የዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የሁለት ዓመታት የልማትና የለውጥ ጉዞ ስኬቶች፣ ስጋቶች እና ቀጣይ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ላይ ከዎላይታ ዞን ከተወጣጡ የተለያዩ ተቋማትና የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር ምክክር ተካሄደ፡፡

ሰላምንና ሠላማዊነትን በማረጋገጥና በማዝለቅ በ2013 በጀት ዓመት የመማር ማስተማር ሥራን ውጤታማ ለማድረግ ታስቦ ከማህበረሰቡ ጋር ለመምከር የተዘጋጀ የምክክር መድረክ መሆኑም ተገልጿል፡፡

የዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ፍጽም ሠላማዊ ሆኖ እንዘልቅ እና በልማቱ ያለውን ድርሻ ለማበርከት ዘርፈ ብዙ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን ነው የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ታከለ ታደሰ በአውደ ምክክሩ ተሳታፊ ለሆኑ አካላት በእንኳን በደህና መጣችሁ ንግግራቸው የገለጹት፡፡

በምክክር መድረኩ የወላይታ ሀገር ሽማግሌዎች፣ የሐይማኖት አባቶች፣ የመንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የሠላምና ጸጥታ አስከባሪዎች፣ የወጣት ተወካዮች እንዲሁም ተጽህኖ ፈጣሪ ግለሰቦች የተሳተፉ ሲሆን፤ ዩኒቨርሲቲው ፍጹም ሠላማዊ ሆኖ በመማር ማስተማር፣ በችግር ፈቺ ጥናትና ምርምር፣ በአሳታፊ የማህበረሰብ አገልግሎት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና ስርጸት እንዲሁም በዘርፈ ብዙ ልማታዊ ሥራዎች የሚፈለገው ውጤት እንዲመዘገብ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎና ሚና ጉልህ መሆኑን ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል፡፡

በምክክር መድረኩ የተሳተፉ ባለድርሻ አካለት የዩኒቨርሲቲውን ሠላማዊነት በማረጋገጥ እና በማዝለቅ ለሠላማዊ መማር ማስተማር መስፈን ከምንግዜውም በላይ ከተቋሙ ጎን በመሆን የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ያላቸውን ተሳትፎ አጠናክረው እንዲያስቀጥሉ ፕሮፌሰር ታከለ ታደሰ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በምክክር መድረኩ የተገኙት የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪና የዩቨርሲቲው ምክትል ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር እንድሪያስ ጌታ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ተግባር ባሻገር፣ በሳይንሳዊ ጥናት ላይ በመመርኮዝ ተግባራዊ እያደረገ ያለው የማህበረሰብ አገልግሎት ስራ በአካባቢው አወንታዊ ልማት እውን እንዲሆን ጉልህ ሚና ተጫውቷል በማለት ተናግረዋል፡፡

እንደ ዶክተር እንድሪያስ ገለጻ ዩኒቨርሲቲው ለአካባቢው ወጣቶች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድሎችን በማመቻቸት ረገድ የድርሻውን ኃላፊነት የተወጣ ከመሆኑም ባሻገር፤ በአረንጓዴ ልማት ከተሞችን በማስዋብ፣ ትምህርት ቤቶችን በማስፋፋት፣ በከተማ መሰረተ ልማት ዝርጋታ በሶዶ ከተማ የተተገበረው የመንገድ ዳር መብራት እና የትራፊክ መቆጣጠሪያ መብራት፣ በግብርናው መስክ የአርሶአ አደሩን ምርትና ምርታማነት በሚያረጋግጡ ፕሮጀክቶች እንዲሁም በአካባቢው ለሚገኙ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የትምህርት ዕድልን በማመቻቸት ጭምር የተተገበሩ ሥራዎች ተጨባጭ ለውጥ ማምጣታቸውን ምክትል ቦርድ ሰብሳቢው አውስተዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የተገመሩ ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በተለይማ በማህበረ-ኢኮኖሚው መስክ በተጨባጭ የታዩ አወንታዊ ለውጦች የበለጠ እንዲያብቡ ሠላምን መሠረት በማድረግ በተቀናጀ እና በተደራጀ አግባብ ሁሉም ባለድርሻ አካል በባለቤትነት መንፈስ ከተቋሙ ጎን መሰለፍ እንደሚገባ ዶ/ር እንድሪያስ አሳስበዋል፡፡

ለሠላም እጦት መነሻ የሚሆኑ ተግዳሮቶችን በመለየት ብሎም በተቋም ደረጃ ሠላምን ሊያደፈርሱ የሚችሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመለየት መፍትሄዎችንም በማበጀት ረገድ ሁሉም ባለድርሻ አካል በትብብር ሊሰራ እና ተቋመኑን ወደ ተሸለ ከፍታ ሊያሸጋገር ይገባል ሲሉም ዶ/ር እንድሪያስ ጌታ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በምክክርር መድረኩ የወላይታ የዩኒቨርሲቲው የሁለት ዓመታት የልማትና የለውጥ ጉዞ ስኬቶች፣ ስጋቶች እና ቀጣይ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ላይ የተዘጋጀ ሪፖርት በዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ታከለ ታደሰ የቀረበ ሲሆን፤ እንደ ተቋም የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡና አዎንታዊ ለውጥ የሚመጡ ስራዎችን የቅድሚያ ቅድሚያ ለሰጣቸው የሚገቡ ተግባራትን በመለየት በቀጣይም አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ በሪፖርታቸው ፕሬዝዳንቱ አሳውቀዋል፡፡

ለብልሹ አሰራር የሚዳርጉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በየደረጃው በመለየት ተገቢውን ርምት ለመውሰድ አቅጣ የተቀመጠ መሆኑን ፕሬዝዳንቱ አውስተው፤ በተደራጀና በተቀናጀ ሕዝባዊ ተሳትፎ በተቋሙ የታቀዱና ትኩረት በሚሹ የልማት መስኮች ላይ ትኩረት ሰጥተን እንሰራልን ሲሉም ፕሮፌሰር ታከለ ታደሰ በሪፖርቱ ጠቁመዋል፡፡

ከሠዓት በኋላ በነበረው መድረክም ሠላማዊ መማር ማስተማርን በተቀናጀ መልኩ ለማስቀጠል በሚቻልበት አግባብ ሠላምና ጸጥታን በተመለከተ የተዘጋጀ ሰነድ የዎላይታ ዞን ሠላምና ጸጥታ መምሪያ ኃላፊ በሆኑት በአቶ ተስፋዬ ጎአ የቀረበ ሲሆን፤ በወላይታ ዞን ቤተሰብን የማዳን ፕሮጀክት አተገባበርን በተመለከተ የተዘጋጀ የጥናት ሠነድ በዩኒቨርሲቲው መምህር በሆኑት በዶ/ር አብርሃም አሻ እንደሚቀርብ ይጠበቃል፡፡

በቀረቡ ሰነዶች ላይ ውይይት ከተካሄደ በኋላ የምክክር መድረኩ ተሳታፊዎች በዩነቨርሲቲው የተከናወኑ የልማት ሥራዎችን እና ተማሪዎችን መልሶ ለመቀበል የሚደረጉ ዝግጅቶችን እንደሚጎበኙ ከዝግጅቱ ከአስተባባሪ ኮሚቴ ለማወቅ ተችሏል ሲል የዩኒቨርስቲው ኮሙኒኬሽን ዳይሮክተሬት ዘገባ ያመለክታል።