GridArt_20251021_172356433

በጋሞ አርባምንጭ-ኮንሶ መንገድ ላይ የተፈጠረው የፀጥታ ችግር ተባብሶ መንገዱ ሙሉ በሙሉ በመዘጋቱ የንግድና ሌሎች እንቅስቃሴዎች መቋረጡ ተገልጿል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከጋሞ ዞን አርባ ምንጭ ወደ ኮንሶ በሚወስደው ዋና የመንገድ ክፍል ላይ ከፍተኛ የጸጥታ ችግር በመፈጠሩ፣ መንገዱ ሙሉ በሙሉ ከተዘጋ ዛሬ (ጥቅምት 11/2018 ዓ.ም.) ሦስተኛ ቀኑን መያዙን WT Media ከስፍራው ባገኘው መረጃ አረጋግጧል።

ከትናንት በስቲያ ማምሻው ጀምሮ በኤልጎ ከተማ አካባቢ በተነሳ ግጭት ምክንያት ወደ አካባቢው የሚጓዙ አሽከርካሪዎችና ተጓዦች በየቦታው ቆመው የንግድ እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ ተስተጓጉሏል።

በፀጥታ ምክንያት ተጓዦች መንገድ ላይ ቆሟል

መንገዱ በመዘጋቱ ምክንያት የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከፍተኛ ችግር ውስጥ ገብተዋል። ወደ አካባቢው እየተጓዙ የነበሩ ነጋዴዎች፣ ቱሪስቶችና ሌሎች መንገደኞችም ለእንግልት ተዳርገዋል።

በተጨማሪም የሚበላሹ አትክልቶችን የጫኑ የንግድ ተሽከርካሪዎች ለብልሽት እየተዳረጉ ሲሆን፣ ሌሎች የሕዝብ ትራንስፖርት ተሽከርካሪዎችና የአካባቢው ነዋሪዎችም ጉዟቸው በመቋረጡ ለችግር ተዳርገዋል።

የዓይን እማኞች፣ ተጓዦች እና አሽከርካሪዎች እንደሚሉት፣ መንገዱ መዘጋቱ የተፈጠረውን የጸጥታ አለመረጋጋት የሚያሳይ ሲሆን፣ ይህ የክልሉን አጠቃላይ መረጋጋት የሚያናጋ ድርጊት ነው።

በሌላ በኩል በተጨማሪም ይህ የመንገድ መዘጋት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እየተባባሰ የመጣውን የጸጥታ ሁኔታ የሚያሳይ ሲሆን፣ WT Media ትናንት (ጥቅምት 10/2018 ዓ.ም.) የዘገበው ዘገባ የችግሩን ምንጭ ያሳያል።

በጋሞ ዞን ውስጥ በዘይሴ ብሔረሰብ ላይ “የዘር ማጥፋት (Genocide) መስፈርትን ያሟላል” ተብሎ በተከሰሰበት አካባቢ፣ የክልሉ ልዩ ኃይል እና የጋሞ ዞን መደበኛ ፖሊስ ከአካባቢው አርሶ አደሮች ጋር ከፍተኛ ጦርነት ከፍተው ውጊያ ላይ መሆናቸውን የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ (WT Media) በትናንትናው ዕለት መዘገቡ ይታወሳል።

ይህ የዘይሴ ግጭትና የሌሎች አካባቢዎች የመንገድ መዘጋት፣ ክልሉ እውነተኛ አመራር አጥቶት በተለያዩ ጉዳዮች (የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ የሙስና ቅሌት፣ የውዝፍ ደመወዝ ጥያቄን ተከትሎ የሚደረግ እስር እና የወባ ወረርሽኝ) እየተሰቃየ መሆኑን ያመለክታል።

የፌዴራል መንግሥትና የክልሉ አመራር በአስቸኳይ ለዚህ አሳሳቢ የጸጥታና የመልካም አስተዳደር ችግር መፍትሔ እንዲሰጡ የንግዱ ማኅበረሰብና ተጓዦች ጥሪ አቅርበዋል።

ማሳሰቢያ፦ WT MEDIA በሀገሪቱ በተለይም ደቡብ ኢትዮጵያ አከባቢ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት በማያገኙ ለተጮቆኑ ህብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥተው እውነትንና ሀቅን መሠረት አድርገው የሚሰራ ስለሆነ የመረጃ ሰጪ ግለሰቦች ምስጥርና ደህንነት በተጠበቀ ሁኔታ የደረሱን መረጃዎችን መልሰን አጣርተን ለህዝብና የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዲሰጡበት በታማኝነት ይፋ እናደርጋለን።

ለማህበረሰቡ ከፍተኛ ፋይዳ ባላቸው ህዝብ ጉዳዮች ላይ ሀሳባችሁን ለማካፈል ለሚፈልጉ ሁሉ ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ሆነን እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ሰብዓዊነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚፀባረቅበት በሌሎች ትላልቅ ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለ ዘውትር አብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው!! እኛ ዘውትር የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን !!

Voice of Marginalized Community – WT Media