የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል “በከፍተኛ የሌብነት ሰንሰለት፣ በአመራር ውድቀት፣ በጎሰኛና ቤተሰባዊ የአመራር አደረጃጀትና በመንግስት ስራ መቆም ምክንያት አደጋ ተጋርጦበታል” ተብሏል።
በሌላ በኩል በዛሬው ዕለት በዎላይታ ሶዶ የተሰበሰበው የዚሁ የክልሉ አስፈጻሚ ካቢኔ አባላት የተሳተፉበት የመስተዳድር ምክርቤት ስብሰባ፤ የካቢኔ አካላት ሽግሽግና መልሶ የማደራጀት ሂደት እንዲሁም የተሿሚዎች መስፈርት ያለ ስምምነት መበተኑ የክልሉን አሳሳቢ የአመራር ቀውስ ያሳያል ተብሏል።
ለእነዚህ ችግሮች እንደማሳያነት፣ በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ጽ/ቤት ውስጥ ልክ ያልሆነ እና ጫፍ የወጣ የሌብነት ሰንሰለት መዘርጋቱን WT Media ከውስጥ ምንጮች ባገኘው አዲስ መረጃ አረጋግጧል።
የዚህ ዝርፊያ ሰንሰለት መሪዎች በዋናነት የአቶ ጥላሁን ከበደ የቅርብ ዘመዶች እና አብሮ አደጎች መሆናቸው ተጠቁሟል።
በካቢኔ ማዕረግ የርዕሰ መስተዳድሩ ፕሮቶኮል እና የመንግሥት ግንኙነት ኃላፊ አቶ ባህሩ ሙሉቱ (የርዕሰ መስተዳድሩ የወንድም ልጅ) በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ገንዘብ ያለምንም ስብሰባ ከአርባ ምንጭ ከተለያዩ ሆቴሎችና ሎጆች “የአልጋና የመስተንግዶ ወጭ ነው” በማለት በሕጋዊ ደረሰኝ ሽፋን እየዘረፉ መሆናቸው ተገልጧል።
ሹፌሮችን በመጠቀም ለግል ጉዳይ የሚውል ወጪ ‘በሥራ ማስኬጃ’ አስመስለው ከፋይናንስ ሕግ ውጭ በማድረግ ለደስታና ለሐዘን በማሰራጨት የመንግሥትን ሀብት እያባከኑ እንደሆነም የደረሱን ሰነዶችና መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ይህ መረጃ እንዳይወጣ በማለት ለረጅም ዓመታት የመረጃ እና ሪከርድ ሥራ ሂደት ባለሙያዎችንና አመራሮችን በግል ፍላጎት በማውጣት፣ በአዋጅ ታግዶ ባለበት ሁኔታ ሕገወጥ ቅጥርና ዝውውር ከጋሞ እና ጎፋ ዞን በማድረግ የመንግሥት ተቋማትን እያተራመሱ እንደሚገኙ የ WT Media ምንጮች አረጋግጧል።
በኮንትራት ተቀጣሪ የሆኑ ሠራተኞችን በማባረር እና መንግሥት የጨመረውን ደመወዝ በመከልከል የቀድሞ 1100 ብር ብቻ እየከፈሉ ጉልበት ብዝበዛ እያደረጉ ነው።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት በአንድ ብሔር እና “አብሮ አደግ” በሚል የተጠናከረ የቤተሰብ ስብስብ ውስጥ መሆኑ ተጋልጧል።
አቶ ዱፄ ታምሩ (የርዕሰ መስተዳድሩ የቅርብ ዘመድ) እና ዶ/ር ቦሻ ቦምቤ (የፕሬዝዳንቱ ልዩ አማካሪና አብሮ አደግ) የዚህ አደረጃጀት ዋነኛ አካል ናቸው።

የጋሞ ብሔርን ወክሎ በተመደቡ ካቢኔዎች ስር እንኳ የጋሞ ብሔር ተወላጆች ሳይሆኑ፣ ቤተሰባዊ አደረጃጀት በሕገወጥ ዝውውርና ቅጥር እየተደረገ ነው።
የክልሉ ከፍተኛ አመራር ከኃላፊነት ስራቸው ይልቅ በአዲስ መልክ ይፋ ይደረጋል የተባለውን ሹም ሽረት በማኅበራዊ ሚዲያ እየተጠባበቁ ተጠምደዋል።
የክልሉ አስፈፃሚ አካላት ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣው አዋጅ በምክር ቤት የጸደቀ ቢሆንም፣ ዕውቀትና ክህሎት ያላቸውን አመራር መልሶ የማደራጀት ሥራ በድጋሚ ለማክሸፍ ሙከራ እየተደረገ መሆኑ ከአንዳንድ ከፍተኛ አመራሮች ተቋውሞ እንዲገጥመው አድርጎታል።
ርዕሰ መስተዳድሩ ያቀረቧቸው አስፈፃሚ አካላት ተቀባይነት ባለማግኘታቸው፣ ዛሬ የተደረገው የካቢኔ ሽግሽግ ስብሰባ ያለስምምነት መበተኑን አሁን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

በአጠቃላይ 75 አመራሮች ከኃላፊነት ተነስተው ወደ ባለሙያነት ወይም ወደ መጡበት ዞኖች በምደባ እንደሚሄዱ WT Media አረጋግጧል።
የክልሉ ምክር ቤት ውሳኔዎች ተጥሰው፣ በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ አዲስ የተጠኑ ተቋማት አመራሮች ሹመት ተግባራዊ ባለመሆኑ ምክንያት፣ አብዛኛው የመንግሥት ሥራ እንቅስቃሴ ወደ መቆም መድረሱን ከስድስቱ የክልሉ ክላስተር ማዕከላት የተገኘ መረጃ ያሳያል።
በአብዛኛው ክላስተር ላይ የመደበኛ መንግሥት ሥራ እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ ሞቷል።
በአዋጅ በፈረሱ ተቋማት ላይ የመንግሥት በጀት እየተመደበ ሲሆን፣ አመራሮች በቀጣይ ምደባቸውን ባለማወቃቸው ያለምንም ሥራ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ በውሎ አበልና በነዳጅ እየተከፋፈሉ ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ።
“ታዲያ በዚህ ሁኔታ ሕዝቡ ምን ዓይነት ለውጥ ይጠብቃል?” እና “በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ላይ መንግሥትና አለ ማለት ይቻላል?” የሚሉ ከፍተኛ ጥያቄዎች ተነስተዋል።
ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ (WT Media)፣ የአካባቢውን ፖለቲካ በቅርበት የሚከታተሉ፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ ከፍተኛ አመራሮች እና ሌሎች የደረሱ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፦ በአጠቃላይ በክልሉ በከፍተኛ ደረጃ እየተስተዋለ ከሚገኘው ፀጥታ ችግር ባሻገር የተፈጠረው ይህ ችግር ጠንካራ የአመራር ሥርዓት ካልተዘረጋ እየቀረበ ባለው ሀገራዊ ምርጫ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ከማሳደር በተጨማሪ ክልሉን የመፍረስ አደጋ ሊያጋጣም የሚችል እንደሆነ በስፋት እየተነሳ ይገኛል።
ማሳሰቢያ፦ WT Media በሀገሪቱ በተለይም ደቡብ ኢትዮጵያ አከባቢ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት በማያገኙ ለተጮቆኑ ህብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥተው እውነትንና ሀቅን መሠረት አድርገው የሚሰራ ስለሆነ የመረጃ ሰጪ ግለሰቦች ምስጥርና ደህንነት በተጠበቀ ሁኔታ የደረሱን መረጃዎችን መልሰን አጣርተን ለህዝብና የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዲሰጡበት በታማኝነት ይፋ እናደርጋለን።
ለማህበረሰቡ ከፍተኛ ፋይዳ ባላቸው ህዝብ ጉዳዮች ላይ ሀሳባችሁን ለማካፈል ለሚፈልጉ ሁሉ ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ሆነን እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ሰብዓዊነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚፀባረቅበት በሌሎች ትላልቅ ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለ ዘውትር አብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው!! እኛ ዘውትር የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን !!
Voice of Marginalized Community – WT Media