GridArt_20251121_172927551

“ክልሉ የማያውቀው አስቸኮይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ ከአርባምንጭ ከተማ በ5 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በሚገኘው ዘይሴ ህዝብ ላይ የተደራጀ የዘር ማጥፋት ዘመቻ እየተካሄደ ነው” ሲሉ የአከባቢው አይን እማኞች ገልጿል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በፕሬዝዳንት አቶ ጥላሁን ከበደ ሰብሳቢነት የተደራጀው “ልዩ ገዳይ ኮማንድ ፖስት” በጋሞ ዞን እና በክልሉ ውስጥ የዘይሴ ብሔረሰብን የማንነት እና ራስን በራስ የማስተዳደር ሕገመንግሥታዊ ጥያቄን ለማፈን በኢኮኖሚ ማዳከም፣ በአፈና እና ከሕግ ውጪ በሆነ ግድያ ላይ ተሰማርቶ እንደሚገኝ WT Media ከውስጥ አዋቂና ታማኝ ምንጮች የደረሰው መረጃ ይጠቁማል።

በክልሉ እና በጋሞ ዞን የተቋቋመው ይህ ልዩ ቡድን፣ የዘይሴን ሕዝብ ኢኮኖሚያዊ አቅም በማዳከም፣ ሕዝባዊ ትግሉን ለማኮላሸት እየሰራ መሆኑን የመረጃ ምንጮች አስረድተዋል።

ፕሬዝዳንት አቶ ጥላሁን ከበደ በአርባምንጭ ከተማ ውስጥ ያሉ ከአካባቢው ተወላጅ ውጭ የሆኑ ባለሀብቶችና ባለንብረቶች፣ “እናንተ ናችሁ ለዘይሴና አካባቢው የፀጥታ ችግር ምክንያት” በማለት በማስፈራራት ላይ ናቸው ብለዋል።

ባለፈው ሳምንት ለተካሄደው ሀገር ዓቀፍ የሃይማኖት ተቋማት የሰላም ኮንፈረንስ የመጡ እንግዶች፣ ከአካባቢው ውጭ ባሉ ሆቴል ባለቤቶች አልጋ፣ ምሳ፣ እራት እና ቁርስ ያለምንም ክፍያ እንዲስተናገዱ መደረጉ፣ የባለሀብቶቹን የኢኮኖሚ አቅም የማዳከም ስልት አካል መሆኑ ተጠቁሟል።

በፕሬዝዳንቱ አቶ ጥላሁን ከበደ ቀጥተኛ ትዕዛዝ፣ በአርባምንጭ እና ዙሪያ ያሉ የዘይሴ ብሔር ተወላጆች እየታፈኑ፣ እየተወሰዱ በጫካ እየተረሸኑ መሆኑን የደረሱ መረጃዎች እያሳዩ ነው።

በሕዝባዊ ጥያቄያቸው ምክንያት እንደ ወንጀለኛ እየተቆጠሩ የሚታደኑት የዘይሴ ተወላጆች ላይ፣ የክልሉ ልዩ ኃይል፣ አድማ ብተና፣ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ እና የሀገር መከላከያ ሠራዊት ጭምር በአጠቃላይ ከ470 በላይ የፀጥታ ኃይል በአንድ ወረዳ ላይ በማሰማራት ዘመቻ እየተካሄደ እንደሚገኝ የ #WTMedia ምንጮች አረጋግጠዋል።

የፀጥታ ኃይሉ ሰዎቹን እየያዘ ለጋሞ ዞን ፖሊስ ፍርድ ቤት እንዲያቀርብ ቢያስረክብም፣ የጋሞ ዞን ፖሊስ አባላትና አመራሮች ግን ያለምንም የፍርድ ቤት ውሳኔ ሌሊት ወደ ጫካ በመውሰድ እየረሸኑ እንደሆነም ከአይን እማኞች ለማወቅ ተችሏል።

በጋሞ አመራር ውስጥ ያለ አንድ ከፍተኛ ባለሥልጣን፣ የሁኔታውን አሳሳቢነት በመገንዘብ በውስጥ መስመር ለWT Media መረጃ ያካፈሉ ሲሆን፣ ለዘይሴ ሕዝብም ጥብቅ መልእክት አስተላልፈዋል፡

“ዘይሴዎች ልዩ ጥንቃቄ እንዲያደርጉና ትግላቸው ወደ ጫፍ እየደረሰ በመሆኑ አጠናክረው እንዲቀጥሉ… ኢኮኖሚያው ነገ ተሰርቶ ይመጣል፤ ይህ ትግል ከተቋረጠ መቼም ቢሆን የዘይሴ ማንነት ጥያቄ… አይሳካም። አንድነታችሁን ጠብቃችሁ ትኩረታችሁን በትግሉ ላይ አድርጉ” የሚል ጥሪ ቀርቧል።

“ትግሉ ወደ ጫፍ በመድረሱ፣ መንግሥት አጠቃላይ አርባምንጭ ኮንሶ አማሮ ቡርጂ ጂንካ ኮሪደርን ላለማጣት ሲል “አፋጣኝ መልስ ለመስጠት እየተነጋገሩ ይገኛሉና ትግሉ መቀጠልና መፏፏም አለበት” የሚል ምክርም ሰጥተዋል።

አስተያየት ሰጪዎቹ እንደገለፁት፦ በጋሞ ዞን በዘይሴ ብሔረሰብ ላይ ብሔር ተኮር ጥቃት ከተጀመረ ረጅም ዓመታት ያስቆጠረ ቢሆንም፣ የዘንድሮው እየደረሰ ያለው ስቃይ “ለየት ባለ መልኩ በርትቶ ቀጥሏል” ብሏል።

በመሆኑም የሚመለከተው የፌዴራል የመንግሥት አካል፣ የሰብአዊ መብት ተቋማትና የሚዲያ አካላት በዘይሴ ህዝብ ላይ ያለማቋረጥ እየተፈፀመ የሚገኘውን የተደራጀ የዘር ማጥፋት ዘመቻ እንዲቆምና ወንጀሎችን ለህግ ለማቅረብ መተባበር እንዳለባቸውም ተማፅነዋል።

🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏

Voice of Marginalized Community – WT Media