GridArt_20260109_093518790

በሀዋሳ ከተማ ትናንት ሌሊት በተከሰተ አስከፊ የእሳት አደጋ የሁለት ሰዎች ህይወት ማለፉንና በበርካታ መኖሪያ ቤቶችና ንብረት ላይ ከፍተኛ ውድመት መድረሱን ታውቋል።

አደጋው የተከሰተው ማታ ከሌሊቱ 5፡10 ገደማ ሲሆን፣ መነሻው ከአዲሱ መናኸሪያ ወደ ወልደ አማኑኤል በሚወስደው መንገድ ላይ “አጠና ተራ” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው።

በአደጋው ሳቢያ በአሰቃቂ ሁኔታ ህይወታቸው ያለፈው አንዲት እናትና ልጃቸው መሆናቸውን ከስፍራው የደረሱን መረጃዎች ያመለክታሉ።

እሳቱን ለመቆጣጠር የከተማ አስተዳደሩ የእሳት አደጋ መከላከል ቡድንና የአካባቢው ነዋሪዎች ከፍተኛ ርብርብ ቢያደርጉም፣ እሳቱን ሙሉ በሙሉ ማጥፋት የተቻለው እስከ ሌሊቱ 7፡45 ድረስ በቆየ ጥረት ነው።

በሰው ህይወት ላይ ከደረሰው ጉዳት በተጨማሪ፣ በርካታ መኖሪያ ቤቶችና የንግድ መደብሮች ሙሉ በሙሉ በመቃጠላቸው ነዋሪዎች ለከፍተኛ እንግልት ተዳርገዋል።

WT Media ስለ አደጋው መንስኤና ስለደረሰው የንብረት ውድመት ዝርዝር መረጃ ለማግኘት ወደሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ስልክ በመደወል ተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርግም፣ ለጊዜው ሙከራው ሳይሳካ ቀርቷል።

የከተማ አስተዳደሩ በአሁኑ ወቅት የእሳቱን መነሻ መንስኤ በማጣራት ላይ እንደሚገኝ የታወቀ ሲሆን፣ ህዝቡና የሚመለከታቸው አካላት መሰል አደጋዎችን ለመከላከል አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄና ዝግጅት እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል።

በደረሰው ድንገተኛ አደጋ ህይወታቸውን ላጡ ወገኖች የተሰማንን ጥልቅ ሃዘን እየገለጽን፣ ለቤተሰቦቻቸውና ለወዳጅ ዘመዶቻቸው መጽናናትን እንመኛለን።