በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ውስጥ የሚገኘው የዘይሴ ብሔረሰብ የጠየቀውን የልዩ ወረዳ መዋቅር ጥያቄ ለማፈን ሲባል፣ በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ እና በጋሞ ዞን አመራሮች አማካኝነት በሕዝቡ ላይ የኢኮኖሚ እገዳና የዘር ማጥፋት ወታደራዊ አዋጅ መታወጁን WT Media ከስፍራው ባገኘው መረጃ አረጋግጧል።

ከጥቅምት 2/2018 ዓ.ም. ጀምሮ ማለትም ለድፍን ሁለት ሳምንታት፣ የዘይሴ አርሶ አደር ዋነኛ ገቢ ምንጭ የሆነው ሙዝ እንዳይሸጥና እንዳይለወጥ በጋሞ ዞንና በአቶ ጥላሁን ከበደ ትዕዛዝ ክልከላ መጣሉን ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።

ክልከላው የተደረገው የዘይሴን ሕዝብ በአጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ጫና ውስጥ በመጣል፣ የሕልውና ትግሉንና ሕዝባዊ እምቢተኝነቱን እንዲያቆም ለማስገደድ ነው ብሏል።

ለምሳሌ ከዘይሴ የሚመረተው ሙዝ በመላው ኢትዮጵያ ከተሞች አልፎ እስከ ጅቡቲና ሶማሌላንድ ድረስ የሚጫን ሲሆን፣ ይህ ሕገወጥ እገዳ በሀገር ደረጃ የሙዝ ዋጋ በእጅጉ እንዲነር ምክንያት ሆኗል። በዘይሴ ማሳ ውስጥ ሙዝ በስሎ እየበሰበሰና ዋጋውን እያጣ ባለበት ወቅት፣ በሀገር ደረጃ ዋጋው ንሯል።

ከዚህ ባሻገር የጋሞ ዞን እና አቶ ጥላሁን ከበደ የሕዝቡን እንቅስቃሴ ለመገደብ ወታደራዊ አዋጅ ዓይነት እርምጃ እየወሰደ እንደሚገኝ የዘይሴ ብሄረሰብ ይገልፃሉ።

በክልሉና በዞኑ ያለ የፖሊስ ሠራዊት ሁሉ በዘይሴ መልክዓምድር ሰፍሯል። የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አድማ ብተና፣ የጋሞ ዞን ፖሊስ፣ የአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ፖሊስ እና ከሁሉም የጋሞ ዞን ወረዳዎች የተወጣጡ ሚሊሻዎች በዘይሴ ሕዝብ ላይ መሰማራታቸውን ነዋሪዎቹ ለWT Media አረጋግጧል።

ሕዝቡ በሰላም እንዳይወጣና እንዳይገባ እንዲሁም ዕለታዊ እንቅስቃሴውን እንዳያደርግ ክልከላ ተደርጓል።

የዘይሴ ደምብሌ ት/ቤት፣ ጤና ጣቢያና ማዘጋጃ ቤትን የፀጥታ ኃይሎች ካምፕ በማድረግ መንግሥታዊ ሽብርተኝነት እየፈጸሙ ይገኛሉ።

ፀጥታ ኃይሉ ወጣቶችን በገበያ ግቢ ደብድቦ ሲገድል፣ ሬ’ሳ ጭምር አንሰጥም ብለው ወስደው ሲደብቁ እንዲሁም ንብረትና እህል ከነጎተራው ሲያቃጥሉ ቤቶች በፍተሻ ምክንያት ሲዘረፉ ቆይተዋል።

በአርባ ምንጭ ከተማ ከቤተክርስቲያን የሚያገለግሉ ቀሳውስትን ጨምሮ 42 የዘይሴ ተወላጆችን ከሳምንት በላይ ሕገወጥ በሆነ የእህል መጋዘን ውስጥ አስረው ካሰቃዩ በኋላ ወደ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ አስገብተዋቸዋል። ከ200 ሰው በላይ ደግሞ ከዓመት በላይ በሐሰት ክስ ታስረዋል።

የጋሞ ዞን አመራሮች በተለያዩ አካባቢዎች ሕዝብ ሰብስበው ስለዘይሴ በመወያየት፣ የጋሞ ሕዝብ በዘይሴ ሕዝብ ላይ ጥላቻ እንዲያሳድር የጥላቻ ሐሳቦችን እየነዙ መሆናቸው ተገልጿል።

ይህ ድርጊት ነገ በትውልድ መካከል የሚኖረውን መልካም ጉርብትና የሚያበላሽ መሆኑ ተጠቁሟል።

የዘይሴ ሕዝብ በአሁኑ ሰዓት “ጭቆናው በቃ፣ ከእንግዲህ በኋላ አንታገስም” በማለት ሕዝባዊ እምቢተኝነት ውስጥ መግባቱን አሳውቋል።

የዘይሴ ሕዝብ አቶ ጥላሁን ከበደ የሚባሉ “አረመናዊ አፋኝ” ከክልሉ እስኪነሱ ድረስ ከመንግሥት ምንም መልካም ነገር እንደማይጠብቅ ገልጿል።

በጋሞ ዞን አመራሮች እና በአቶ ጥላሁን ከበደ አማካኝነት በሙዝ ምርት ላይ የተጣለው ሕገወጥ እገዳ በአስቸኳይ እንዲነሳ እንዲሁም ለዘይሴ ሕዝብ ፍትሕ እንዲሰፍን እና ሕዝቡ የጠየቀው የልዩ ወረዳ ጥያቄ እንዲመለስ፣ በጋሞ አመራሮችና በልዩ ኃይል እየተካሄደ ያለው የዘር ማጥፋት ዘመቻ እንዲቆም የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ ጥሪ አቅርቧል።

በፀጥታ ችግር ምክንያት የአርባ ምንጭ-ኮንሶ-ጅንካ መንገድ ዛሬ ለስድስተኛ ቀን ዝግ መሆኑን የደረሰው መረጃ ያሳያል።

ማሳሰቢያ፦ WT MEDIA በሀገሪቱ በተለይም ደቡብ ኢትዮጵያ አከባቢ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት በማያገኙ ለተጮቆኑ ህብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥተው እውነትንና ሀቅን መሠረት አድርገው የሚሰራ ስለሆነ የመረጃ ሰጪ ግለሰቦች ምስጥርና ደህንነት በተጠበቀ ሁኔታ የደረሱን መረጃዎችን መልሰን አጣርተን ለህዝብና የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዲሰጡበት በታማኝነት ይፋ እናደርጋለን።

ለማህበረሰቡ ከፍተኛ ፋይዳ ባላቸው ህዝብ ጉዳዮች ላይ ሀሳባችሁን ለማካፈል ለሚፈልጉ ሁሉ ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ሆነን እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ሰብዓዊነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚፀባረቅበት በሌሎች ትላልቅ ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለ ዘውትር አብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው!! እኛ ዘውትር የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን !!
Voice of Marginalized Community – WT Media