GridArt_20251015_182659696

በዎላይታ ዞን የወባ በሽታ ወረርሽኝ አስጊ ደረጃ በመድረሱ ሕዝቡን ዋጋ እያስከፈለ ነው ተብሏል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በዎላይታ ዞን፣ የዎላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ በሁሉም አካባቢ ማለት በሚቻል ሁኔታ የወባ በሽታ ወረርሽኝ መከሰቱና አስጊ ደረጃ ላይ መድረሱን WT Media ከስፍራው ባገኘው መረጃ አረጋግጧል።

መረጃው እንደሚያመለክተው፣ እያንዳንዱ ቤተሰብ ደረጃ ይህ በሽታ ያላጠቃው የለም ማለት በሚቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል።

በወባ በሽታ ታመው አልጋ ይዘው የሚገኙ ሰዎች ቁጥር ከዞኑ ሕዝብ አብዛኛውን የሚይዝ ሲሆን፣ ይህ አሳሳቢ ሁኔታ ከጤና ተቋማት የሚወጡ መረጃዎች ያረጋግጣሉ።

የመረጃ ምንጮቻችን እንደገለጹት፣ ለዚህ አስጊ የወባ ወረርሽኝ መከሰት ዋናው መንስኤ ከመከላከል ረገድ በጊዜ ያልተሠሩ ሥራዎች ናቸው።

በተጨማሪም አስቀድሞ ቤት ለቤት የወባ ኬሚካል ርጭት አለመካሄዱ፣ የአልጋ አጎበር ሥርጭት በበቂ ሁኔታ አለመኖሩ፣ ከፌዴራል እስከ ወረዳ ያለው የጤና ተቋማት መዋቅር በጊዜ በሽታው የመከላከል ሥራ ላይ ትኩረት ሰጥቶ አለመሥራቱ ሕዝቡን ዋጋ እያስከፈለ መሆኑን የመረጃ ምንጮቻችን አብራርተዋል።

በዚህም በገጠርም ሆነ በከተማ በተመሳሳይ ሁኔታ የተከሰተው ይህ ወረርሽኝ፣ በሕዝቡ ጤንነትና ኢኮኖሚ ላይ ከባድ ጫና እየፈጠረ ነው።

በበሽታው የተያዘው ሰው ለሕክምና ብዙ ብር እያወጣ ቢገኝም፣ ከበሽታው ነፃ መውጣት ባለመቻሉ ኢኮኖሚውንና የዕለት ተዕለት ኑሮውን እየተፈታተነው መሆኑ ተረጋግጧል።

የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ (WT Media) ከነዋሪዎችና ከጤና ተቋማት ያገኘው ተጨማሪ መረጃዎች እንደሚመለከተው ወረርሽኙ የተለመደውን ኳርተም የተባለውን የወባ ዝርያ የተላመደ መሆኑና፣ በየመንግሥት ጤና ተቋማት የመድኃኒት አቅርቦት ውስን በመሆኑ ሕዝቡ ተቸግሯል።

በወባ በሽታ የተያዙ ሰዎች ከ90% በላይ መድኃኒት ከግል ፋርማሲ በውድ ዋጋ ገዝተው እየተጠቀሙ ነው። ሆኖም ተጎጂዎች የመድኃኒት ጥራትና ፈዋሽነት ምንም እንዳልሆነ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ከዚህ በሽታ ጋር ተያይዞ የሰው ሕይወት ወደመጥፋት ደረጃ እየደረሰ እንደሚገኝ ከጤና ተቋማት ያገኘነው መረጃ ያረጋግጣል።

ተጎጂዎቹና የጤና ተቋማት አደጋው ከቁጥጥር ውጭ እንዳይወጣ በመስጋት ለመንግሥት ጥሪ አቅርበዋል።

በጥቅምት 5/2018 ዓ.ም. በተደረገው የፓርቲ ውይይት በወባ በሽታ ዙሪያ የቀረበው ሠነድ የችግሩን አሳሳቢነት ያሳያል።

መንግሥት በአፋጣኝና በአግባቡ መድኃኒት አቅርቦት፣ የአጎበር ሥርጭት እንዲሁም ኬሚካል ርጭት በጊዜ ካላካሄደ፣ ሕዝቡ በአደጋ ውስጥ እንዳለ መረጃ ሰጭዎቹ አስጠንቅቀዋል።

በመሆኑም መንግሥት ትኩረት ለሕዝቡ ጤና ይስጥ! በማለት ጥሪ አቅርበዋል።

ማሳሰቢያ፦ WT MEDIA በሀገሪቱ በተለይም ደቡብ ኢትዮጵያ አከባቢ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት በማያገኙ ለተጮቆኑ ህብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥተው እውነትንና ሀቅን መሠረት አድርገው የሚሰራ ስለሆነ የመረጃ ሰጪ ግለሰቦች ምስጥርና ደህንነት በተጠበቀ ሁኔታ የደረሱን መረጃዎችን መልሰን አጣርተን ለህዝብና የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዲሰጡበት በታማኝነት ይፋ እናደርጋለን።

ለማህበረሰቡ ከፍተኛ ፋይዳ ባላቸው ህዝብ ጉዳዮች ላይ ሀሳባችሁን ለማካፈል ለሚፈልጉ ሁሉ ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ሆነን እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ሰብዓዊነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚፀባረቅበት በሌሎች ትላልቅ ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለ ዘውትር አብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው!! እኛ ዘውትር የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን !!
Voice of Marginalized Community – WT Media