GridArt_20260226_141544126

የወልቃይት ፀገዴና ራያ ጉዳይ የአማራና የትግራይ ክልሎች ብቻ ተደርጎ መወሰዱን የደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢ ፖለቲከኞች ተቃውሟል።

በወልቃይት ፀገዴ እና ራያ አካባቢዎች ዙሪያ የሚነሱ የባለቤትነት እና የምርጫ ክርክሮች አሁንም የቀጠሉ ሲሆን፣ ጉዳዩ የአማራ እና የትግራይ ክልሎች ብቻ ተደርጎ መወሰዱን የደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢ ፖለቲከኞች እና ነዋሪዎች ክፉኛ ተቃውመዋል።

በተለይም በኢትዮ-ትግራይ ጦርነት ወቅት በከንቱ የተሰው የደቡብ ወጣቶች መስዋዕትነት በድርድርም ሆነ በውሳኔ ሂደት ውስጥ ችላ ሊባል እንደማይገባው አሳስበዋል።

የጌታቸው ረዳ ፓርቲ (ትዴት) የጀመረው የክስ ሂደት ሥልጡን አካሄድ ቢሆንም፣ የወልቃይት ፀገዴ እና ራያ ጉዳይ በትግራይ እና በአማራ መካከል ብቻ የሚደረግ ሽሚያ ተደርጎ መወሰዱ ስህተት መሆኑን ፖለቲከኞቹ ይገልጻሉ።

በክሱም ሆነ በማንኛውም የመፍትሔ ሂደት ውስጥ የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝብ ድምፅና ተሳትፎ ሊኖር እንደሚገባ ተጠቁሟል።

የፌዴራል መንግሥት አከራካሪ ቦታዎችን በሕገ-መንግሥቱ አግባብ በጊዜው እልባት ባለመስጠቱ ምክንያት፣ አካባቢዎቹን ለመቆጣጠር በተደረገ ጦርነት የበርካታ ወጣቶች ሕይወት መጥፏል።

በኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ውስጥ የነበሩ የደቡብ ኢትዮጵያ ልጆች በእነዚህ አካባቢዎች በገፍ ተሰውተዋል።

የደቡብ ወጣቶች የፈሰሰውን ደምና አጥንት ታሳቢ ያላደረገ ማንኛውም ውሳኔ “በሰማዕታቱ ላይ የተፈጸመ ክህደት” እና “ወላጆችን ዳግም ማድማት” ተደርጎ ተቆጥሯል።

የአካባቢው ተወላጆች እና ፖለቲከኞች መሠረታዊ ጥያቄዎችን ሰንዝረዋል፦

የደቡብ ወጣት እስከመቼ ነው በማያገባው ጦርነት የሚማገደው? ደምና ነፍሱ ከሌላው ወገኑ አንሶ የታየው ለምንድነው?

የፌዴራል መንግሥት የደቡብ ወጣቶች የከፈሉትን መስዋዕትነት ያላገናዘበ ውሳኔ የመስጠት ሕጋዊ ሥልጣን ሊኖረው አይገባም።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የሰብዓዊ መብት ተቋማት የሚከተሉትን ነጥቦች እንዲያስከብሩ WT Media ጥሪውን ያስተላልፋል፦

በወልቃይት ፀገዴ እና ራያ ለተዋደቁ የደቡብ ወጣቶች ተገቢው መታሰቢያ እና ብሔራዊ እውቅና እንዲሰጥ፤ ሕይወታቸውን ላጡ ወጣቶች ቤተሰቦች የሕግ እና የሞራል ካሣ እንዲከፈል ጠይቋል።

በተጨማሪም በማንኛውም የአከባቢዎቹ ዕጣ ፈንታ ውሳኔ ላይ የልጆቹን ደም የገበረው የደቡብ ሕዝብ መብትና ጥቅም እንዲከበር በሚልም አክለዋል።

የደቡብ ወጣቶች ደምና አጥንት ከንቱ ሊሆን አይገባም። የፌዴራል መንግሥት ለተሰው ሰማዕታት ተገቢውን ክብር ሊሰጥና የቤተሰቦቻቸውን መብት ሊያስከብር እንደሚገባ WT Media ያሳስባል።

ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏

Voice of Marginalized Community – WT Media