Victim

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚኖሩት አቶ ላቁ ማሊሞ (በዎላይታ ሶዶ ከተማ የኦሞ ሸለቆ ሆቴል ባለቤት የነበሩ)፣ ከወይዘሮ ባሎሜ ባሳ ጋር ባላቸው የንብረት ክፍፍል ክርክር ላይ ከሁለት አስርተ ዓመታት በላይ ቢመላለሱም እስካሁን ፍትሕ ማጣታቸውን በመግለጽ  እሮሮአቸውን ለ WT Media አሰምተዋል።

 ግለሰቡ ለሚዲያችን በላኩት የቪዲዮ ምስክርነት እና የፍርድ ቤት ሰነዶች፣ የፍትሕ ሥርዓቱ በደል እየፈጸመባቸው መሆኑን ገልጸዋል።

አቶ ላቁ ከወይዘሮ ባሎሜ ጋር በነበራቸው ጋብቻ ያፈሩትን ንብረት እንዲካፈሉ ቀደም ሲል በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት (በመዝገብ ቁጥር 24782) ውሳኔ አግኝተው ነበር። 

ሆኖም ይህ ውሳኔ በዎላይታ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንዲፈጸም ትዕዛዝ ቢሰጥም፣ የክርክሩ ሰነዶች (ፋይሎች) በወቅቱ በነበረው የአወቃቀር ለውጥ ምክንያት “የመዝገብ ቤት ዝውውር” ሰበብ ደብዛቸው መጥፋቱ በሰነዶቹ ላይ ተመልክቷል።

የደቡብ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በቁጥር 009015 በጻፈው ደብዳቤ፣ በሰበር ደረጃ የተሰጠው ውሳኔ መኖር አለመኖሩ ተጣርቶ ለተበዳዩ ምላሽ እንዲሰጥ ለሶዶ ከተማ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ አስተላልፏል።

የሶዶ ከተማ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በበኩሉ ፋይሉን ለማግኘት ጥረት እያደረገ መሆኑን ቢገልጽም፣ ሰነዶቹ ከ2005 ዓ.ም በኋላ በነበረው የአሠራር ለውጥ ምክንያት ሊገኙ አለመቻላቸውንና አሁንም ፍለጋው መቀጠሉን ገልጿል።

አቶ ላቁ ማሊሞ “ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ የነበረው የሕግ ክርክር ውጤት ሳይሰጠኝ፣ ሰነዶቼም በየቢሮው እየጠፉ ለከፍተኛ እንግልት ተዳርጌአለሁ” ብለዋል።

 በተለይም የንብረት ክፍፍሉን የሚወስነውና የገንዘብ መጠኑን የሚገልጸው ውሳኔ ባለመፈጸሙ ለኢኮኖሚያዊና ለሞራል ስብራት መዳረጋቸውን ገልጸው፣ የሚመለከተው የፍትሕ አካል በአደባባይ መልስ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

አሁንም ፍርድ ቤቱ መዝገቡን እየፈለገን ነው ማለት ገደብ የለሽ ማጉላላትን ከማስከተሉም ባሻገር የእሳቸው የአፈጻጻም መዝገብ መጨረሻ ውሳኔ ደረጃ ከደረሰ በኃላ ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን የነበረው መዝገብ የጠፋበት ምክንያት በፍርድ ቤቱ ከባድ የሙስና መፈጸሙን ያመላክታል።

WT Media ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለ ለሚመለከታቸው የፍትሕ አካላት ጥያቄውን ማቅረቡን እንደሚቀጥል እያረጋገጠ የሚመለከታቸው አካላትም ይሄንን የአደባባይ ፍትህ ማጣት መፍትሔ እንዲሰጡ እንጠይቃለን። 

🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏

Voice of Marginalized Community – WT Media