GridArt_20260224_174601229

ቁጥሮች አይዋሹም፦ የብሔር ጭቆና ቁስል በዎላይታ ሶዶ የሥራ አጥነት መጠን ሲገለጽ

በኢትዮጵያ ከተሞች ካለው አማካይ የሥራ አጥነት መጠን አንጻር የዎላይታ ሶዶ ከተማ አኃዝ በከፍተኛ ሁኔታ ማሻቀቡንና ይህም የዘመናት የብሔር ጭቆና ውጤት መሆኑን ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና ባወጡት አዲስ መጣጥፍ አመልክተዋል።

የWT Media ተጋባዥ ጸሐፊ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና እንደገለፁት የከተማ ሥራ አጥነት (Urban Unemployment Rate) በኢትዮጵያ የከተማ ሥራ አጥነት መጠን ማለት በአንድ ከተማ ውስጥ ለሥራ ብቁ በሆነ የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙና ሥራ እየፈለጉ ያጡ ነዋሪዎችን ብዛት የሚገልጽ ቀመር ነው።

ይህ አኃዝ የኢኮኖሚውን ጤናማነት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራንና ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረግ ፍልሰትን ያሳያል።

እንደ ፕሮፌሰሩ ትንታኔ፣ በቅርብ ዓመታት መረጃ መሠረት በኢትዮጵያ ከተሞች አማካይ የሥራ አጥነት መጠን ከ17% – 23% ሲሆን፣ በ2026 መጨረሻ 19.2% ይሆናል ተብሎ ይገመታል።

ለምሳሌ፦ አዲስ አበባ፦ 22.7% (አሁን እስከ 30% ይደርሳል የሚሉ መረጃዎች አሉ) ድሬዳዋ፦ 23.8% ነው።

የዎላይታ ሶዶ ከተማ የሥራ አጥነት መጠን ከሀገራዊ አማካዩ በእጥፍ በመብለጥ 40% ገደማ መድረሱ ተገልጿል።

አንዳንድ ጥናታዊ መረጃዎች ደግሞ አኃዙን እስከ 61.5% ያደርሱታል። በተለይ የሴቶች ሥራ አጥነት ብቻውን ሲታይ 60% ገደማ መሆኑ ሁኔታውን አሳሳቢ ያደርገዋል።

ከዚህም ባለፈ፣ በከተማዋ ሥራ ላይ ካለው የሰው ኃይል ውስጥ 60% የሚሆነው በኢ-መደበኛው የሥራ ዘርፍ (Informal Sector) ላይ የተሰማራ ነው።

እነዚህ ነዋሪዎች የሥራ ፈቃድ፣ የሥራ ዋስትና፣ ማኅበራዊ ደህንነትና የቁጥጥር ጥበቃ ስለሌላቸው ለከፍተኛ ችግር የተጋለጡ መሆናቸውን ፕሮፌሰሩ ለ WT Media አብራርተዋል።

ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ለዚህ ከፍተኛ የሥራ አጥነት መጠን መንስኤ ናቸው ያሏቸውን ነጥቦች ዘርዝረዋል፦

በዎላይታ ብሔር ላይ ለዘመናት የደረሰው ጭቆና፣ ባለፉት ዓመታት በብሔሩ ተወላጆች ላይ የደረሱ ጥቃቶችና መፈናቀሎች፣ በዞኑ ያለው ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥርና የመሬት አጠቃቀም ፍትሀዊ አለመሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ብልጽግና ፓርቲ ዎላይታ ሶዶን በሁለተኛ ደረጃ ከተማነት ከሚያሳድጋቸው ከተሞች ተርታ አለማካተቱ “የአደባባይ ምስጢር የሆነ የብሔር ጭቆና ነው” ሲሉ ፕሮፌሰሩ ይገልጻሉ።

በከተማዋ ለረዥም ጊዜ ሲጠየቅ የኖረው የኢንዱስትሪ ዞን በፍጥነት መገንባት ችግሩን በትንሹ ሊያቀልለው እንደሚችል የተጠቆመ ቢሆንም፣ በቂ እንዳልሆነ ተገልጿል።

ዎላይታ የራሱ ክልል አለመሆኑ እና የዞኑ የፖሊሲ ቀረጻ ሥልጣን ውሱን መሆኑ ለችግሩ መባባስ የራሱ ድርሻ እንዳለው ተመልክቷል።

“ቁጥሮች አይዋሹም (Numbers don’t lie)” ያሉት ፕሮፌሰሩ፣ ብልጽግና ፓርቲ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትንና ሚዛናዊ ውክልናን መንፈጉን ከቀጠለ እድሜው እንደሚያጥርና ይህም ከባድ ሀገራዊ ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

በመጨረሻም የሕዝብ ወኪል ተብለው በተለያዩ ቦታዎች የተቀመጡ ሰዎች ከታሪክ ተጠያቂነት እንደማያመልጡና ትግላቸው እንደሚጠበቅ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

በዎላይታ በቅርቡ የተደረገው ጥናት እንደሚያመለክተው በዞን ደረጃ ከ200 ሺህ በላይ ከዲፕሎማ በላይ የተማሩ ስራአጥ ወጣቶች ስለመኖሩ አረጋግጧል።

ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏

Voice of Marginalized Community – WT Media