GridArt_20260417_184935267

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጋሞ ዞን ስር በሚገኘው የቁጫ ምርጫ ክልል፣ ከነገ ቅዳሜ ሚያዝያ 10 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ለሚካሄደው የምርጫ ቅስቀሳ መርሃ-ግብር የፌዴራል ፖሊስ አባላት ስምሪት መጀመሩን የቁጫ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቁሕዴፓ) አረጋግጧል።

​የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በጻፈው ደብዳቤ መሠረት፣ በቁጫ ምርጫ ክልል ለሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች አስፈላጊው የጸጥታ ጥበቃ እንዲደረግ ጥያቄ አቅርቦ ነበር።

በዚህም መሠረት የጸጥታ ኃይሉ ከዛሬ ጀምሮ ወደ ሰላምበር ከተማ መግባቱ የተረጋገጠ ሲሆን፣ ዓላማውም ለ7ኛው አጠቃላይ ምርጫ የሚደረጉ የቅስቀሳ መርሃ-ግብሮች በሰላማዊ ሁኔታ እንዲጠናቀቁ ማስቻል መሆኑ ታውቋል።
​
​የቁጫ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቁሕዴፓ) በሰላምበር ከተማ በሚገኘው ሁለ-ገብ የሕዝብ መሰብሰቢያ አዳራሽ ለሚያካሂደው ታላቅ የቅስቀሳ መርሃ-ግብር መላው የቁጫ ሕዝብ እንዲገኝ ጥሪ አቅርቧል።

ፓርቲው በሰጠው መግለጫ ​የጸጥታ ስጋት የሌለ መሆኑን በመግለጽ ሕዝቡ ያለምንም ማመንታት በነቂስ እንዲወጣ ጥሪ አድርጓል።

​በፕሮግራሙ ላይ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮችና ዕጩዎች እንደሚገኙ ታውቋል።

WT Media በምርጫው ሂደትና በጸጥታው ሁኔታ ዙሪያ የሚኖሩ አዳዲስ መረጃዎችን እየተከታተለ ለተከታታዮቹ የሚያቀርብ መሆኑን እንገልጻለን።