በናትናኤል ጌቾ(Artout)

በመሬት መንሸራተት ምክንያት ለችግር መጋለጣቸውን በወላይታ ዞን የካዎ ኮይሻና የኪንዶ ኮይሻ ወረዳ አርሶ አደሮች ተናገሩ፡፡


ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት መምሪያ አስታውቋል፡፡
ሰሞኑን በሁለቱም ወረዳዎች በደረሰው የመሬት መንሸራተት የ4 ሰዎች ህይወት አልፏል፡፡
በወላይታ ዞን ከሐምሌ 2012 ጀምሮ በጣለው ከባድ ዝናብ 12 ወረዳዎች የመሬት መንሸራተት አደጋ ሰለባ መሆናቸውን ከዞኑ እርሻና ተፈጥሮ መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ አርሶ አደር ታዲዮስ ዳንሳና እዮብ ባሳ በዞኑ የካዎ ኮይሻና የኪንዶ ኮይሻ ወረዳ ነዋሪዎች ናቸው፡፡


በየወቅቱ በሚደርሰው የመሬት መንሸራተት ለችግር መዳረጋቸውን ተናግረዋል፡፡የአከባቢው ህብረተሰብ ስጋት ላይ መሆናቸውን አርሶ አደሮች ጨምረው ገልፀዋል፡፡


በዘላቂነት መንግስት ከስጋት ነጻ በሆነ አከባቢ እንዲያሰፍራቸውም ጠይቀዋል፡፡
የካዎ ኮይሻ እና የኪንዶ ኮይሻ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪዎች አቶ ጎበዙ ጎቶሮ እና አቶ ተሾመ ሀብቴ እንዳሉት በወረዳዎቹ በየወቅቱ የመሬት መንሸራተት መከሰት እንዳሳሰባቸው አስታውቀዋል፡፡
የአከባቢው ነዋሪዎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን የተናገሩት አስተዳዳሪዎቹ ጊዜያዊ እርዳታ እያደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በዘላቂነትም ነዋሪዎቹን ለማስፈር የሚመለከታቸው አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡
በወላይታ ዞን እርሻና ተፈጥሮ ሀብት መምሪያ የአደጋ ስጋት አመራር ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ዘውዱ ኡርቃቶ በበኩላቸው በዞኑ በተለያዩ ወረዳዎች በደረሰው የመሬት መንሸራተት የሰው ህይወትና ንብረት ወድሟል፡፡
ጉዳት የደረሰባቸውን 21 ሺህ 5 መቶ ነዋሪዎችን የመደገፍ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ኃላፊው ገልጸዋል።


በመሬት መንሸራተትና በጎርፍ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች ከዞኑ መንግስት የ2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በጀት መመደቡን አቶ ዘውዱ ተናግረዋል፡፡
ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትት በዞን ደረጃ እየተሰራ መሆኑን ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡
ሰሞኑን በሁለቱም ወረዳዎች በደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ የ4 ሰዎች ህይወት ማለፉም ታውቋል፡፡