"እየሱስ ጌታ ነው" በማለቱ በአርባ ምንጭ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ተማሪ ላይ በፖሊስ የተፈጸመ አሰ’ቃቂ ድብደባ
በጋሞ ዞን አርባ ምንጭ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ፣ ትምህርቱን አጠናቆ ደስታውን እየገለጸ በነበረ ተማሪ ላይ በአንዲት የፖሊስ አባል አማካኝነት እጅግ ዘግናኝና ኢ-ሰብአዊ ድርጊት መፈጸሙን ለ WT Media የደረሱ ተንቀሳቃሽ ምስሎችና መረጃዎች አረጋገጡ።

1. የሁኔታው ዝርዝር
ጥር 09/2018 ዓ.ም. ከአሪ ዞን የመጣውና የኮሌጁ ተማሪ የሆነው ገረሙ ሺንኪባይስ፣ የሕክምና ትምህርቱን አጠናቆ የብቃት መመዘኛ (COC) ፈተና በስኬት ማለፉን አረጋግጧል። ተማሪው ይህንኑ ስኬቱን ተከትሎ “እየሱስ ጌታ ነው፤ አሻግሮኛል!” በማለት ፈጣሪውን እያመሰገነና ደስታውን እየገለጸ ከግቢው መውጫ በር ላይ ሲደርስ፣ ያልታሰበ ጥቃት ተሰንዝሮበታል።
2. የተፈጸመው ኢ-ሰብአዊ ድርጊት
በመውጫ በሩ ላይ የነበረችው የፖሊስ አባል (ማንነቷን እያጣራን እንገኛለን)፣ ተማሪው ደስታውን በመግለጹ ብቻ በዱላ ደብድባዋለች። ድርጊቱ እጅግ ዘግናኝ የሚሆነው፦

- ተማሪውን መሬት ላይ እያንከባለለች በዱላ ስትቀጠቅጠው እንደነበረ።
- ከመውጫ በሩ አንስቶ እስከ ተፈተነበት አዳራሽ ድረስ እየገረፈች በማመላለስ፣ የተማሪው አካል በኮብል ስቶን (የድንጋይ መንገድ) ተልጦ እስኪያልቅ ድረስ ስቃይ እንዳደረሰችበት።
- በመጨረሻም በጠራራ ፀሐይ ጭንቅላቱ (አናቱ) ላይ በሰነዘረችበት ድብደባ ተማሪው ራሱን ስቶ መውደቁ ተገልጿል።
3. የተማሪው ወቅታዊ ሁኔታ
በደረሰበት አሰቃቂ ድብደባ ራሱን የሳተው ተማሪ ገረሙ ሺንኪባይስ፣ በአሁኑ ወቅት በአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል በከፍተኛ ሕክምና ላይ እንደሚገኝ ታውቋል።
ተማሪው ትምህርቱን ጨርሶ ለወላጆቹና ለሀገሩ ሊደርስ ባለበት ሰዓት እንዲህ ዓይነት ጥቃት መሰንዘሩ በኮሌጁ ተማሪዎችና በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሷል።
የ WT Media ማሳሰቢያና ጥሪ
ሕግን ለማስከበር የቆመ የፖሊስ አባል፣ ደስታውን በገለጸና ፈጣሪውን ባመሰገነ ተማሪ ላይ እንዲህ ዓይነት “አረመኔያዊ” ጥቃት መፈጸሟ ተቀባይነት የለውም። ድርጊቱ የዜጎችን በነፃነት የማምለክና የመደሰት መብትን የሚጥስ ከመሆኑም በላይ፣ ግልጽ የሰብአዊ መብት ጥሰት ነው።
WT Media የሚከተሉትን ጥሪዎች ያቀርባል፦
- ድርጊቱን የፈጸመችው የፖሊስ አባል በአፋጣኝ በቁጥጥር ሥር ውላ ለሕግ እንድትቀርብ።
- የአርባ ምንጭ ጤና ሳይንስ ኮሌጅና የጋሞ ዞን ፖሊስ መመሪያ በጉዳዩ ላይ ግልጽ ማብራሪያ እንዲሰጡ።
- ለተጎጂው ተማሪ አስፈላጊው የሕክምና ክትትልና ፍትሕ እንዲረጋገጥለት።
የጭቁኖች ድምፅ – WT Media