በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የዘመናት የሁለቱ ህዝቦች ጥያቄ የነበረው የደሜ ድልድይ ግንባታ ተጀመረ ቢባልም፣ በጋሞ ዞን አመራሮች ጫና ግንባታው እንዲቆም እየተደረገ መሆኑ ተገለፀ
በክልሉ በዎላይታ ዞን ኪንዶ ዲዳዬ ወረዳን እና በጋሞ ዞን ቁጫ አልፋ ወረዳን የሚያገናኝና የበርካታ ዓመታት የአከባቢው ሕዝብ ጥያቄ የነበረው የደሜ ወንዝ ድልድይ ግንባታ፣ በይፋ መጀመሩ ቢበሰርም አሁን ላይ በከፍተኛ አመራሮች ጫና ግንባታው እንዲቆም መደረጉን የሚጠቁሙ መረጃዎች ለ WT Media ደርሷል።

የዎላይታ ዞን ኪንዶ ዲዳዬ ወረዳ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ግንባታው መጀመሩን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ እና WT Media ከአካባቢው ነዋሪዎችና ከባለሙያዎች ባሰባሰበው የምርመራ ዘገባ መረጃ መካከል ሰፊ ልዩነት ታይቷል።
የዎላይታ ዞን ትራንስፖርት እና መንገድ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል አይሳሮ እና የኪንዶ ዲዳዬ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበበ ዋኬ በቦታው ተገኝተው በሰጡት መግለጫ ግንባታው የሁለቱን ሕዝቦች የዘመናት ጥያቄ የሚመልስ መሆኑን ገልጸዋል።

ድልድዩ የዎላይታ ዞን ኪንዶ ዲዳዬ እና የቁጫ አልፋ ወረዳዎችን ከ15 በላይ ቀበሌያት በቅርበት የሚያገናኝ ሲሆን፣ ለማኅበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ትስስር ከፍተኛ ሚና አለው።
ይሁን እንጂ ግንባታው መጀመሩን ተከትሎ ከጋሞ ዞን በኩል ግንባታውን ለማስተጓጎል ሙከራዎች እየተደረጉ መሆኑን ለWT Media የደረሱ መረጃዎች ያመለክታሉ።
በዎላይታ በኩል ቁፋሮው ተሠርቶ እያለቀ ቢሆንም፣ ትናንት ከቁጫ ወረዳ የመጡ የፀጥታ አካላት ግንባታው እንዲቆም ለፕሮጀክቱ መሐንዲሶች ማስጠንቀቂያ መስጠታቸውን የዓይን እማኞች ገልጸዋል።
ጨረታውን አሸንፎ ወደ ሥራ የገባው Prop Construction PLC ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ ሲሳይ ቁሳቁሶችን ወደ ቦታው ማጓጓዝ ቢጀምሩም፣ የጋሞ ዞን አመራሮች ድልድዩ እንዳይሠራ ከፍተኛ ጫና እያደረሱባቸው መሆኑ ተጠቁሟል።

አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ መረጃ ምንጭ፣ ግንባታው ወደ ቁጫ ወረዳ እንዳይሻገር በክልል ከፍተኛ አመራር ትእዛዝ መስተጓጎሉን ገልጸው፤ ዓላማው ተቋራጩ ቅድመ ክፍያውን ሳይወስድ ሥራውን ጥሎ እንዲወጣ ለማድረግ ነው ብለዋል።
“ለበርካታ ዓመታት ሳይሳካ የዘለቀውን ይህን ፕሮጀክት፣ አሁንም ተቋራጩ ጥሎ እንዲወጣ በክልሉ ከፍተኛ አመራር ትእዛዝ መሠረት ጫና የማድረግ የተለመደ ሙከራ እየተደረገ ነው” በማለት አንድ የቁጫ አልፋ ወረዳ ነዋሪ አስረድተዋል።
WT Media የደረሰውን ጥቆማ መሠረት በማድረግ በጉዳዩ ዙሪያ ከክልሉ መንግሥት፣ ከጋሞ ዞን እና ከቁጫ አልፋ ወረዳ አመራሮች ማብራሪያ ለማግኘት ያደረገው ጥረት እስካሁን አልተሳካም።
እነዚህ ተቋማት ግንባታው ስለመቆሙም ሆነ ስላለበት ደረጃ እስካሁን የሰጡት ይፋዊ መግለጫ የለም።
የአካባቢው ነዋሪዎች ይህንን “አስነዋሪ ድርጊት” በማውገዝ፣ የፌዴራል መንግሥት በጉዳዩ ላይ ጣልቃ በመግባት የሕዝቡን የልማት ጥያቄ እንዲያስከብርና ግንባታው እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏
Voice of Marginalized Community – WT Media