት በተጠበቀ ሁኔታ የደረሱን መረጃዎችን መልሰን አጣርተን ለህዝብና የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዲሰጡበት በታማኝነት ይፋ እናደርጋለን።

ለማህበረሰቡ ከፍተኛ ፋይዳ ባላቸው ህዝብ ጉዳዮች ላይ ሀሳባችሁን ለማካፈል ለሚፈልጉ ሁሉ ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ሆነን እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ሰብዓዊነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚፀባረቅበት በሌሎች ትላልቅ ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለ ዘውትር አብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው!! እኛ ዘውትር የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን !!
Voice of Marginalized Community – WT Media