1000083862

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጋሞ ዞን አርባምንጭ ከተማ በቅርቡ አንድ ግለሰብ በፈጸመው ዘግናኝ የሕፃን ግድያ ወንጀል ምክንያት፣ በከተማዋ በሚኖሩ በአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ ብሔር ተኮር ወንጀሎች እና ከፍተኛ የሆነ ድብደባና ያለአግባብ እስር እየደረሰባቸው መሆኑን WT Media ከነዋሪዎች በደረሰው መረጃ አረጋግጧል።

በተመሳሳይ፣ የጋሞ ተወላጆችም በገዛ ምድራቸው ወንጀል ፈጻሚዎች ሽፋን ተሰጥቷቸው በሕዝባቸው ላይ እየተፈጸመ ያለውን በደል በቁጭት ገልጸዋል።

  1. በጋሞ ምድር በአማራ ተወላጆች ላይ የሚደርሰው በደል (ከአማራ ተወላጆች ቅሬታ)

የአርባምንጭ ከተማ ነዋሪ የሆኑና ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ግለሰብ ለሚዲያችን እንደገለጹት፣ አንድ ግለሰብ ህዳር 4 ቀን 2018 ዓ.ም. በአንድ ሕፃን ላይ በፈጸመው ዘግናኝ ግድያ ወንጀል (ወንጀለኛው በፖሊስ ቁጥጥር ስር ቢውልም)፣ በከተማዋ በተቃራኒው በአማራ ብሔረሰብ ተወላጆች ላይ ብሔር ተኮር ወንጀሎች እየተፈጸሙ ነው።

የጋሞ ብሔር ተወላጆች የአማራ ተወላጆችን በመለየት ከሥራ መስካቸው ታግተው እየተወሰዱ በከተማው ፖሊስ ጽ/ቤት እና በጋሞ ዞን መደበኛ ፖሊስ ከፍተኛ የሆነ ድብደባና ያለአግባብ እስር እየተፈጸመባቸው ይገኛል።

በ2010 ዓ.ም. በክሪው ባር ውስጥ የጋሞ ልማት ማኅበር ሥራ አስኪያጅ ልጅ ጋር በተፈጠረ ግጭት፣ የክለቡ ባለቤት የአማራ ተወላጅ በመሆኑ “አማራ ነፍጠኛ ነው” በሚል ከፍተኛ ድብደባ ተፈጽሞበት ክለቡ እንዲዘጋ መደረጉን በማስታወስ፣ አሁንም በከተማዋ በሕይወት ለመኖር ሰቀቀን እየሆነባቸው እንደሆነ ገልጸዋል።

“ብሔር ተኮር በአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ እየተፈጸመ ያለዉን ዘግናኝ ድብደባዎችን አጥብቀን እየተቃወምን ፍትሕ ለአማራ ተወላጆች!” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

  1. የጋሞ ሕዝብ ቁጭት እና መራራ እውነታ (ከጋሞ ተወላጆች ቅሬታ)

በተመሳሳይ ከጋሞ ተወላጆች ለWT Media በደረሰው መረጃ፣ “ወንጀለኛ ግለሰብ እንጂ ወንጀለኛ ብሔር እንደሌለ” በመግለጽ፣ በጋሞ ምድር በተለይ ከአማራ ክልል በመጡ ግለሰቦች እየተፈጸሙ ያሉ ተከታታይ ወንጀሎች እና የክልሉ አመራር የሚሰጠውን ሽፋን በዝርዝር አብራርተዋል።

የአማራ ተወላጆች ፈጽመው የተባሉ ወንጀሎች:

ሕዳር 4 ቀን 2018 ዓ.ም. በአርባምንጭ አንድን ሕፃን ካገተ በኋላ ወላጆቹን አስፈራርቶ ገንዘብ ተቀብሎ ሕፃኑን በአሰቃቂ ሁኔታ ገድሎ አካሉን ቆራርጦ ሽንት ቤት የጣለ የአማራ ተወላጅ።

በ2017 ዓ.ም. በአርባምንጭ አንድ ሆቴል ተቀጥሮ ሲሰራ የነበረች የጋሞ ተወላጅን በአሰቃቂ ሁኔታ ገድሎ በአሁኑ ሰዓት አማራ ክልል ተሸሽጎ የሚገኝ ግለሰብ።

ለመንፈሳዊ አገልግሎት የቀረቡ ሴቶችና ታዳጊዎች ላይ አስገድዶ መድፈር ወንጀል በመፈጸም ወደ ትውልድ አካባቢው አማራ ክልል አምልጦ የሚገኝ የሐይማኖት አባት።

የጋሞ ሕዝብ መብት ጥሰት እና የአመራሩ ሽፋን:

በአርባምንጭ ሆቴል ውስጥ የጋሞ ተወላጅ ወጣት የገደለው ግለሰብ መታወቂያ ጭምር እያለ ሆን ተብሎ እስከ ዛሬ ድረስ ተዳፍኖ ይገኛል። በሕግ አምልጦ የአማራ ክልል ገብቶ ይገኛል።

በቁጫ ወረዳ ሰላማዊ ሰልፍ የወጡ የጋሞ ተወላጆች ላይ ጥይት ተኩሶ ወጣት የገደለ ፖሊስ በአሁኑ ሰዓት ጨንቻ ከተማ ተዛውሮ እየሰራ ሲሆን የሟች ቤተሰቦች ፍትሕ ተነፍገዋል።

በኦሞ ባንክ አርባምንጭ ዲስትሪክት ውስጥ ከአራት ዓመት በላይ ለሚሆን ጊዜ ከአማራ ክልል ብቻ በልዩ ሁኔታ እያመጡ መሾማቸው ብቻ ሳይሆን፣ እንደመጡ የአርባምንጭ ከተማ ነዋሪነት መታወቂያ “ብሔር በሚለው ቦታ ‘ጋሞ’ የሚል ተጽፎበት” መሰጠቱ ተገልጿል።

የጋሞ ቴሌቪዥን ውስጥ የጋሞኛ ቋንቋ የማይችል ሠራተኛ በማስገባት፣ የጋሞነት እሴቶችን የሚያጎሉ ጽሑፎች (እንደ “Gamo Land of Peace”) ከብሔር ብሔረሰቦች በዓል በኋላ በፍጥነት እንዲነቀሉ በማድረግ “ጋሞ በገዛ ምድሩ ባይተዋር እንዲሆን” እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

የጋሞ ሕዝብ ኢኮኖሚያዊ አቅም ካለው “ክፉዎችን የመታገል ጉልበት ያገኛል” በሚል ስሌት፣ ለፖሊሶች፣ ዳኞችና ዓቃቤ ሕጎች በሚሊዮኖች የሚቆጠር ጉቦ በመስጠት የጋሞ ተወላጅ ባለሀብቶችን ማሳደድና ማክሰር ሥራ እየተሰራ ነው” ሲል ገልፀዋል።

በአጠቃላይ፣ የአርባምንጭ ከተማ “በሁለቱም ወገኖች በተቀነባበረ የፖለቲካ ሴራና በብሔር ተኮር ፍረጃ ምክንያት የፍትሕ መጓደል እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚታይባት ከተማ ሆናለች” በሚል አክለዋል።

🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏

Voice of Marginalized Community – WT Media

R