1000081367

ሰበር መረጃ: “በጎፋ የመሬት ናዳ የእርዳታ ገንዘብ ዘረፋ ሙከራ የታሰሩ ተጠርጣሪዎች እየተፈቱ ነው! የ60 ሚሊዮን ብር ቅሌት ተሳታፊ አመራሮች ከጥያቄ ለማምለጥ በሹመትና በጡረታ እንዲሸሹ እየደረገ ነው” ተባለ!

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በጎፋ ዞን የመሬት ናዳ ተጎጂዎች የእርዳታ ገንዘብ ላይ የተፈጸመውን የ60 ሚሊዮን ብር ዘረፋ ሙከራ ተከትሎ በቁጥጥር ሥር ውለው የነበሩ ተጠርጣሪዎች እየተፈቱ መሆናቸውን እና በቅሌቱ ውስጥ የተሳተፉ አመራሮች ደግሞ ከተጠያቂነት ለማምለጥ የሥልጣን ሽግሽግና ጡረታ እንደመሸሸጊያ እየተጠቀሙ መሆናቸውን WT Media ከአካባቢው ባገኘው አዲስ መረጃ አረጋግጧል።

ይህ አሳሳቢ ሁኔታ በጉዳዩ ዙሪያ የክልሉ መንግሥት ጉዳዩ በተከሰተበት ወቅት ብቻ መግለጫ ሰጥቶ ጉዳዩ የደረሰበትን ለህዝብ ይፋ አለማድረጉ አጠራጣሪነትን በማጠናከሩ በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎችም WT Media ን የጉዳዩ የደረሰበትን አሳውቁ በማለት ጥያቄ እያቀረቡ ይገኛሉ።

ከሦስት ሳምንት በፊት WT Media ዘግቦ እንደነበረው፣ የዘረፋው ሙከራ ተፈጽሟል በተባለበት አዲስ አበባ ንግድ ባንክ ሸገር ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ ለሚዲያው ሲመልሱ፦ “በእኛ ባንክ ቅርንጫፍ በተባለው ግለሰብና 60 ሚሊዮን ብር ተብሎ በተጠቀሰው ገንዘብ መጠን ለማጭበርበር የመጣ ሰው አላየንም። እኛ ስለጉዳዩ እንደማንኛውም ሰው ከማኅበራዊ ሚዲያዎች ነው ያየነው፣ እኛ ጋ ያንን በተመለከተ ምንም መረጃ የለንም” ብለዋል።

ይህ የባንኩ ምላሽ የጎፋ ዞን መንግሥት “በአስተዳደሩ ጥቆማ ዘረፋው መክሸፉን” በሚል ከሰጠው መግለጫ ጋር የሚጋጭ ሆኖ ቀጥሏል፤ ባንኩ የወንጀል ድርጊት ተፈጽሞበታል ከተባለ በኋላ ዝም ማለቱ ሕጋዊ ጥያቄዎችን አስነስቷል።

ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ (WT Media) ከታማኝ ምንጮች አዲስ የደረሱ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፦ በጉዳዩ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉ ግለሰቦች እየተፈቱ መሆናቸው ተገልጿል።

በዘረፋው ሙከራ ውስጥ በቀጥታ ተሳትፎ ያላቸው አመራሮች ተጠያቂነት እንዳይኖርባቸው ከቦታ ወደ ሌላ ሥልጣን እንዲቀየሩ እየተደረገ ነው። እንዲሁም፣ አንዳንድ ተሳታፊዎች በጡረታ እንዲወጡ በማድረግ ክስ እንዳይመሰረትባቸው እየተሸፈኑ ይገኛሉ።

በሐሰተኛ ቼክ ገንዘቡን ለማውጣት ሞክሯል የተባለው ግለሰብ “መሐመድ ኑርሁሰን ሲራጅ” በተባለ የክልሉ አመራሮች ለጥቅም እንደተጠቀሙበት በሚጠረጠር ግለሰብ ላይ የተደረገው “በብቸኝነት በተለየ ክፍል መታሰር” እና “ማንም እንዳይጠይቀው መከልከል” ሕገወጥነትና እውነታውን የመደበቅ ሩጫ መሆኑ ቀድሞውንም ተገልጾ ነበር።

ክልሉ ከሰጠው ብቸኛ መግለጫ ውጪ ሌላ ማብራሪያ እስካሁን አልሰጠም። ይህም የሚከተሉትን ዋና ጥያቄዎች መልስ አልባ አድርጓቸዋል፦ በሙከራው ውስጥ ቁልፍ ተሳታፊነት አላቸው ተብለው የተጠረጠሩት ጉዳያቸው የት ደርሷል? በተለየ ክፍል ታስሮ የነበረው “መሐመድ ኑርሁሰን ሲራጅ” የተባለው ቁልፍ ተጠርጣሪ ያለበት ሁኔታ ምንድነው? የሚሉት ይገኙበታል።

ሌላው ለአብነትም፦ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ፣ ለተጎዱ ወገኖች ከተለያዩ አካላት ከተሰበሰበው በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር የእርዳታ ገንዘብ ቀጥታ ሲመራ የነበረውን አቶ ጋንታ ጋምኦን ከአደጋ ስጋት ሥራ አመራርና የምግብ ዋስትና ኮሚሽን ኮሚሽነርነት ኃላፊነት በማንሳት በጡረታ እንዲገለሉ በማድረግ በክልሉ ከፍተኛ ሰብዓዊ መብት ጥሰት ተሳትፎ ባደረገው ግለሰብ በመተካት፣ የዘረጉትን የሌብነት ሰንሰለትና ተጠያቂነት ለመሸፈን መሞከራቸው ተነግሯል።

አቶ ጋንታ ጋምኦ ኮሚሽነር በነበሩበት ወቅት፣ በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ላይ በተከሰተው የመሬት ናዳ ምክንያት ከተለያዩ ወገኖች የተሰበሰበውን በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ከፕሬዝዳንቱ በተሰጠው “ቀጭን ትዕዛዝ” ከነጋዴዎች ጋር በመመሳጠር ያሸሹትና የተከፋፈሉ፣ ገንዘቡን ለማውጣት በመንግሥት ተቋማት ሥም የታተመውን ቼክ፣ ምንም ዓይነት ውልና ሰነድ በሌለበት ሁኔታ የውስጥ ፈራሚ የፋይናንስ ባለሞያዎችን በማስፈራራት አስፈርመው፣ ምንም ነገር ያልተጻፈበትን ቼክ እራሳቸው እየሞሉ ለፕሬዝዳንቱ ቅርብ ለሆኑ ግለሰቦች ሲያድሉ እንደነበር መረጃው ያመለክታል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአደጋ እርዳታ ገንዘብ ላይ የተፈጸመው የዘረፋ ሙከራ፣ በክልሉ ከፍተኛ አመራሮች እየተሸፈነና ሕገወጥ የሆነ የማስፈታትና የማስሸሽ ተግባር እየተፈጸመበት መሆኑን የደረሱ መረጃዎች ያመለክታሉ።

WT Media ይህንና መሰል የሙስና ሰንሰለት ማጋለጡን የሚቀጥል ሲሆን፣ የፌዴራል መንግሥትና የሕግ የበላይነት አካላት በጉዳዩ ላይ በአስቸኳይ ጣልቃ እንዲገቡና እውነታውን ለሕዝብ ይፋ እንዲያደርጉ አበክሮ ይጠይቃል።

ማሳሰቢያ፦ WT MEDIA በሀገሪቱ በተለይም ደቡብ ኢትዮጵያ አከባቢ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት በማያገኙ ለተጮቆኑ ህብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥተው እውነትንና ሀቅን መሠረት አድርገው የሚሰራ ስለሆነ የመረጃ ሰጪ ግለሰቦች ምስጥርና ደህንነት በተጠበቀ ሁኔታ የደረሱን መረጃዎችን መልሰን አጣርተን ለህዝብና የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዲሰጡበት በታማኝነት ይፋ እናደርጋለን።

ለማህበረሰቡ ከፍተኛ ፋይዳ ባላቸው ህዝብ ጉዳዮች ላይ ሀሳባችሁን ለማካፈል ለሚፈልጉ ሁሉ ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ሆነን እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ሰብዓዊነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚፀባረቅበት በሌሎች ትላልቅ ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለ ዘውትር አብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው!! እኛ ዘውትር የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን !!
Voice of Marginalized Community – WT Media