በዎላይታ ሶዶ ከተማ የሚገኘው የኢንፎሊንክ ኮሌጅ ተማሪዎች፣ ተቋሙ “ሕገ-ወጥ” የሆነ የገንዘብ ብዝበዛ፣ እንግልትና ማስፈራሪያ እያደረሰብን ነው ሲሉ ለ WT Media ቅሬታ አቅርበዋል።
ኮሌጁ ጥያቄ ያነሱ ተማሪዎችን በፖሊስ ኃይል እያስፈራራ መሆኑም ታውቋል።
ተመራቂ ተማሪዎች ለ WT Media እንዳስረዱት፣ ኮሌጁ ለምረቃ ጋዋን በሚል 1,600 ብር እንዲከፍሉ እያስገደዳቸው ይገኛል።
ተማሪዎቹ ቅሬታቸውን በሚከተሉት ነጥቦች ያቀርባሉ፦
የዋጋ ንረት፦ ለጋዋን የተጠየቀው 1,600 ብር ካለው ወቅታዊ የገበያ ዋጋ አንጻር እጅግ የተጋነነና ተማሪን የመበዝበዝ ተግባር ነው።
የመብት ረገጣ፦ ጋዋን የመውሰድም ሆነ ያለመውሰድ መብት የተጠበቀ መሆን ሲገባው፣ ኮሌጁ ግን ክፍያውን ካልከፈላችሁ በሚል ተማሪዎችን እያገደ ይገኛል።
ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር፦ ክፍያው የሚፈጸመው በተቋሙ ሕጋዊ የባንክ አካውንት ሳይሆን በግለሰብ አካውንት እንዲሆን መታዘዙ፣ አሠራሩ ግልጽነት የጎደለውና ለሙስና የተጋለጠ መሆኑን ያሳያል።
የአምስተኛ ዓመት ተማሪዎች የመመረቂያ ጥናት ጽሑፍ (Defense) ለማቅረብ ለማክሰኞ ቀጠሮ የተያዘላቸው ቢሆንም፣ በዚሁ የገንዘብ ውዝግብ ምክንያት እስካሁኑ ሰዓት ድረስ እየተንገላቱ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም ከተለያዩ ወረዳዎችና ራቅ ካሉ አካባቢዎች የመጡ ተማሪዎች ለሳምንታት ያህል ያላንዳች መፍትሔ ለከፍተኛ ወጪና እንግልት ተዳርገዋል።
ተማሪዎች መብታቸውን በጠየቁበት ወቅት፣ የኮሌጁ አስተዳደር የጸጥታ ኃይሎችን (ፖሊስ) ወደ ግቢው በማስገባት ተማሪዎች እንዲበተኑና ወደ ግቢው እንዳይገቡ እያደረገ መሆኑ ተገልጿል።




WT Media የፖሊስ አባላት ተማሪዎችን ሲያባርሩና ግቢውን ሲዘጉ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል (Video) ከቦታው ደርሶታል።
WT Media የተማሪዎችን አቤቱታ መሠረት በማድረግ ከኢንፎሊንክ ኮሌጅ የዎላይታ ሶዶ ካምፓስ አመራሮች ማብራሪያና ምላሽ ለማግኘት ተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርግም፣ የአመራሮቹ ስልክ ባለመነሳቱ ሙከራው ሳይሳካ ቀርቷል።
WT Media የጭቁን ተማሪዎችን ድምፅ ለማሰማትና እውነት እስኪወጣ ድረስ ጉዳዩን በቅርበት መከታተሉን ይቀጥላል።
የሚመለከታቸው የትምህርት ጥራትና የጸጥታ አካላት በዚህ ሕገ-ወጥ አሠራር ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡና የተማሪዎች እንግልት በአፋጣኝ እንዲቆም እንጠይቃለን።
🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏
Voice of Marginalized Community – WT Media