1000080476

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከሕግና ሥነ ምግባር ውጪ ሾልከው ያመለጡ በሙስና የተዘፈቁ አመራሮች፤ የብልሹ አሰራር ሰንሰለት መቀጠሉ አሳሳቢ መሆኑ ተገልጿል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ውስጥ “ስር በሰደደው ሙስና፣ ስነምግባር ጉድለት፣ አድሏዊነትና ብልሹ አሰራር” ምክንያት ከመንግሥት አቅጣጫ ውጪ ሆነው፣ የርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ድጋፍ በማግኘት ሾልከው ያመለጡ አመራሮች መኖራቸው የብዙዎችን ትኩረት ስቧል።

ሰሞኑን የፌዴራል መንግሥት ትዕዛዝ ሰጪነት በተካሄደው ግምገማ “ህብረተሰቡ በመንግሥት ላይ እምነት እንዳይጥል እንቅፋት ፈጥረዋል” ተብሎ የተገመገሙ አመራሮች ሹም ሽረት እየተካሄደ ቢሆንም፣ አብዛኞቹ ዋና ችግር ፈጣሪዎች በሥልጣን እንዲቀጥሉ መደረጉን WT Media ከውስጥ ምንጮቹ አረጋግጧል።

WT Media በተደጋጋሚ በሙስና፣ በሌብነት፣ በከበሩ ማዕድናት፣ በኮንትሮባንድ እና በመሬት ኢንቨስትመንት ላይ የተዘፈቁ አመራሮችን ከሰነድ ጋር በማጋለጡ ይታወቃል።

ለአብነትም ከመንግሥት አቅጣጫ ውጪ የቀጠለ ሥልጣን ከመንግሥት አካሄድ ውጪ “ዎላይታ እና ጋሞ በክልል መዋቅር አንድ ላይ በፍጹም አይደራጅም፣ ህዝብን ባያስገድድ ይመረጣል” በሚል በመንቀሳቀስ የሚታወቁት፣ የቀድሞ የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪና የወቅቱ የደቡብ ኢትዮጵያ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ በሥልጣን ላይ የቀጠሉት አመራር ዋነኛ ምሳሌ ናቸው።

አቶ ብርሃኑ ዘውዴ በጋሞ ዞን አስተዳዳሪ በነበሩበት ከ2010 እስከ 2014 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ፣ ከክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት እውቅና ውጪ ከ104 ሺህ ካሬ ሜትር በላይ መሬት በምደባ አስተላልፈዋል።

በአርባ ምንጭ ከተማ በጥቅም ትስስርና ሕጋዊ አሰራርን በመጣስ በቁጥር 53 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች አሰራር ባልተከተለ መልኩ በጥቅም ትስስር የተላለፉ መሆናቸውን WT Media አስቀድሞ ዘግቧል።

ከ500 ሄክታር በላይ የማዕድን ልማት መሬት ከክልሉና ከኢንቨስትመንት አሰራር ውጪ ለግለሰቦች በአንድ ደብዳቤ ትዕዛዝ ሰጥተዋል።

በተለይም በቦረዳ ወረዳ ውስጥ ያለውን የድንጋይ ከሰል ለማምረት ለማራ ማይኒንግ ከነበረው 600 ሄክታር ላይ 10 ሄክታር ብቻ በማስቀረት ሌላውን ለጋሞ ልማት ማህበርና ለግል ተሸንሽኖ እንዲሰጥ ትዕዛዝ መስጠታቸው በሰነድ ተረጋግጧል።

ሌላኛው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ አለምነሽ ደመቀ የሚመሩት ቢሮ በከፍተኛ አድሏዊነትና የገንዘብ ብልሹነት ተዘፍቋል።

ወ/ሮ አለምነሽ ሌሎች ብሔሮች ሠራተኛ አለአግባብ እንዲባረሩ እና በውድድርም እንዳይገቡ በማድረግ፣ 88% በላይ ሰራተኞች የአንድ አካባቢ ብቻ እንዲሆኑ አድርገዋል።

ከ77 ሠራተኞች መካከል 88% ጋሞ ሲሆኑ፣ የዎላይታ ተወላጆች 6 ብቻ (2 ሹፌሮች እና 4 ተራ ሠራተኞች) መሆናቸውን መረጃው ያመለክታል።

በክልሉ በተለይም በዎላይታ ዞን፣ በጌዴኦ እና ጎፋ ዞን የሚገኙ ግብር ከፋይ ባለሀብቶች ላይ በልዩነት ያልተገባ ጫና በመፍጠር ፋብሪካዎች እንዲዘጉና ባለሀብቶች እንዲታሰሩና እንዲሸማቀቁ አድርገዋል።

የክልሉ ገቢ ቢሮ በሕጋዊ ቀመሩ መሠረት ለዞኖች መከፈል የነበረበትን “የጋራ ገቢ” ገንዘብ ሕጋዊ ቀመር በመጣስ በክልሉ እንዲቀር በማድረግ ከአመራሮቹ ጋር በመመሳጠር አለአግባብ ወጪ እንዲሆን ታደርጋለች።

ለጉዳዩ ቅርበት ያለው አመራር እንደገለጸው፣ ከፌዴራል ለክልሉ የተላከው በቢሊዮን የሚቆጠር ከፍተኛ ገንዘብ አለአግባብ ወጪ እየሆነ እስካሁን ኦዲት እንዳልተደረገ አስረድቷል።

የገዥው ፓርቲ በይፋ እንዳረጋገጠው ክልሉ “የመንግሥት አሰራር ሆነ የገዥው ፓርቲ ተግባርና ሕግ በመጣስ” በሌብነት፣ በሰብዓዊ መብት ጥሰትና በመልካም አስተዳደር ላይ እንቅፋት ፈጥረዋል በሚል የተገመገሙ አመራሮች ሹም ሽረት አካሄድ፣ ለኅብረተሰቡ ዘላቂ ልማትና ሰላም ሲባል ዋናው ችግር ፈጣሪዎች ላይ በማድረግ ዳግም ሊታይና ሊፈተሽ ይገባል የሚል ሀሳብ በርካቶች እያንፀባረቁ ይገኛሉ።

ማሳሰቢያ፦ WT MEDIA በሀገሪቱ በተለይም ደቡብ ኢትዮጵያ አከባቢ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት በማያገኙ ለተጮቆኑ ህብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥተው እውነትንና ሀቅን መሠረት አድርገው የሚሰራ ስለሆነ የመረጃ ሰጪ ግለሰቦች ምስጥርና ደህንነት በተጠበቀ ሁኔታ የደረሱን መረጃዎችን መልሰን አጣርተን ለህዝብና የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዲሰጡበት በታማኝነት ይፋ እናደርጋለን።

ለማህበረሰቡ ከፍተኛ ፋይዳ ባላቸው ህዝብ ጉዳዮች ላይ ሀሳባችሁን ለማካፈል ለሚፈልጉ ሁሉ ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ሆነን እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ሰብዓዊነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚፀባረቅበት በሌሎች ትላልቅ ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለ ዘውትር አብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው!! እኛ ዘውትር የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን !!
Voice of Marginalized Community – WT Media