GridArt_20260102_174336827

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በኮንሶ ዞን ኮልሜ ወረዳ ቦርቃራ ቀበሌ፣ “አለታ” በተባለች መንደር የሚኖሩ ዜጎች ለመኖሪያ ቤታቸው የኤሌክትሪክ ኃይል ለማስገባት በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ከከፈሉ በኋላ፣ የተገባላቸው ቃል ተጥፎ ለከፋ ብዝበዛና እንግልት መዳረጋቸውን ለ WT Media በምሬት ገልጸዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች ለመብራት ቆጣሪና ለዝርጋታ በሚል በቀበሌውና በወረዳው አመራሮች አማካኝነት ከፍተኛ የገንዘብ ማሰባሰብ ተካሂዶባቸዋል።

ለምሳሌ በመንገድ ዳር የሚገኙ ቤቶች ለእያንዳንዱ ቤት 4,205 ብር እንዲከፍሉ ተደርጓል።

ከመንደሩ ነዋሪዎች በአጠቃላይ እስከ 5,000,000 (አምስት ሚሊዮን) ብር የሚጠጋ ገንዘብ ተሰብስቦ ለአመራሮች ገቢ መደረጉን ተጎጂዎቹ ያስረዳሉ።

ገንዘቡ ከተሰበሰበ በኋላ ነዋሪዎቹ የጠበቁት መብራት ሳይመጣ፣ አሁን ላይ አመራሮቹ “መብራቱ መንደሩን አልፎ ይሄዳል እንጂ እዚህ አይወርድም” የሚል ምላሽ መስጠታቸው ነዋሪዎችን አስቆጥቷል።

ይህ አልበቃ ብሎ አሁን ደግሞ “አሠሪዎች ተጨማሪ ገንዘብ ይፈልጋሉ” በሚል ሌላ የክፍያ ጥያቄ እየቀረበባቸው መሆኑን ተጎጂዎቹ ገልጸዋል።

የአለታ መንደር ነዋሪዎች በክልሉና በዞኑ አመራሮች ላይ እምነት በማጣታቸው፣ ጉዳዩን የፌዴራል መንግሥትና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያውቁት በ WT Media በኩል አደራ ብለዋል።

“የተሰበሰበው ሚሊዮኖች የት ገባ?” የሚለው ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ እንዲያገኝ ይፈልጋሉ።

የመብራት ፕሮጀክቶችን የሚመራውና የሚያሠራው የፌዴራል አካል በመሆኑ፣ በድሆች ላይ እየተፈጸመ ያለውን ይህን ግልጽ ብዝበዛ እንዲያስቆም ጥሪ ቀርቧል።

WT Media የተሰበሰበው ገንዘብ የት እንደደረሰና የመብራት ዝርጋታው ለምን እንደተሰናከለ ለማወቅ ወደ ኮልሜ ወረዳና ወደ ቀበሌው አመራሮች ስልክ በመደወል ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ጥረት ቢያደርግም፣ ሙከራው ሳይሳካ ቀርቷል።

WT Media የጭቁን ዜጎችን ድምፅ ለማሰማትና እውነት እስኪወጣ ድረስ ጉዳዩን በቅርበት መከታተሉን ይቀጥላል።

የሕዝብ ገንዘብ የበሉ አካላት ለሕግ እንዲቀርቡና ለአለታ መንደር ፍትሕ እንዲሰጥ እንወተውታለን።

🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏

Voice of Marginalized Community – WT Media