በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በዎላይታ ዞን እና በሲዳማ ክልል አጎራባች በሆነው አበላ አባያ፣ ብላቴ ቀበሌ ባለፈው አርብ ስድስት ሰዎች ከሲዳማ ክልል በኩል ዘልቀው በገቡ ታጣቂዎች ታፍነው መወሰዳቸውን ለ WT Media የደረሰው መረጃ አመልክቷል።
የአካባቢው ምንጮች እንደገለጹት፣ የታገቱት ሰዎች ሶስቱ የዎላይታ ሚሊሻዎች ሲሆኑ፣ ሶስቱ ደግሞ የአካባቢው ሲቪል ማህበረሰብ አባላት መሆናቸው ታውቋል።
እነዚህ ሰዎች የታገቱት ባለፈው ቅዳሜ ሲሆን፣ እስካሁን ያሉበት ሁኔታም ሆነ አጋቾቹ እነማን እንደሆኑ በውል አለመታወቁ የአካባቢውን ነዋሪዎችና ቤተሰቦችን ለከፍተኛ ስጋት ዳርጓል።
የታገቱት ሚሊሻዎች በቅርቡ የዎላይታ ዞን አስተዳዳሪዎች በተገኙበት ሰልጥነው የወጡ ቢሆንም፣ በወቅቱ ትጥቅ ያልነበራቸው መሆኑ ለእገታው አጋልጧቸዋል ተብሏል።
የታገቱ ሰዎች ቤተሰቦች በ WT Media አማካኝነት ለመንግስት ባስተላለፉት ጥሪ፣ ልጆቻቸው ያሉበት ታውቆ በአስቸኳይ እንዲፈቱና መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።
ነዋሪዎች በበኩላቸው አካባቢው በተደጋጋሚ ከፍተኛ የፀጥታ ችግር የሚታይበት መሆኑን ገልጸው፣ በተመሳሳይ ሁኔታ ሰዎች ሲገደሉና ሲታገቱ የዞኑ አስተዳደር ለጉዳዩ ትኩረት አልሰጠም ሲሉ ቅሬታቸውን አቅርበዋል።
WT Media ስለዚህ የእገታ መረጃ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ወደ ሲዳማ ክልል እና ወደ ዎላይታ ዞን የሚመለከታቸው የጸጥታ ኃላፊዎች ጋር ተደጋጋሚ ስልክ ቢደውልም፣ ሙከራው ሳይሳካ ቀርቷል።
የአካባቢው የጸጥታ መዋቅር ደካማ መሆን ለእንዲህ አይነት ድርጊቶች መስፋፋት ምክንያት መሆኑን የሚገልጹት ምንጮች፣ መንግስት በአፋጣኝ ጣልቃ ገብቶ የታጋቾችን ደህንነት እንዲያረጋግጥ እየጠየቁ ይገኛሉ።
WT Media የጉዳዩን ሂደት እየተከታተለ ተጨማሪ መረጃዎችን እንደደረሱት ይፋ የሚያደርግ ይሆናል።
🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏
Voice of Marginalized Community – WT Media