1000081452

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በዘይሴ ሕዝብ ላይ የዘር ማጥፋት ዘመቻ፣ የግፍ ግድያ፣ እስርና ንብረት ውድመት እየተካሄደ ያለውን ለመሸፈን “ሀገር አቀፍ የሰላም” ኮንፈረንስ ለማካሄድ እንቅስቃሴ መጀመሩ ተገልጿል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጋሞ ዞን መዋቅር ውስጥ እንዲካተቱ የተገደደው የዘይሴ ሕዝብ “ራስን በራስ ማስተዳደርና የልዩ ወረዳ” ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄ በመጠየቁ ብቻ፣ በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ እና በጋሞ ዞን አመራሮች ቀጥተኛ ትዕዛዝ የዘር ማጥፋት ዘመቻ (Genocide) እየተፈጸመ መሆኑን WT Media ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የአካባቢው ተወላጅ ጋር ባደረገው ቆይታ ተጋልጧል።

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ መምህሩ እንዳሉት፣ በዘይሴ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለው ግፍ “በዘይሴነታቸው ምክንያት ብቻ የዘር ማጥፋት ወንጀል ወይም ጄኖሳይድ” ነው።

“በየቀኑ ከ20 በላይ ወጣቶች በግፍ እየተገደሉ ነው ቀጥታ በአቶ ጥላሁን ከበደ ትዕዛዝ የዜይሴ ሕዝብ የመኖር ሕልውናውን አጥቷል” ሲሉ ገልጸዋል።

እንደ መምህሩ ገለፃ ይህንን በበላይነት የሚመሩት “የጋሞ አመራሮችና የጥላሁን ከበደ አሽከሮች የሆኑት የክልሉ ጸጥታ አካላት” ናቸው።

ጸጥታ ኃይሎችና የጋሞ ዞን ፖሊሶች ሕዝቡን ከቤት እያወጡ እንደሚረሽኑ፣ እንደሚያስሩና ቤት ንብረት እንደሚያቃጥሉ መምህሩ ገልጸዋል።

በተጨማሪም በአካባቢው የተጎዱት እንዳይታከሙ “ጤና ጣቢያ ጭምር ተቃጥሎ ሕዝቡ ጫካ ገብቷል” ብለዋል።

የዘይሴ ሕዝብ የራሱ የሆነ ቋንቋ፣ ባህል፣ ታሪክና ማንነት ያለው ሕዝብ ሲሆን፣ የሕገ መንግሥታዊ ጥያቄው በአቶ ጥላሁን ከበደ ቡድን በኃይል እየታፈነ ያለው ለፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንደሆነ መምህሩ አብራርተዋል።

የጋሞ ዞን አስተዳደርና የአቶ ጥላሁን ከበደ ቡድን የጋሞን ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ፣ ዘይሴን፣ ቁጫንና ዶርዜን ጨምሮ የማንነት ጥያቄ የሚጠይቁ ብሔረሰቦችን በጉልበት በመጫን የአካባቢውን የፖለቲካ የበላይነት ለመያዝ ይፈልጋሉ።

ዓላማቸውም “ጥቂት ቁጥር ያለው ጋሞ” በእነዚህ ብሔረሰቦች ሥም አጠቃላይ ክልሉን በማፈን የራሳቸውን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ፍላጎታቸውን ለመሙላትና ክልሉን እንደፈለጉ ለመዘወር ማቀዳቸው ነው።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል (ማረቆ፣ ቀቤና፣ ጣምባሮ) ተመሳሳይ የልዩ ወረዳ ጥያቄዎች ምላሽ አግኝተው ሳለ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የዘይሴና የቁጫ ሕዝብ ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄ በግድያና በእስራት መታፈኑ የሕግ የበላይነትን የሚጥስና “ዘር የሚያስጠፋ ተግባር” የሆነው በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ብቻ ነው ብለዋል።

ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ (WT Media)፣ ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የአካባቢው ተወላጅ አክለውም እንደገለፁት፦ በዘይሴ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ላለው ጭፍጨፋ የፌዴራል መንግሥት ዝምታ የሰጠው ትኩረት አሳሳቢ እንደሆነም ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ሕዝቡን ቀርበው ማናገር አለመፈለጋቸውን እና በዘይሴ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን “ጭካኔ የተሞላበትን ዘር ማጥፋት ዘመቻ በዝምታ ማየታቸው” ሕዝቡ “ፈጣሪ ይጠይቃቸዋል” የሚል እምነት እንዳለው ገልጸዋል።

ይህንን የዘይሴውን ጭፍጨፋ ለመደበቅ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ስለ ጸጥታ መዋቅር አደረጃጀት የውሸት መግለጫ እየሰጡና “ሀገር አቀፋዊ የሰላም ጉባኤ አርባምንጭ ታስተናግዳለች” የሚል ሽፋን እየሰጡ መሆኑን መምህሩ አጋልጠዋል።

በዘይሴ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለው ግፍ “መንግሥት ባለበት አገር መፈጸሙ በጣም ያሳዝናል” ሲሉ፣ መምህሩ ጠንካራ ጥሪ አቅርበዋል።

በዘይሴ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን የዘር ማጥፋት ዘመቻ ቀጥታ በጋሞ ዞን አመራሮችና በአቶ ጥላሁን ከበደ አማካኝነት የሚፈጸም በመሆኑ፣ በፎቶና በቪዲዮ የተደገፉ መረጃዎች ተደራጅተው ለአለም አቀፍ ፍርድ ቤት፣ ለኤምባሲዎች፣ ለሰብዓዊ ኮሚሽኖችና ለዓለም አቀፍ ተቋማት ለማቅረብ ዝግጅት እየተደረገ ነው።

“ይህንን የዘር ማጥፋት ወንጀል ለመደበቅ የሚደረገውን ጥረት ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአንድነት ሊቃወመውና ድምፅ ሊሆን ይገባል” ሲሉ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል።

ማሳሰቢያ፦ WT MEDIA በሀገሪቱ በተለይም ደቡብ ኢትዮጵያ አከባቢ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት በማያገኙ ለተጮቆኑ ህብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥተው እውነትንና ሀቅን መሠረት አድርገው የሚሰራ ስለሆነ የመረጃ ሰጪ ግለሰቦች ምስጥርና ደህንነት በተጠበቀ ሁኔታ የደረሱን መረጃዎችን መልሰን አጣርተን ለህዝብና የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዲሰጡበት በታማኝነት ይፋ እናደርጋለን።

ለማህበረሰቡ ከፍተኛ ፋይዳ ባላቸው ህዝብ ጉዳዮች ላይ ሀሳባችሁን ለማካፈል ለሚፈልጉ ሁሉ ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ሆነን እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ሰብዓዊነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚፀባረቅበት በሌሎች ትላልቅ ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለ ዘውትር አብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው!! እኛ ዘውትር የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን !!
Voice of Marginalized Community – WT Media