በዎላይታ ሶዶ ክርስትያን ሆስፒታል የተዘረጋው የሙስና መረብና በጤና ባለሙያዎች ላይ እየደረሰ ያለው የጨረር አደጋ – ልዩ የምርመራ ዘገባ
በ ናትናኤል ጌቾ (WT Media መስራችና ዋና ኤዲተር)
መግቢያ፦ የተቋም መውደቅ ስጋት
በ1998 ዓ.ም. በዎላይታ ምድር ሲመሰረት ዓላማው ግልጽ ነበር፤ ለኢትዮጵያውያንና ለምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ጥራት ያለውና በክርስቲያናዊ ስነ-ምግባር የታነጸ የሕክምና አገልግሎት መስጠት። በታዋቂው ኢትዮጵያዊ ምሁር ዶ/ር ቀለሙ ደስታ እና በአሜሪካዊው ዶ/ር ሃሮልድ አዶልፍ የተመሰረተው፣ በአንጋፋው ሥራ አስኪያጅ አቶ ደሣለኝ ኢኖሬ ዘመን ደምቆ የታየው የሶዶ ክርስትያን ሆስፒታል (Soddo Christian Hospital)፣ ዛሬ ግን በታሪኩ አይቶት የማያውቀው የህልውና አደጋ ተጋርጦበታል።
WT Media ካለፉት በርካታ ወራት ጀምሮ ከሆስፒታሉ የሠራተኛ ማህበር፣ ከውስጥ ምንጮችና ከፋይናንስ ሰነዶች ያሰባሰበው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ተቋሙ በጥቂት የአስተዳደር አካላት የተደራጀ የሙስና መረብ፣ የፋይናንስ ምዝበራ እና የሰብአዊ መብት ረገጣ ውስጥ ሰጥሞ ይገኛል።

1. የዘጠኝ ቀናት ዝምታ፦ የአመራሩ ሽሽት
ይህ ዘገባ ለሕዝብ ይፋ ከመደረጉ በፊት፣ WT Media የጋዜጠኝነት የሥነ-ምግባር መርህን በመከተል ለሆስፒታሉ አመራር ምላሽ እንዲሰጥ ሰፊ ዕድል ሰጥቶ ነበር።
- ከጥር 1 (Jan 01/2026) ጀምሮ ለዋና ሥራ አስኪያጁ (CEO) አቶ ኤፍሬም ገብረስላሴ በግል የዋትስአፕ (WhatsApp) ስልክና መልዕክት ቢላክም ምላሽ አልተገኘም።
- በሆስፒታሉ ኦፊሴላዊ ኢሜይል በኩል ለቀረበው ጥያቄ፣ የአሜሪካው ቦርድ አባል ኬን አምስተትዝ (Ken Amstutz) መልዕክቱ መድረሱን አረጋግጠው ለCEO ኤፍሬም እንዲመልሱ ቢልኩላቸውም፣ ሥራ አስኪያጁ ግን በዝምታ መደበቅን መርጠዋል።
ይህ በባለሥልጣናቱ በኩል የታየው የኃላፊነት መሸሽ፣ በሆስፒታሉ ውስጥ ለሚነገረው “ተጠያቂነት የሌለው አምባገነናዊ አሠራር” ሕያው ምስክር ሆኗል።
2. የ85 ሚሊዮን ብር ቅጣትና የፋይናንስ ምስቅልቅል
የሆስፒታሉ የፋይናንስ ሥርዓት ግልጸኝነት በጎደለውና ተቆጣጣሪ በሌለው ሁኔታ በጥቂት ግለሰቦች እጅ ወድቋል።
- የታክስ ቅጣት፦ የፌዴራል ታክስ ኦዲት የሐዋሳ ቅርንጫፍ መ/ቤት በሆስፒታሉ ላይ ከ85 ሚሊዮን ብር በላይ ቅጣት መጣሉ ተረጋግጧል። ይህ ቅጣት የተጣለው በአስተዳደሩ የሰነድ አያያዝ ግድፈትና በብልሹ አሠራር ቢሆንም፣ አመራሩ ግን ለሆስፒታሉ ባለቤቶችና ለጋሾች ጉዳዩን በማድበስበስ “በልመና ከመጣ ገንዘብ እንከፍላለን” የሚል ኃላፊነት የጎደለው ሪፖርት ማቅረቡ ተጋልጧል።
- ያለ ጨረታ የሚደረጉ ግዢዎች፦ መድኃኒቶች፣ የሕክምና ቁሳቁሶች፣ አልፎ ተርፎም የካፌና የንጽህና አገልግሎቶች ያለ ምንም ግልጽ ጨረታ ለአስተዳደሩ ቅርብ ለሆኑ ግለሰቦች ይሰጣሉ። ይህም ሆስፒታሉን ለተጋነነ የዋጋ ምዝበራ ዳርጎታል።
- የንብረት ምዝበራ፦ ለጥገና የወጡ ውድ የሕክምና መሣሪያዎች ደብዛቸው መጥፋት፣ እንዲሁም የሆስፒታሉ ነዳጅ ለግለሰቦች የግል መኪናና ለቤት አገልግሎት መዋል የዕለት ተዕለት ተግባር ሆኗል።

3. የጤና ባለሙያዎች በደል፦ “ጉልበት መበዝበዝ”
የሆስፒታሉ የጤና ባለሙያዎች የሚገኙበት ሁኔታ እጅግ አሳዛኝ መሆኑን የሠራተኛ ማህበሩ መረጃዎች ያሳያሉ።
- የደመወዝ ጭቆና፦ የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ መመሪያ ቁጥር 1110/2018 ያወጣውን የደመወዝ ስኬል ማሻሻያ ሆስፒታሉ ተግባራዊ ለማድረግ ፈቃደኛ አልሆነም።
- የታካሚዎች መበዝበዝ፦ ለሠራተኛው ደመወዝ ለመጨመር “ጥናት እያደረግን ነው” የሚለው አስተዳደሩ፣ በታካሚዎች የአገልግሎት ክፍያ ላይ ግን ከ20,000 እስከ 30,000 ብር የሚደርስ ድንገተኛ ጭማሪ ማድረጉ የጤና አገልግሎቱን ለሕዝብ የማይቀመስ አድርጎታል።
- የአድልዎ ቅጥር (Nepotism)፦ ልምድ ያላቸው ነባር ሠራተኞች “ካልፈለጋችሁ ልቀቁ” በሚል ማስፈራሪያ እንዲሰናበቱ ይደረጋል። በምትካቸውም የሥራ ልምድ የሌላቸው የአስተዳደሩ ቤተሰቦችና ጓደኞች በከፍተኛ ደመወዝ ይቀጠራሉ። ጥቂት የአስተዳደር አባላት ከ100,000 ብር በላይ ሲከፈላቸው፣ የሕክምና ባለሙያው ግን ከኑሮ ውድነቱ በታች ባለ ደመወዝ እንዲማቅቅ ተፈርዶበታል።
4. የጨረር (Radiation) አደጋ፦ የባለሙያዎችና የታካሚዎች ሕይወት በፈተና
በጣም አሳሳቢውና አስደንጋጩ የምርመራ ውጤት በኦፕሬሽን ክፍል ውስጥ ያለውን የጨረር አያያዝ ይመለከታል።

- መከላከያ የሌለው ጨረር፦ በኦፕሬሽን ክፍል ውስጥ ያሉ ሁለት የC-arm X-ray ማሽኖች፣ የክፍሉ ጣሪያና ግድግዳ የጨረር መከላከያ (Lead lining) ሳይገጠምላቸው አገልግሎት እየሰጡ ነው።
- የጤና ጉዳት፦ በዚህ ክፍተት ምክንያት በክፍሉ ውስጥ የሚሠሩ ዶክተሮች፣ ነርሶችና የአንስቴዥያ ባለሙያዎች ለከፍተኛ የጨረር አደጋ ተጋልጠዋል። ይህም በባለሙያዎች ላይ የፅንስ መጨንገፍ፣ ከፍተኛ ራስ ምታትና ሌሎች የጤና እክሎችን እያስከተለ መሆኑን የሠራተኛ ማህበሩ በቁጭት ገልጿል።
- ሕገ-ወጥ አሠራር፦ በሙያው ያልሰለጠኑና ፈቃድ የሌላቸው ግለሰቦች የጨረር ማሽኖችን እንዲያንቀሳቅሱ መደረጉና ለባለሙያዎች የሚገባው የተጋላጭነት ክፍያ መከልከሉ የአስተዳደሩን ግድየለሽነት ያሳያል።
5. የ”ኮለን” ሪከርድ፦ የባከኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ፈንዶች
ለሆስፒታሉ ማስፋፊያ ተብሎ በሚሊዮን የሚቆጠር በጀት ተመድቦለት የነበረው የ “Women and Children’s – Hope Center” ግንባታ፣ በአሁኑ ወቅት በኮለን ደረጃ ቆሞ የቀረ “የሙስና ሀውልት” ሆኗል። ለዓመታት ግንባታው ተቋርጦ የህንጻው አጽም ብቻ መታየቱ፣ ለእናቶችና ለሕጻናት መድረስ የነበረበትን ሕይወት አድን አገልግሎት አግቷል። ለዚህ ፕሮጀክት የመጣው ገንዘብ የት እንደደረሰ የሚጠይቅ አካል አለመኖሩ ደግሞ ጉዳዩን ይበልጥ አሳዛኝ ያደርገዋል።



6. መደምደሚያና የለውጥ ጥሪ
የሶዶ ክርስትያን ሆስፒታል ለዘጠኝ ዓመታት ያህል ከሠራተኛው ጋር ስብሰባ አድርገው በማያውቁት ሥራ አስኪያጅ አቶ ኤፍሬም ገብረስላሴ ስር ወድቆ ወደ ማይቀረው ጥፋት እየተጓዘ ይገኛል። ሆስፒታሉ በአሁኑ ወቅት የሕክምና ተቋም መሆኑ ቀርቶ በጥቂት ግለሰቦች ፍላጎት የሚመራ “የንግድ ማዕከል” መስሏል።
WT Media ለሚመለከታቸው አካላት የሚከተሉትን ጥሪዎች ያቀርባል፦
- የፌዴራል ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን፦ በሆስፒታሉ ውስጥ ያለውን መጠነ-ሰፊ የገንዘብ ምዝበራና የግዢ ሥርዓት በአስቸኳይ እንዲመረምር።
- የጤና ሚኒስቴርና የጨረር ባለሥልጣን፦ በኦፕሬሽን ክፍል ውስጥ ያለውን የጨረር አደጋ መርምሮ የሠራተኞችንና የታካሚዎችን ደህንነት እንዲያስጠብቅ።
- የዎላይታ ሕዝብና የሀገር ሽማግሌዎች፦ ይህንን ታሪካዊ ተቋም በጥቂት ስግብግብ ግለሰቦች እጅ ወድቆ ከመጥፋት እንዲታደጉት።
እውነት ይወጣል! ተቋሙን ከውድቀት ለማዳን የምናደርገውን የምርመራ ዘገባ እንቀጥላለን።
በጋዜጠኝነት ግዴታችን መሠረት፣ የሆስፒታሉ አስተዳደር በማንኛውም ሰዓት ምላሽ ለመስጠት ቢፈልግ WT Media በሩ ክፍት መሆኑን እንገልጻለን።
🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይም በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏
Voice of Marginalized Community – WT Media