የጋሞ ልማት ማህበር (ጋልማ) በከፍተኛ ሙስና፣ በስልጣን መባለግ እና በፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት ምክንያት ለህልውናው የሚያሰጋ “የካንሰር በሽታ” እንደተያዘ የህግ ባለሙያውና የቀድሞ የቦርድ አባል አቶ ደሳለኝ ከበደ ካዛ በድጋሚ አጋልጠዋል።
አቶ ደሳለኝ ከሁለት ወራት በፊት ከቦርድ አባልነታቸው በገዛ ፈቃዳቸው መልቀቃቸውን ተከትሎ ያነሷቸውን 10 ነጥቦች በማጠናከር፣ ዛሬ በሰጡት ተጨማሪ መግለጫ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ተቋሙን ወደ ግል መጠቀሚያነት ቀይረውታል ሲሉ መክሰሳቸውን WT Media ተመልክቷል።
አቶ ደሳለኝ ዛሬ ይፋ ባደረጉት መረጃ፣ የጋሞ ልማት ማህበር የታሪክ ውርደት እየገጠመው መሆኑን ገልጸዋል።
የጋልማ የበላይ ጠባቂ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ መሆናቸው እየታወቀ፣ አቶ ጥላሁን ከበደ ራሳቸውን “የበላይ ጠባቂ” አድርገው በመሾም የልማት ማህበሩን የሙስና ማዕከል አድርገውታል።
አቶ ጥላሁን ከ2003 እስከ 2011 ዓ.ም. በቦርድ ሰብሳቢነት በነበሩበት ወቅት ተቋሙን የካድሬ መጫወቻ አድርገውት እንደነበር ያስታወሱት አቶ ደሳለኝ፣ አሁንም በቦርድ አባልነት ስም ተቋሙን ወደ ቁልቁለት እየመሩት መሆኑን ገልጸዋል።

የአርባ ምንጭ እርሻ ልማት መሬት ቅርምት
በቢሊዮን የሚቆጠር የህዝብ ሀብት እየተመዘበረ መሆኑን አቶ ደሳለኝ በማስረጃ ጠቁመዋል።
ከ900 ሄክታር በላይ ከሆነው የጋልማ መሬት ውስጥ ከ250 ሄክታር በላይ የሚሆነው ያለ ቦርድ ውሳኔና ያለ ካሳ ለጥቂት ግለሰቦችና ተቋማት ተላልፏል።
በአቶ ጥላሁን ቀጥተኛ ትዕዛዝ የአርባ ምንጭ እርሻ ልማት መሬት ለልዩነህ ዱባለ ትምህርት ቤት፣ ለፓርክላንድ ኮሌጅ (እናት ፓርቲ) እና ለአሚባራ ሪል እስቴት በሙስና መሰጠቱን አጋልጠዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በጋሞ ህዝብ ላይ እየፈጸሙት ነው ያሉት ጥሰቶች እጅግ አሳሳቢ ናቸው፦
በጋሞ ዞን ሻራ እና ዘይሴ አካባቢዎች ለተከሰቱት ግጭቶችና የንጹሃን ዜጎች ግድያ አቶ ጥላሁን እጅ እንዳለባቸው አቶ ደሳለኝ በይፋ ከሰዋል።
“ህገ-መንግስታዊ ስርዓትን ለመናድ ተንቀሳቅሰዋል” በሚል በንጹሃን ላይ የተመሰረተው ክስ የፖለቲካ ድራማ መሆኑንና አቶ ጥላሁን “ህግ ሳይሆን ፖለቲካ ነው የማገዛው” በሚል መርህ ህዝቡን እያሰቃዩ መሆኑን ጠቁመዋል።
ከኦሮሚያ የተፈናቀሉ የጋሞ ተወላጆችን መልሶ ለማቋቋም የቀረቡ ፕሮጀክቶች በአቶ ጥላሁን ፍቃደኝነት ማጣት ሳይሳኩ ቀርተዋል።
መመሪያ ተጥሶ የወንጀል ሪከርድ ያላቸውና ጡረተኞች በአቶ ጥላሁን ትዕዛዝ ተቀጥረው ሀብት እያባከኑ ይገኛሉም ብሏል።
ተቋሙ የዘረፋ ማዕከል መሆኑንና በትዳር የተሳሰሩ አመራሮች (ርዕሰ መምህርትና አስተዳዳሪ) ተማሪዎች ላይ የሞራል ስብራት እያደረሱ መሆኑ ተገልጿል።
አቶ ጥላሁንን ጨምሮ አንዳንድ አባላት ከ15 እስከ 25 ዓመታት በቦርድ አባልነት በመቆየት ተቋሙን እንደ ግል ቤት እያገለገሉበት ይገኛሉ።
አቶ ደሳለኝ ከበደ ካዛ ለጋሞ ህዝብና ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላት የሚከተለውን ጥሪ አቅርበዋል።
የበላይ ጠባቂው አቶ ታገሰ ጫፎ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ በመጥራት ቦርዱን ሙሉ በሙሉ በሪፎርም እንዲያፈርሱና በተፈጸሙ የሙስና ወንጀሎች ላይ ተጠያቂነት እንዲሰፍንና ተቋሙ ከውድቀት እንዲድን ጠይቀዋል።
የፌደራል መንግስት በአቶ ጥላሁን ከበደ ላይ እየቀረቡ ባሉ ተጨባጭ የሌብነትና የሰብዓዊ መብት ጥሰት መረጃዎች ላይ አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድም አሳስበዋል።
WT Media ቀደም ሲል በርዕሰ መስተዳድሩ ዙሪያ ሲያቀርባቸው የነበሩት ዘገባዎች ዛሬ በተቋሙ ውስጥ በነበሩ ከፍተኛ አመራሮች መረጋገጣቸው የሚዲያችንን እውነተኝነት ዳግም ያረጋገጠ መሆኑን እየገለጽን፣ ጉዳዩን በቅርበት መከታተላችንን እንቀጥላለን።
🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏
Voice of Marginalized Community – WT Media