GridArt_20260222_152456206

የዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ጉቼ ጉሌ፣ ከወራት ዝምታ በኋላ ስለ ኦቶና ሆስፒታል ወቅታዊ ሁኔታና መልሶ ግንባታ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ፕሬዝዳንቱ ሆስፒታሉ በከፊል አገልግሎት እየሰጠ መሆኑንና ግንባታውን ለመጀመር ከገንዘብ ሚኒስቴር “መልካም ቃል” መገኘቱን ቢገልጹም፣ WT Media ያሰባሰባቸው መረጃዎች ግን አሁንም በሚሊዮን የሚቆጠሩ የዎላይታና የአካባቢው ሕዝቦች በጤና አገልግሎት እጦት እየተሰቃዩ መሆኑን ያመለክታሉ።

ዶ/ር ጉቼ ጉሌ ባወጡት መግለጫ፣ ሆስፒታሉ በእሳት ከወደመ በኋላ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና ሆስፒታሎች የሕክምና መሣሪያዎች ድጋፍ ተደርጎላቸው አገልግሎት መቀጠሉን ገልጸዋል።

ሀዋሳ፣ አርባ ምንጭ፣ ዲላ፣ ጅንካና ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም የክልሉ መንግሥትና የዎላይታ ዞን አስተዳደር ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

ሆስፒታሉ ከሌሎች ተቋማት በሚገኙ “ጥቁር ቁርጥራጭ” ድጋፎች አገልግሎት መስጠቱ የሚበረታታ ቢሆንም፣ ይህ ግን በሚሊዮኖች የሚቆጠር ሕዝብን ፍላጎት ሊያሟላ እንደማይችልና በአሁኑ ወቅት ሆስፒታሉ ለሕዝቡ የሚሰጠው አገልግሎት እጅግ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ከታካሚዎች የሚደረሱ ቅሬታዎች ያረጋግጣሉ።

የመልሶ ግንባታው መዘግየትን በተመለከተ ፕሬዝዳንቱ ሲያስረዱ፦ “ሥራው ተጀምሮ በመንገድ ላይ እንዳይቆም የፌዴራል ገንዘብ ሚኒስቴር እውቅና ሰጥቶ በጀት እንዲመድብ ተገቢው ሥራ ተሠርቷል፤ መልካም ቃልም እየተገኘ ነው” ብለዋል።

WT Media ቀደም ሲል ባደረገው ምርመራ፣ ለመልሶ ግንባታው የተከፈተው አካውንት ውስጥ ያለው 13.1 ሚሊዮን ብር ብቻ መሆኑንና ራሳቸው ፕሬዝዳንቱና ርዕሰ መስተዳድሩ ቃል የገቡትን ገንዘብ አለማስገባታቸውን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

ዛሬም ግንባታው በ”ተስፋ ቃል” ላይ መሆኑ እንጂ ተጨባጭ ግንባታ አለመጀመሩ የሕዝቡን ስጋት አላቀለለም።

ፕሬዝዳንቱ በሚቀጥሉት ከ8 እስከ 10 ወራት ውስጥ ሆስፒታሉ ተጠግኖ ሙሉ አገልግሎት እንደሚሰጥ ቃል ገብተዋል።

WT Media ያነጋገራቸው ታካሚዎች ግን “እስከዚያ ድረስ ስንቱ ሕመምተኛ በግል ሆስፒታሎች ውድ ክፍያና በጤና አገልግሎት እጦት ሕይወቱ ያልፋል?” ሲሉ ይጠይቃሉ።

ቃጠሎው ከደረሰ ወራት ተቆጥረው አሁንም “ግንባታ ለመጀመር በጀት እየተጠበቀ ነው” መባሉ የአመራሩን ዝግተኛነት ያሳያል ተብሏል።

ዶ/ር ጉቼ ዩኒቨርሲቲው የጤናና ሕክምና ትምህርት የልህቀት ማዕከል (Excellence Center) ሆኖ እንደሚቀጥል ቢገልጹም፣ በቅርቡ የዩኒቨርሲቲው ሴነት “የሕክምና ኮሌጁ ከልህቀት ማዕከልነት ይውጣ” የሚል ውሳኔ ማሳለፉን የሚገልጹ መረጃዎች ከውስጥ እየወጡ ይገኛሉ።

ፕሬዝዳንቱ ይህንን ጉዳይ “በትኩረት እንሰራለን” በሚል ቃል ቢሸፍኑትም፣ ተጨባጭ ስጋቱ ግን አልተቀረፈም።

የዶ/ር ጉቼ ጉሌ መግለጫ ከሕዝቡ ከፍተኛ ግፊት በኋላ የመጣ “የማረጋጊያ ቃል” ቢሆንም፣ ተግባራዊነቱ ግን በትልቅ ጥያቄ ምልክት ውስጥ ነው።

ለመልሶ ግንባታው የተሰበሰበው ገንዘብ በግልጽ ኦዲት ተደርጎ ለሕዝብ ይፋ መደረግ አለበት።

“መልካም ቃል” ሳይሆን ተጨባጭ ግንባታ በቦታው ላይ መቼ እንደሚጀመር ሕዝቡ ማወቅ ይፈልጋል። የሕክምና ኮሌጁን ደረጃ ዝቅ ለማድረግ የታቀዱ ሴራዎች በአስቸኳይ ሊቆሙ ይገባል የሚሉ ድምፆች ከፍ ብሎ እየተደመጡ ይገኛሉ።

WT Media የኦቶና ሆስፒታል ግንባታ ተጀምሮ ለአገልግሎት እስኪበቃ ድረስ ለሕዝብ ጆሮና ድምፅ መሆኑን ይቀጥላል።